“ሰላም ከሌለ ልማት የለም” የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ሲዲ ዑል ታ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 28 2017የ60 ዓመቱ ሲዲ ዑል ታ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሚያስገነባው አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚያበድረው የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንትነታቸውን ባለፈው ሰኞ ተረክበዋል። ከአራት ዓመታት ገደማ በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደው ግንባታ ከሚያስፈልገው 10 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ አየር መንገዱ 20% ይሸፍናል።
ናይጄሪያዊው አኪንዉሚ አዴሲና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለማ ያደቻ ጋር በነሐሴ 2017 መጀመሪያ በተፈራረሙት ሥምምነት የአፍሪካ ልማት ባንክ ለግንባታው የሚያስፈልገውን 8 ቢሊዮን ዶላር ብድር የማፈላለግ ኃላፊነት ወስዷል። የቀድሞው የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዝደንት “እጅግ በጣም ደስ ብሎናል” ነበር ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለባንካቸው ስለሰጠው ኃላፊነት ሲናገሩ።
አዴሲና ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው አስር ዓመታት የአፍሪካ ልማት ባንክ ከ55 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለመሠረተ-ልማት ግንባታ እንዳቀረበ ሲናገሩ በኩራት ነው። በወቅቱ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንትነታቸውን ለማስረከብ የቀሯቸው ጥቂት ሣምንታት ቢሆኑም “ኢትዮጵያ ይህን ህልም እንድታሳካ ለመደገፍ ከጎኗ እንገኛለን” ብለው ነበር።
አኪንዉሚ አዴሲናን የተኩት አዲሱ ፕሬዝደንት የፋይናንስ ሚኒስትሮች እና የብሔራዊ ባንክ ገዥዎችን በሚያካትተው የአፍሪካ ልማት ባንክ አስተዳደር ቦርድ የተመረጡት ግንቦት 21 ቀን 2017 በተካሔደ ምርጫ ነው። አምስት እጩዎች የቀረቡበት ምርጫ በሦስት ዙሮች የተካሔደ ሲሆን ሲዲ ዑል ታ ከተሰጡ ድምጾች 76% አግኝተዋል።
ከተመሠረተ 60 ዓመታት ያስቆጠረው የአፍሪካ ልማት ባንክ አኪንዉሚ አዴሲናን ሸኝቶ በታሪኩ ዘጠነኛው የሆኑትን ፕሬዝደንት የሾመው በኮት ዲቯር የኢኮኖሚ ከተማ አቢጃን ነሐሴ 26 ቀን 2017 በተካሔደ መርሐ-ግብር ነው።
ኃላፊነታቸውን በይፋ ከተረከቡ በኋላ አዲሱ ፕሬዝደንት ባሰሙት ንግግር ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ነዋሪዎች ያሉት አፍሪካ ከጥገኝነት በመላቀቅ በራሱ አቅም፣ ፍላጎት እና ውክልና እንዲቆም ባንካቸው ላቅ ያለ ሚና መጫወት አለበት የሚል ዕምነት እንዳላቸው ጥቆማ ሰጥተዋል። ለዚህም በተለይ ከአኅጉሩ ሕዝብ 70 በመቶ ገደማ ለሚሆነው ወጣት ትኩረት እንዲሰጥ ይሻሉ።
“በክፍለ-ዘመኑ አጋማሽ በዓለም ላይ ከሚኖረው አራት ሰው አንዱ አፍሪካዊ ይሆናል። አኅጉራችን የወጣቶች፣ ትልቅ የለውጥ ፍላጎት እና እምቅ አቅም ያለው ነው። የለውጥ አንቀሳቃሽ ሆኖ ጥቅም ላይ መዋል ያለበት ኃይል ይህ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ሲዲ ዑል ታ ላለፉት 10 ዓመታት ዋና መቀመጫውን በሱዳን ዋና ከተማ ኻርቱም ያደረገውን የአረብ ባንክ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት ሲመሩ ቆይተዋል። ከዚያ በፊት የግብርና እንዲሁም የኢኮኖሚ እና ገጠር ልማት ሚኒስትር ሥልጣኖችን ጨምሮ በሞሪታኒያ መንግሥት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ሠርተዋል።
አዲሱ ፕሬዝደንት በፈረንሳይኛ እና በእንግሊዘኛ ያሰሙት ንግግር በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ምን ሊሰሩ እንዳቀዱ ይፋ ያደረጉበት ብቻ አይደለም። በግጭት እና ጦርነት በሚታመስ አኅጉር ብልጽግና ያለ ሰላም ሊታሰብ እንደማይችል ማስጠንቀቂያ የሰጡበት ጭምር ነበር።
በልማት ዙሪያ ያለውን ተዋስዖ ቅርጽ ለመስጠት በግብዓትነት ከሚያገለግሉ ዋንኛ ነገሮች አንዱ የሰላም አስፈላጊነት እንደሆነ ያስታወሱት ሲዲ ዑል ታ ጉዳዩ ለረዥም ጊዜ በዘለቀው መደበኛ የብልጽግና ግንባታ ሒደት አስተምህሮ ለመረሳት የተቃረበ እንደሆነ ጠቁመዋል። ይህ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ የመዋዕለ-ንዋይ ዕቅዱን በአስቸኳይ መልሶ እንዲመለከት እና በሰላም ላይ ያተኮረ አንድ ክፍል እንዲያካትት እንዳስገደደውም ገልጸዋል።
“ሰላም ከሌለ ልማት የለም። ልማት ከሌለ ሰላም የለም” ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል። “አፍሪካ እያየን ነው። ወጣቶች እየጠበቁን ነው” ያሉት አዲሱ ፕሬዝደንት “ጊዜው የተግባር ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ኢኮኖሚዎቻችንን መደበኛ ማድረግ፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ተቋሞቻችንን ማጠናከር እና ሥራ ፈጠራን ማበረታታት ይኖርብናል። ወጣቶች እና ሴቶችን ማበረታታት ገንዘብ፣ ሥልጠና እና ቴክኖሎጂ ይፈልጋል። እነዚህን መደገፍ ብሩህ መጻኢ ጊዜ ይገነባል” የሚል አቋም አላቸው።
የአፍሪካ ልማት ባንክ በአጠቃላይ 81 ባለድርሻ አባል ሀገራት አሉት። ከእነዚህ ውስጥ 54 የአፍሪካ ሀገራት ሲሆኑ የቀሩት 27 የባንኩ ባለ ድርሻዎች ከአፍሪካ ውጪ የሚገኙ ናቸው። የአፍሪካ ሀገራት ከባንኩ አጠቃላይ ድምጽ 58.7% ድርሻ አላቸው።
ከባንኩ ባለድርሻዎች መካከል ከፍተኛውን ተደማጭነት የያዘችው 9.3% ድምጽ ያላት ናይጄሪያ ነች። ግብጽ 6.3%፣ አልጄሪያ 5.3%፣ ደቡብ አፍሪካ 5% እንዲሁም ሞሮኮ 4.8% ድምጽ አላቸው።
በፋይናንስ ሚኒስትሯ የምትወከለው ኢትዮጵያ ያላት የድምጽ ድርሻ ግን 1.5% ብቻ ነው። አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ካናዳ እንደ ቅደም ተከተላቸው በአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ውስጥ ከፍተኛ ድምጽ ያላቸው ከአፍሪካ ውጪ የሚገኙ ሀገሮች ናቸው።
ባንኩ በጎርጎሮሳዊው 2024 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ 8.47 ቢሊዮን ዶላር አከፋፍሏል። የገንዘቡ መጠን በቀደመው ዓመት ከነበረው 6.1 ቢሊዮን ዶላር የላቀ ቢሆንም ከአኅጉሩ ፍላጎት አኳያም ሆነ ከሌሎች ተመሣሣይ ተቋማት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ባለፈው ዓመት የአፍሪካ ልማት ባንክ ወጪ ካደረገው ገንዘብ ውስጥ 29 በመቶ የሚሆነው ለኢንዱስትሪ የተመደበ እንደሆነ ዓመታዊው ሪፖርት ያሳያል። የገንዘብ ክፍፍሉ በክፍለ አኅጉር ደረጃ ቢመዘን 2.29 ቢሊዮን ዶላር የተፈቀደለት ደቡባዊ አፍሪካ 27% ድርሻ በመውሰድ ቀዳሚ ሆኖ ይገኛል።
ከአኅጉራዊው ባንክ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የደረሰው ምሥራቅ አፍሪካ 24% ድርሻ በመያዝ ሁለተኛ ነው። ምዕራብ አፍሪካ በ1.85 ቢሊዮን ዶላር ሦስተኛ፣ ሰሜን አፍሪካ በ1.19 ቢሊዮን ዶላር አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ 94 ሚሊዮን ዶላር የተፈቀደለት ማዕከላዊ አፍሪካ በመጨረሻ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አዲሱ ፕሬዝደንት ግን “የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ለሁሉም ወገን ሁሉንም ነገር የመሆን ዓላማ ሊኖረው አይችልም” የሚል አቋም አላቸው። ሥራቸውን በይፋ ሲጀምሩ “ሁልጊዜም በአጋርነት መንፈስ መርፌውን የበለጠ ማንቀሳቀስ የሚችልበት ላይ ማተኮር አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።
“በመገለል ሳይሆን በመተባበር በጋራ አፍሪካ በራሷ ምርጫ የሚያገለግላት የፋይናንስ ሥርዓት ለማበጀት ከመንግሥታት፣ የግሉ ዘርፍ እና ከዓለም አቀፍ አግሮቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን መሥራት አለብን” ሲሉ በሥራ ዘመናቸው ሊከተሉት ስለሚችሉት አካሔድ ጥቆማ ሰጥተዋል።
መቀመጫውን በአቢጃን ያደረገው የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን አንገብጋቢ ጉዳዮች ግን ብቻውን ማሳካት እንደማይችል አዲሱ ፕሬዝደንት አላጡትም። ለዚህም አጋርነት መመሥረት ቁልፍ ጉዳይ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ዓለም ባንክን ከመሣሠሉ ተቋማት ጋር በትብብር የሚሠራ ቢሆንም ሀገራት ከመሠረቷቸው ሶቭሪን ፈንዶች እና የጡረታ ፈንዶች ጋር አጋርነት እንዲመሠርት ፍላጎት እንዳላቸው ጥቆማ ሰጥተዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ቀዳሚ ግብ በልማት እና ማኅበራዊ ዕድገት አስተዋጽዖ የአባል ሀገራቱን ድሕነት መቀነስ ነው። የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአፍሪካ የልማት ፈንድ እና የናይጄሪያ ትረስ ፈንድ ዓላማውን ለማሳካት የሚጠቀምባቸው ተቋማት ናቸው።
ሲዲ ዑል ታ የአፍሪካ ልማት ባንክን ለመምራት ኃላፊነት የወሰዱበት ጊዜ ግን ለተቋማቸውም ይሁን ፕሬዝዳንቱ ለሚመኙት አጋርነት ፈታኝ ይመስላል። የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራትን ለሚደግፉ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሮጀክቶች አሜሪካ የምትሰጠውን 555 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የማቋረጥ ዕቅድ አለው።
በትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ በቀጥታ የሚጎዳው ለደሐ የአፍሪካ ሀገሮች በዝቅተኛ ወለድ የሚያበድረው የአፍሪካ የልማት ፈንድ ይሆናል። የአፍሪካ የልማት ፈንድ በሥራው ወጪ የሚያደርገው ገንዘብ በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ በአባል ሀገራቱ መተካት አለበት። ይህ በሚቀጥለው ሕዳር ሊከናወን የታቀደ ሲሆን የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ 25 ቢሊዮን ዶላር የማሰባሰብ ዕቅድ ነበረው።
ይህ ዕቅድ እንዳይደናቀፍ አዲሱ ፕሬዝደንት አሜሪካ ውሳኔዋን እንድትቀለብስ ማሳመን አሊያም ከአፍሪካ ውጪ ከሚገኙ እንደ ቻይና፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ያሉ ሀገሮች ተጨማሪ ገንዘብ የማፈላለግ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል። የአፍሪካ ሀገሮች ተጨማሪ ገንዘብ በማዋጣት የጎደለውን እንዲሞሉ ማግባባት ሌላው አማራጭ ሊሆን ይችላል።
በምረጡኝ ዘመቻቸው ወቅት ሲዲ ዑል ታ አሜሪካ የውጪ ርዳታ ስታቆም የአፍሪካ ልማት ባንክ አማራጭ ማፈላለግ እንደሚኖርበት ሲያሳስቡ ነበር። አሜሪካ መራሹ ምዕራቡ ዓለም ለውጪ ርዳታ የሚሰጠውን ድጋፍ በመቀነሱ አዲስ አጋር በሚያስፈልግበት ወቅት የአረብ ባንክን በኃላፊነት የመሩት የሞሪታኒያው ሰው ከገልፍ ሀገሮች ጋር ያላቸው ግንኙነት እንደ በጎ ጎን ተቆጥሮላቸዋል።
ከውጪ የልማት ዕርዳታ መቀነስ በተጨማሪ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የአፍሪካ ሀገሮችን የሚፈታተነው ከፍተኛ ዕዳ እና የከባቢ አየር ለውጥ ዳፋዎች ሌሎች ፈተናዎች እንደሆኑ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕን የሚመሩት ሲዲ ዑል ታ አምነዋል።
“ስነ-ሕዝብ፣ ቴክኖሎጂ ወይም ከባቢ አየርን የመሳሰሉ የዘመናችን ተግዳሮቶች ዓለም አቀፍ ናቸው” ያሉት ሲዲ ዑል ታ “አፍሪካ ሙሉ ሚናዋን ካልተጫወተች መፍትሔዎቻቸው ዓለም አቀፍ ሊሆኑ አይችሉም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። የአኅጉራዊው ባንክ ፕሬዝደንት “የእኛ ሚና ለችግሮች የሚበጁ መፍትሔዎች በአፍሪካ አመለካከት፣ አፍሪካ ቅድሚያ በትምሰጣቸው ጉዳዮች እና በአፍሪካ ውክልና የተቃኙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
አዲሱ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዝደንት በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት የተቋሙን “የሥራ ክንውን ለማፋጠን፣ አተገባበሩን ለማቀላጠፍ እና የቢሮክራሲ ማነቆዎችን ለማቃለል” የሚያስችል “ፈጣን የማሻሻያ” ተግባራዊ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ፕሬዝደንቱ ተቋሙ ዘላቂ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚያስፈገውን ከፍተኛ ገንዘብ ለማሰባሰብ ከአፍሪካ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማጥበቅ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ።
በተለይ የአፍሪካ የልማት ፈንድ ካፒታልን የመሙላት አንገብጋቢ ሥራ በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት ዋና ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል። “የፋይናንስ አቅርቦትን ለማስፋፋት፣ ሥራ ለመፍጠር፣ ሴቶች እና ወጣቶችን ለማበረታታት፣ የአፍሪካን የኢንዱስትሪ እና የፋይናንስ አቅም ለመጪዎቹ ትውልዶች ጥቅም ላይ ለማዋል” የሚያስችሉ “ተጨባጭ መፍትሔዎችን ማፋጠን” ሌላው ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ነው።
ሲዲ ዑል ታ ሥራቸውን በአቢጃን በይፋ በጀመሩበት መርሐ-ግብር “በክፍለ-አኅጉሮች፣ በፍላጎቶች እና በአተገባበር፣ በመንግሥት እና በግሉ ዘርፎች፣ በአንገብጋቢ ጉዳዮች እና በቢሮክራሲ መካከል ያለ ልዩነትን የሚያገናኝ ድልድይ ባንክ እንሆናለን” በማለት ቃል ገብተዋል። የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ በስድስት አስር ዓመታት ታሪኩ 250 ሚሊዮን ዶላር የነበረውን የመነሻ ካፒታል ወደ 318 ቢሊዮን ዶላር በማሳደግ በአፍሪካ ቀዳሚ የልማት ተቋም መሆን ችሏል።
የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመጠጥ ውኃ እና የትምህርት አገልግሎት ለማስፋፋት፣ የተመጣጠነ ምግብ እጦት እና በሽታዎችን ለማስወገድ እንዲሁም መሠረተ-ልማት ለመገንባት ለተወጠኑ በርካታ ፕሮጀክቶች ብድር ሲያቀርብ ቆይቷል። ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን የማበረታታት እና ድሕነትን የመቀነስ ዋንኛ ዓላማዎቹን ለማሳካት ግን ብዙ ይቀረዋል።