የአፍሪቃ ኅብረት የፍትሕ ጥያቄ ምላሽ ያገኝ ይሆን?
ረቡዕ፣ የካቲት 12 2017ሰሞነኛው የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ አኅጉሩ በቅኝ ግዛት እና በባሪያ ፍንገላ እና ንግድ ለደረሰበት ጉስቁልና የማካካሻ ፍትሕ ያስፈልጋል የሚል አቋም አራምዷል ። ለመሆኑ ይህ ጥያቄ እንዴት እና በምን ሁኔታ ምላሽ ያገኝ ይሆን? መሰል ጥያቄዎች የሚስተናገዱበት ዓለም አቀፍ የመዳኛ ተቋማትና መዋቅሮችስ ይኖሩ ይሆን? በዚህ ዙሪያ የአለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳይ ተንታኝ አነጋግረናል ።
የማካካሻ ፍትሕ ሐሳቡ በራሱ እንዴት ይታያል?
አፍሪቃውያን በባሪያ ንግድ እና በኋላም በቅኝ ግዛት ዘመን ደርሶባቸዋል ለሚባለው ታሪካዊ ወንጀል፣ ጉስቁልና እና በደል የማካካሻ ፍትሕ እንዲያገኙ የተጠየቀበት የሰሞኑ 38 ኛው የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ለተፈጸሙ ጥፋቶች በቂ እውቅና መስጠትንም የሚሻ ነው።
ከቅኝ ግዛት፣ ባርነት እና ሥርዓታዊ መድልዎ የሚመነጩ ታሪካዊ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ለመቅረፍ ያተኮሩ የተለያዩ ጅምሮችንም ያጠቃልላል ነው የተባለው ። በቅድሚያ ሀሳቡ በራሱ እንዴት ይታያል ስንል ስማቸውን ትተው ሀሳባቸውን የሚገልፁትን የአለም አቀፍ ሕግና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ ጠይቀናቸዋል ። «እንደ ሐሳብ በጣም መልካም ሀሳብ ነው። ግን ወደ መሬት መውረድ የሚችልበት ትጨባጭ ሁኔታ አለ ብየ አላስብም ።»
ጥያቄው ሊገጥመው የሚችለው ፈተና
የመሬት አያያዝን መልሶ ማቋቋም፣ የባህል ጥበቃ፣ እኩልነት፣ አድሎአዊነትን የሚያራምዱ ፖሊሲዎች መለወጥ ጥያቄው የሚያካትታቸው ናቸው ተብሏል። ይህንን ጥያቄ ለቀድሞ ቅኝ ገዥዎችና በዳዮች ማቅረቡ ያዋጣ ይሆን? «አዎ ያዋጣል ። ካሳ የማስገኘት ጥያቄዎችን ቢያነሳ ተገቢ ነው ።» የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የማካካሻ ጥያቄው የበጎ አድራጎት ወይም የገንዘብ ድጋፍ ፍለጋ እንዳልሆነና ይልቁንም የፍትሕ ጥሪ ስለመሆኑ ተናግረዋል ። ጉዳዩ አዲስ አጀንዳ አይደለም የሚሉት ተንታኙ አሁን የተለየ የሚሆነው በአፍሪካ ሕብረት ደረጃ መንቀሳቀሱ ነው ብለዋል። ሀሳቡ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት እርዳታ የማቋረጥ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ የመጣ ይሆን ወይ የሚለው ምላሽ ያሻዋል ባይ ናቸው ።
የፍትሐዊ ካሳ ጥያቄው እጅግ ውስብስብ መሆኑን የሚጠቅሱት ባለሙያው ካሳ ይከፍላሉ የሚባሉት ቀኝ ገዢዎች ሙሉ በሙሉ ስምምነት እንኳን ቢኖራቸው በአጭር ጊዜ መስተናገድ የሚችል አይደለም ብለዋል።
ከአፍሪቃ የተዘረፉ ቅርሶች
ከአፍሪቃ ተዘርፈው ተግዘው የተወሰዱ ልዩ ልዩ ቅርሶችን በመመለስ ሂደት የሚታየው ውጣ ውረድ እና ፈተና በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን በአስረጂ ያነሳሉ። የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ እንደተቋም በሂደት ምን እንደሚያከናውኑ ባይገልፁም የጥያቄውን ፍትሐዊነት ግን አጥብቀው ገልፀዋል።
«አፍሪቃ የሁለት ግዙፍ እና የተወሳሰቡ ኢፍትሀዊ ድርጊቶች ሰለባ መሆኗን አለም መቼም ሊዘነጋው አይገባም። በመጀመሪያ፣ የቅኝ ግዛት እንዲሁም የአትላንቲክ ውቅያኖስ የባሪያ ንግድ ማጋዝ ከፍተኛ ተጽእኖ ሥሩ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የተዘረጋ ሲሆን መራራ ፍሬው አፍሪካውያንን እና የአፍሪካ ተወላጆችን እስከ ዛሬ ድረስ እየጎዳ ይገኛል።
ከቅኝ ግዛት ቀንበር የመላቀቅ እውነት በራሱ ብቻ መፍትሔ አልነበረም። የፖለቲካ ነፃነት ሀገሮችን ከመዋቅራዊ ብዝበዛ እና ለበርካታ ዐሥርተ ዓመታት ከቆየ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ተቋማዊ ምዝበራዎች ነፃ አላደረገም ። የማሻሻያ የፍትህ ማዕቀፎችን ተግባራዊ ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው ።»
አፍሪቃ ኅብረት ጥያቄውን ከግብ ለማድረስ የሚያስችል የተደራጀ አቅም አለው ወይ? የሚለው ሌላኛው ፈታኝ ጉዳይ ነው ። በሚቀጥሉት ዓመታት እየተጠናከረ ሄዶ ውጤት ሊያመጣ ይችል ይሆናል የሚል ተስፋቸውን የገለፁት ባለሙያው ሕብረቱ ጥያቄውን ቢያነሳ ቅኝ ግዛትን እንደተዋጋ ተቋም የሚጠበቅም ነው የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል ።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ