የአፍሪቃ ኅብረት እንደ ስሙ አሕጉሩን በሕብረት ያስተሳስር ይሆን?
ሐሙስ፣ የካቲት 6 2017የቀድሞው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የአፍሪቃ አገራት በአካል ከነበሩበት ቅኝ ግዛት መላቀቅ እንዲችሉ ስለማገዙ ይታመናል ። ተቋሙ የአፍሪቃ ኅብረት ከተባለ ወዲህ ደግሞ አሕጉሩ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ያለው እንዲሆን የተጀመረው ጥረት በበጎ ሥራ ጅምር ይጠቀስለታል ። አብዛኛው ወጪው በውጪ ተቋማት እና ሀገራት የሚሸፈነው የአፍሪቃ ኅብረት ለ37 ጊዜ በተደረጉ የመሪዎች ጉባኤዎች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በአንድነት እና በፀጥታ ረገድ ምን ተጨባጭ ዕድገቶችን ዐሳይቷል?
ዶክተር ቆስጠንጦኖስ በርኸ ተስፋ የአፍሪቃ ኅብረት የፀረ ሙስና የአማካሪ ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ከዚህ በፊት ማገልገላቸው ነግረውናል ። በዋናነት ከአውሮጳ ኅብረት፣ ከዓለም ባንክ፣ ከቻይና እና ከሌሎችም በጀቱን የሚያገኘው ኅብረቱ፣ በአንድ ወቅት ደሞዝም መክፈል ተስኖት ተበድሮ መክፈሉን አስታውሰዋል። ሕብረቱ በአባል ሀገራቱ ሳይቀር ክብር የተነፈገው መሆኑንም ይገልጻሉ።
"የአፍሪቃ ሕብረት አባላት ሀገራቱም ክብር የላቸውም ለተቋሙ። መዋጯቸውን እምአያዋጡም"
አሕጉሩ በአካል ከነበረበት ቅኝ ግዛት መላቀቅ ችሏል የሚሉት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የአለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ አሁን በኃያላኑ የአውሮፓ ሀገራት በአካል ቅኝ የሚገዛ ሀገር አለመኖሩን በበጎ ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ ቀኝ ገዢዎች በእጅ አዙር በብድር፣ በገንዘብ ድጋፍ የአህጉሩን ሁኔታ የሚወስኑለት፣ የሚወስኑበት ጊዜ ላይ መሆናችንን አብራርተዋል። እንዲያም ሆኖ በፀጥታው ምክር ቤት ውክልና እንዲኖር የተጀመረውን ጥረት አፍሪካ ሕብረት ሊጠቀስ የሚችል ካለው በጎ ነገር ይጠቅሱታል።
ሕብረቱ በመሪዎችም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ሥራ የሚሠራ መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ አዲስ ሀሳብ ማምጣት የሚችል ስብስብ ባለመሆኑ የእስካሁኑም የወደፊቱም እንቅስቃሴው ዐይን ገላጭ እንዳልሆነና እንደማይሆን ይናገራሉ። ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ደግሞ የአሕጉሩ የጋራ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ርእዮተ አለም ወደ አንድነት እስካልመጣ ድረስ ሕብረቱን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተቋማትንም የማሳደጉ ኃላፊነት ፈተና አይለየውም።
የአፍሪቃ ኅብረት እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ከመስራት ይልቅ የተለጠጠ ዕቅድ በመያዝ የማሳካት አቅሙን የማያሳይ መሆኑ ያስወቅሰዋል። ሕብረቱ ባለፈው ዓመት ባደረገው የመሪዎች ጉባኤ ለሕብረቱ መመሥረት ቁልፍ ጉዳይ የነበረው ፖን አፍሪካኒዝም ስለመቀዛቀዙ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ድርቅና ድህነት ፣ የፀጥታ ችግር፣ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የሥርዓት ለውጦች መበራከት፣ የትብብር መጥፋት ቁልፍ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው ተለይተው ተጠቅሰው ነበር።
38 ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የፊታችን ቅዳሜ እና እሑድ አዲስ አበባ በሚገኘው መሥሪያ ቤቱ ይካሄዳል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ