የኢሰመኮ መግለጫ የኦሮሚያ ክልል ማስተባበያ፤ የትግራይ የጦርነት ሰለባዎች፤ የሰላም ውይይት ጥሪ
ዓርብ፣ መስከረም 11 2016በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ጊዜያዊ የሰዎች ማቆያ ስፍራ በተላላፊ በሽታ ምክንያት የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታውቋል። በማቆያ ቦታው ከነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል 190 ሰዎችም በሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት ያገኙ መሆኑን በመግለጫው ዘርዝሯል። ጊዜያዊ የሰዎች ማቆያዎቹ ለሰዎች ተብለው የተዘጋጁ ባለመሆኑ የንጽህና ጉድለት መኖሩንም የኢሰመኮ ዘገባ ያመለክታል። ሆኖም የኦሮሚያ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ባለሥልጣን «አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ በክልሉ በሸገር ከተማም ሆነ በፍቼ ከተማ ምንም ዓይነት የማቆያ ስፍራ አለመኖሩን ማረጋገጥ እንወዳለን» የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ከተመለከቱት አንዱ አድማሱ መንገሻ፤ «ገላን 2 ማጎሪያ መጋዘን አለ» በማለት ማስተባበያው ሃሰት ነው ሲሉ፤ኦሮሚያ ኢትዮጵያ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «ከ5 በላይ ሜጎሪያ በኦሮሚያ አለ።» ነው የሚሉት። ጌታቸው መኩሪያ ያደሳ ደግሞ፤ «የጎዳና ተዳዳሪዎች መቆያ ነው ጽንፈኞች ግን የአማራ ታሳሪዎች በማለት ሲያረግቡ ነበር።» ነው የሚሉት። አሌክስ መላኩ በበኩላቸው፤ «እያመኑ መጡ ከ30 ሺህ በላይ አማራ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ አለ።» ይላሉ። ታምሩ ጉታ፤ «ሸገር የሰቆቃ ምድር» ነው ያሉት በአጭሩ። አበቃ ዘመኑ የተባሉ ሌላው የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «አንድ ህዝብ ሆነን አንዱ አሰቃይ ሌላው ተሰቃይ ለምን ???» በማለት ጠየቁ፤ ፋንታሁን አወቀ ደግሞ፤ «ታሪክ ራሱን ደገመ።» አሉ። ማሂር ዑስሪ ዩስራም ሌላው ጠያቂ ናቸው፤ « ሰብዓዊ መብት ፣ በወለጋ ሰው ሲያልቅ የት ነበር?» ብለው።
እስካሁን ድረስ ቁጥሩ በይፋ ባይገለጽም ለሁለት ዓመታት በትግራይ ኃይሎች እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በተደረገው ጦርነት «በሺዎች የሚቆጠሩ» የትግራይ ተዋጊዎች መሞታቸው፣ በርካቶችም ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰሞኑ በጦርነቱ አካላቸው ለተጎዳው የገነባው ማዕከል ሥራ መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን ለሟች ቤተሰቦችም መርዶ እንደሚነገር ይፋ አድርጓል። የማዕከሉን ምረቃ የሚያሳየው ቪዲዮ በዶቼ ቬለ የፌስቡክ ገጽ ከ60 ሺህ በላይ ዕይታ ያገኘ ሲሆን ከመቶ በላይ ሰዎችም አስተያየታቸውን በጽሑፍን በምልክቶች ገልጸውበታል። ፈረምኩኝ ላላፈቅር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በአጭሩ፤ «ምስኪን ወገኔ» ሲሉ መስፍን ግርማ፤ «እነዚህ ወጣት ሴቶች እና ወንዶች እንዲህ ሆነው መመልከት በጣም አሳዛኝ እና የሚያምም ነው። የጥፋቱ ተጠያቂዎች በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ እና በምኒሊክ ቤተመንግሥት ተደላድለው ይኖራሉ።» ነው ያሉት። ሲሳይ አዳነም በበኩላቸው፤ «አይ የኛ አገር ፖለቲካ ፣ የደሐ ልጅ በዊልቸርና በክራንች ይሔዳል፤ የነ እንትና ልጆች ግን በሽጉጥ የቮድካ እና የውስኪ ኮርኪ ይከፍታሉ።» በማለት ስሜታቸውን አጋርተዋል። ሳዲ ቼቡብ ደግሞ፤ «ለኢትዮጵያ ወጣቶች ሁሉ በጣም አሳዛኝ ጊዜ ነው፤ በየጊዜው ወጣቶቻችንን መስዋዕት ማድረጉ ታሪካችን ነው። እባክህ ፈጣሪ ተመልከተንና መፍትሄ አምጣልን!» ብለዋል። የሺምቤት አንዳርጌ፤ «አይ ጦርነት» ሲሉ ተስፋዬ ግርማም፤ «የጦርነት መጨረሻው ይሄ ነው ሲገቡ ተጨበጨበላቸው አልተጨበጨበላቸው ወደነበሩበት ይመልሳቸዋል? አይመልስም።» በማለት የጦርነት ተጎጂዎቹ ወደተዘጋጀው ማዕከል አዳራሽ ሲገቡ ያጀባቸውን ጭብጨባም አያይዘው አስተያየታቸውን አጋርተዋል። እንቹ ጌታነህ፤ «ፖለቲካ ቆሻሻ ነው፤» በማለት ሲተቹ፤ መቅደስ አማን በበኩላቸው፤ «የጦርነት ትርፉ ይኸው ነው» ብለዋል። በትግሪኛ አስተያየታቸውን ካካፈሉት መካከል ሆወይ ወለይ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ሰሎሞን በየነ፤ «ዘላለማዊ ክብር ለጀግኖቻችን» ብለዋል። ሣባ ንግስቲም፤ «ለእኛ ሲሉ ዋጋ የከፈሉ» ነው ያሉት። ምሕረተአብ ገብረ ሥላሴ ደግሞ፤ «ትግራይየጦር ጀግኖች እንጂ ጉዳተኞች የሏትም ። ልባቸው ፥ መንፈሳቸው ፥ አይምሯቸው እጅግ ጠንካራ ነው።» ይላሉ። ሃዳስ አባይ በበኩላቸው፤ «ከዚህ ኣሳዛኝ ድርጊት በኋላ የትውልድ ቅብብሎሽ ህልውና ለመታደግ የሚገጥሙ ችግሮችን ሰከን ብሎ በማሰብና ስልጡን በሆነ አካሄድ በጠረጴዛ ዙሪያ ነገሮችን መፍታት አማራጭ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ድርጊት ለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ፈጣሪ ከጎናቸው ይሁን።» ብለዋል። እሙ ተስፋ ደግሞ፤ «የኛ ችግር ብዛቱ ኡኡኡኡ» በማለት የተሰማቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን ውጊያ እና ግጭት በሰላም ውይይት መፍታት እንደሚገባ በማሳሰብ በተለያዩ አካላት ጥሪ እየቀረበ ነው። ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ላቀረበው የሰላም ውይይት በጎ ምላሽ እያገኘ መሆኑን ሲገልጽ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም እንዲሁ ገዢው ፓርቲም ሆነ ነፍጥ ያነሱ ኃይሎች ለድርድር እና ውይይት አማራጭ ቅድሚያ እንዲሰጡ እያሳሰቡ ነው። የግጭት መንስኤዎችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ፤ካልተቻለ በአማራ ክልል ከሚካሄደው ውጊያ ጎን ለጎን በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች፤ እንዲሁም በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል ድንበር አካባቢዎች የሚቀሰቀሱት ግጭቶች እንዳይስፋፉ ስጋታ መኖሩ እየተገጸ ነው። ሰሎሞን አንበሳው፤ «መንግሥት ድርድር ይገባል ይግባ ይደራደር የሚሉ አሉ ትክክል አይደለም መንግስት ድርድር አይፈልግም።» በማለት ረዝም ያለ አስተያየት አካፍለዋል። ላሚ ዲሪ በበኩላቸው፤ «መንግሥት እንደ መንግሥት ከሁሉም ፓርቲዎችና ከሁሉም የፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ቢወያይ ለሀገራችን መፍትሄ ሊገኝ ይችል ይሆናል! ነገር ግን ከፋኖ ጋር መወያየት ሀገሪቱን ወደ ገደል እንደ መክተት ይቆጠራል!» ይላሉ። መስፍን ሻምበል ግን፤ «ለሰላም በሩን ዘግቶ ሰላም ሰላም መዘመር ውጤቱ ዜሮ ነው» ነው የሚሉት። ነሲቡ ኬ ማራሚም እንዲሁ ፤ «አንድ ጣት ስትቀስር ሦስቱ ወደ ቀሳሪው፤ ሌላኛው ውጫዊ ያመላክታል። ከኔ ምን ከእሱስ ከሌላኛውስ ምን ይጠበቃል? ይገባል? የሚል ሀሳብ የጉዳዩ ማጠንጠኛ መሆን አለበት ።» በማለት ድርድር ወይም ውይይት ሲባል ሊታሰብ ይገባል ያሉትን ጠቅመዋል። ዳግም በላይ ደግሞ፤ «ሺህ ዓመት ብንዋጋ ችግሩ መጨረሻ ላይ የሚፈታው በድርድር ነው። ሌላው 10 ፋኖ ስንገድል ሌላ 1000 ፋኖ መፈልፈሉ ተፈጥሯዊ ነው ።በከንቱ ደምና ሀብት አይፍሰስ ።» ይላሉ።
ታገስ ታሸንፋለህ ደግሞ ፤ «የምክክር ኮምሽኑ ነፃና ገለልተኛ ነው ተብሎ ይታመናል? ይሁን እንመነው ሰላም ካመጣ፤ ግን መንግሥት ሃሳቡ ምንድነው በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ ይህን ያህል ህዝብ ሲያልቅ ንብረት ሲወድም ምንድነው የጎደለኝ ህዝብ ከኔ ምን ይፈልጋል? የሚለውን ለምን ቆሞ እራሱን አይፈትሽም? ሁሌ ህዝብን ጥፋተኛ ከሚል።» በማለት ይጠይቃሉ። ተፈራ አዲሱ የምክክር ኮሚሽኑን ለተመለከተው ጥያቄ፤ «የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ሥራ እየሠራ እኮ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ተከለከሉ እንዴ ? ምንድነው ያለው አዲስ ሃሳብ? የምክክር ኮሚሽኑም መግለጫ ሰጥቷል።» ሲሉ፤ ገረመው ጌቾም እንዲሁ፤ «ፈጣሪ ከረዳን ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ብቻ ነው አሁን ተስፋ የሚጣልበት» ይላሉ። ጃገማ ኬሎ፤ «አቤቱ ታረቀን በቃችሁ በለን» ሲሉ፤ ያውሩ ሥራቸው ነው በበኩላቸው፤ «ጸልዩ እንጸልይ» ብለዋል፤ አዲሱ አበበ ተስፋ ያደረጉ ይመስላል፤ «ከጨለመ ንጋት ይመጣል።» ነው አስተያየታቸው።
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ