«የምርጫ ቦርዱ የፕሪቶሪያዉን ስምምነት ወደ ጎን እየገፋ ነው» ህወሓት
ሰኞ፣ ግንቦት 4 2017'አሁን ላይ የሚሰረዝ ህወሓት የለም፣ ህወሓት የተሰረዘው በ2013 ዓመተምህረት ነው' ህወሓት
ህወሓት በ2013 ዓ/ም የተሰረዘው እውቅና እንዲመለስለት እንደሚሻ አስታወቀ። ከዚህ ውጭ የሆነ አዲስ ምዝገባም ይሁን አውቅና እንደማይሻም ገልጿል። ህወሓት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፕሪቶርያ ስምምነት ወደጎን የገፋ አካሄድ እየተከተለ ነው ሲልም ወቅሷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ለህወሓት 'በልዩ ሁኔታ' የሰጠው የተባለ የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት፥ እሱን ተከትሎ መፈፀም ይገባው የነበሩ ግዴታዎች ባለመፈፀሙ ፓርቲው ማገዱ ባለፈው የካቲት 6 ቀን 2017 ዓመተምህረት መግለፁ ይታወሳል። ምርጫ ቦርድ ለህወሓት በተሰጠው የሶስት ወራት እግድ ግዜ ውስጥ የማስተካከያ የተባሉ እርምጃዎች የማይወስድ ከሆነ፥ ህወሓት በቀጥታ እንደሚሰረዝ ማስታወቁንም አይዘነጋም። ይህ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ቀነ ገደብ ነገ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓመተምህረት የሚጠናቀቅ ሲሆን የቦርዱ የእስካሁን ሂደት የተቃወመው ህወሓት በበኩሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት በአንፃሩ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ እና ለውሉ እውቀና ካለመስጠት የሚነሳ መተማመንን የሚሸረሽር ፖለቲካዊ አቋም 'በሕግ ሽፋን' እያራመደ ነው ከሷል።
በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት የጠየቀዉ ህወሓት
ፓርቲው በሳምንቱ መጨረሻ ባሰራጨው መግለጫ ህወሓት ገና የሚሰረዝ ሳይሆን፥ ከ2013 ዓመተምህረት ጥር ወር ወዲህ ባለው ግዜ ሕጋዊ እውቅናው እንደተነፈገ ነው ያለ ሲሆን፥ ህወሓት ያልተቀበለው ግን ደግሞ ቦርዱ የሰጠው ሰርትፌኬት እሰርዛለሁ የሚል ከሆነ ግን ምርጫ ቦርዱ መሰረዝ ይችላል ሲል ህወሓት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ውሳኔ አጣጥሏል። ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ጉዳዮች የዳሰሰ ማብራሪያ ለህወሓት ይፋዊ ልሳን ወይን ሚድያ የተናገሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው፥ የህወሓት ሕጋዊ እውቅና መመለስ ጉዳይ ከፕሪቶርያው ስምምነት ጋር ተያይዞ የሚታይ እና መመለስ ያለበትም በዚሁ አግባብ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
የህወሐት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል "እኛ እያልን ያለነው፥ በ2013 ዓመተምህረት የተሰረዘው እውቅናችን ይመለስ ነው። ሃምሳ አመት ያስቆጠረው ፓርቲ በ2016 ዓመተምህረት በተሰጠ እውቅና ልንተካው አንችልም። አዲስ ህወሓት ማለት ነው፥ ይህ ደግሞ አይሆንም። የጠየቅነው በ2013 የተሰረዘው ይለስ፥ እነሱ የሰጡን ደግሞ አዲስ ምዝገባ ነው። እኛ ደግሞ በወቅቱ አንቀበልም ብለናን። አሁን እየተደረገ ያለው ቴክኒካዊ ጨዋታ ነው። ራሳቸው የመዘገቡት ራሳየው ሊሰርዙት ይችላሉ። ይህ ለህወሓት የሚመለከት አይደለም" ብለዋል።
የህወሓት ሊቀ-መንበር በፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት ላይ በአፋጣኝ ውይይት እንዲደረግ ጠየቁ
ህወሓት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በሙሉእነት አልተተገበረም፣ በሙሉእነት ላለመተግበሩ ደግሞ የፌደራሉ መንግስት ለዚሁ መፈፀም ዝግጁነት አለማሳየቱ እንደ ምክንያት የሚያነሳ ሲሆን፥ የህወሓቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን እንዳሉትም የትግራይ አስተዳደራዊ ግዛት አሁንም አልተመለሰም እንዲሁም የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት አልተረጋገጠም የሚሉ እና ሌሎች ነጥቦች በማሳያነት አንስተዋል። ይሁንና ጦርነቱ ያስቆመው የሰላም ስምምነት በማክበር ህወሓት እንደሚሰራ፣ ባልተፈፀሙ የስምምነቱ ይዘቶች ምክንያት ውሉ ሙሉበሙሉ የሚፈርስበት አጋጣሚ ብያንስ በህወሓት በኩል የለም ሲሉም አክለዋል።
"ከፕሪቶርያ ስምምነት ጋር በተገናኘ፥ በነበረበት ይቀጥላል። አፈፃፀሙ እንደተገለፀው ነው። ችግሮች አሉት። ይሁንና በምርጫ ቦርድ [የግንቦት አምስት ቀጠሮ] መሰረት ብያንስ በእኛ በኩል የሚቋረጥ ነገር የለም፥ ግንኙነቱም ይቀጥላል። ግዝያዊ አስተዳደሩም ይቀጥላል፣ የፕሪቶርያ ስምምነቱም ይቀጥላል። ሆን ተብሎ የሚደረግ ነገር ካለ ግን ሌላ ነው። አደገኛ ይሆናል፣ እንዲከሰተም አንሻም" ሲሉ ዶክተር ደብረፅዮን ተናግረዋል።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በሁለት ዓመቱ የስልጣን ጊዜ ምን አሳካ?
የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት የመመለስ ጉዳይ በዋነኝነት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ሊያጠነው ይገባል ያለው ህወሓት ከዚህ በተጨማሪ የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ያደራደሩ የዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ አካላት፣ አፍሪካ ሕብረት እና ኢጋደ ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊ እና ሞራላዊ ሐላፊነታችሁ ተዋጡ ሲልም ጥሪ አቅርቧል።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ