የአፍሪቃ ባለ ሥልጣናት ለህክምና ክትትል ወደ ዉጭ ሃገር ለምን ይሄዳሉ?
ዓርብ፣ ነሐሴ 2 2017የአፍሪቃ ባለ ሥልጣናት ለህክምና ለምን ወደ ዉጭ ይጓዛሉ?
የቀድሞ የናይጀርያ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ቡሃሪ እና የዛምቢያዉ ፕሬዚዳንት ኢድጋር ሉንግዉ በውጭ ሀገር የህክምና ጣብያዎች ዉስጥ መሞታቸው የአፍሪቃ መሪዎች በራሳቸው አገራት የጤና ጥበቃ ስርዓት ላይ እምነት ማጣታቸዉን ያመላከተ እና ከፍተኛ ዉይይቶችን ያጫረ ሆንዋል። የሕክምና እርዳታን ለማግኘት የሚደረግ ዉሳኔ የግል ምርጫ ቢሆንም የአፍሪቃ መሪዎች በውጭ አገራት ሕክምና ለማግኘት የሚያደርጓቸው በርካታ አጋጣሚዎች የሃገራቸዉን የጤና ተቋማት ቸል ስለማለታቸዉ ያመላከተ ሆንዋል። መሪዎች ለአገራቸው ዜጎች ተገቢውን የጤና እንክብካቤ ለማረጋገጥ ሃላፊነት ያለባቸዉ መሆኑ እሙን ነዉ። የህክምና ባለሞያዎች ስራ ለማቆም ያስቀመጡት ቀነ ገደብ ተጠናቀቀ፤ ከዚያስ?
የናይጀሪያው ሙሃመድ ቡሃሪ እና የዛምቢያው ኤድጋር ሉንግዉ በውጭ የህክምና ተቋማት ሲታከሙ ቆይተዉ መሞታቸው፤ የአፍሪቃ መሪዎች በገዛ ሀገሮቻቸው ጤና አጠባበቅ ስርዓት ላይ ቸልተኝነት አሳይተዋል የሚለዉ ትችት እና ውንጀላ መሰማቱ አላቋረጠም። የናይጀሪያ የህዝብ ጤና ተመራማሪ የሆኑት ጃሚላ አቲኩ በናይጀርያ የጤና ጥበቃ መዋቅር አሳሳቢ መሆኑን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
«በአሁኑ ወቅት በናይጄሪያ ያለው የጤና እንክብካቤ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው ። በሀገሪቱ የጤና አገልግሎትን ማግኘት እንደ ቅንጦት ይቆጠራል። በርካታ ናይጄሪያውያን የጤና አገልግሎት ለማግኘት ከፍተኛ ወጭ ስላለዉ አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል ። በሌላ በኩል የጤና ተቋማት ብዙውን ጊዜ ንጹሕ ውኃ ስለሌላቸው የመሠረተ ልማት መዋቅሩን አስቸጋሪ ያደርጎታል። ይኸዉም በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ፣ መድሐኒቶች እጥረት ይከሰታል። አብዛኛውን ጊዜ የህክምና መሳሪያዎች ስራ ላይ አይዉሉም።» የተመራቂ ሐኪሞች ሥራ ማጣት
በጤና ጥበቃ የሚውለው ወጪ ዝቅተኛ ነው
ሌላው ምክንያት የውጭ እርዳታ ላይ ከመጠን በላይ ጥገኛ መሆን ነው የሚሉት ደግሞ የዚምባብዌ የጤና ጥበቃ ተሟጋች ቻሙኖርዋ ማሾኮ ናቸዉ። «ከ54 ሃገራት ውስጥ ከሀገራዊ ዓመታዊ በጀታቸዉ ከሰባት በመቶ ያላነሰ ለጤና የሚመድቡ 32 ሀገራት ይገኛሉ። ከ54 ቱ መካከል ፤ 32 ቱ ብቻ መሆናቸዉ አሳኝ መሆኑን ያሳየናል። ይህ ለጤና የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ በጣም አነስተኛ መሆኑን አመላካች ያደርገዋል። በጥቅሉ ሲታይ እነዚህን የገንዘብ ክፍተቶች ለሟሟላት ለጋሾች መጥተዉ ነዉ ክፍተቱን የሚያሟሉት።»
አፍሪቃ ለጤና ጥበቃ ከውጭ ሃገራት የምታገኘዉ የገንዘብ ድጋፍ በዋነኛነት ለዲፕሎማሲያዊ ጥቅም መሆኑን መረዳት ተስኗታል ያሉት ቻሙኖርዋ ማሾኮ ድጋፍ በመስጠት እየረዱን ያሉት ስለኛ ጤንነት ጉዳይ የሚሉ አይደሉም ሲሉ አክለዋል። የአፍሪቃ ሃገራት ከ60 ቢሊዮን ዶላር (52 ቢሊዮን ዩሮ) በላይ የጤና ድጋፍን ያገኛሉ። ይህ ግን ለአህጉሩ ከሚያስፈልገው ጠቅላላ የጤና መዋጮ ውስጥ ጥቂት ፍንካችን ብቻ የሚወክል ነው ። እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር በ2001 አቡጃ ላይ በተደነገገዉ መሰረት የአፍሪቃ ህብረት አባል ሃገራት የአፍሪቃን የጤና የገንዘብ ችግር ለመፍታት ከየዓመቱ አገራዊ በጀት 15% ለጤና እንክብካቤ ለመመደብ ቃል መግባታቸዉ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ከሃያ ዓመታት በኋላ ግቡን ማሳካት የቻሉት ሦስት ሃገራት ብቻ ናቸዉ። እነዚህም ሩዋንዳ፣ ቦትስዋና እና ኬፕ ቬርዴ ናቸው።
የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ከ30 በላይ የአፍሪቃ ሕብረት አባል ሃገራት ከ10% ያነሰ የዓመት በጀታቸዉን ለጤና አገልግሎት እንደመደቡ አመልክቷል። የተወሰኑ ሀገሮች ደግሞ ከ5-7% ብቻ መመደባቸዉን ነዉ ያስታወቁት። የናይጀሪያዉ ጤና ተመራማሪ ጃሚላ አቲኩ እንደተናገሩት ሀገራቸዉ ከዓመታዊ በጀቷ ከ 4-6% ስትመድብ መቆየትዋን ተናግረዋል። እንደ አቲኩ የናይጀርያ ፖለቲከኞች በዋናነት እንደ መንገዶች ባሉ ሌሎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው። በዚህም ይላሉ አቲኩ፤ የህክምና ዶክተሮች፤ የህክምና ባለሙያዎች እና የጤና ጥበቃ ሰራተኞች ብዙውን ጊዜ በቂ ክፍያ ባለማግኘታቸዉ ምክንያት በተደጋጋሚ የስራ ማቆም አድማ ይመታሉ። ለጤና የሚሆን በቂ የሕዝብ ድጋፍ ባለመመደቡ በብዙ የአፍሪቃ አገሮች ውስጥ ውጤት የሌለዉ የጤና ሥርዓት ማስከተሉም ተመልክቷል።
ደሴ ከተማ ደሞዝ ይጨመርልን አደባባይ የወጡ የህክምና ባለሞያዎች ታሰሩ
በውጭ አገራት የትኞቹ የህክምና አገልግሎቶች ይፈለጋሉ?
በአፍሪቃ ሥር ለሰደደ በሽታ ልዩ የሕክም ተቋማት ባመኖራቸው በርካታ አፍሪቃውያን ታካሚዎች ወደ ውጭ አገር ሄደው የሕክምና እርዳታ እንዲፈልጉ ዳርጓቸዋል። ከነዚህ ሕክምና ዘርፎች መካከል የነቀርሳ፣ የልብ፣ የነርቭ፣ የአጥንት ህክምና እና የአካል ክፍልን በሌላ መተካት፣እንዲሁም የመራብያ አካል ምርመራ እና የሕፃናት ሕክምና ይገኙበታል።
ከ300,000 የሚበልጡ አፍሪቃውያን በየዓመቱ የሕክምና እርዳታን ለማግኘት ወደ ሕንድ ይጓዛሉ። በየዓመቱ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይም ያወጣሉ ። ህንድ ከህክምና ቱሪዝም በየዓመቱ ከ6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደምታገኝ ተዘግቧል። የእስያይቷ አገር 'በህንድ ፈውስ' በተሰኘዉ መርሃግብሯ በጎርጎረሳዉያኑ 2026፤ በሕክምና ቱሪዝም 13 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ልታጘኝ እንደምትችል ተገምቷል። African Journal of Hospitality, Tourism and Leisure፤ የተባለዉ መጽሔት እንደዘገበዉ፤ ናይጄሪያውያን ለሕክምና ቱሪዝም በየዓመቱ 1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጡ ይገመታል። በየዓመቱ ወደ 5,000 የሚጠጉ ናይጄሪያውያን ለሕክምና እርዳታ አገሪቱን ለቅቀው የሚወጡ ሲሆን አብዛኞቹ የሚጓዙት ደግሞ ወደ ሕንድ ነዉ።
አንዳንድ የአፍሪቃ የጤና ባለሥልጣኖች ለየሀገሮቻቸዉ የጤና እንክብካቤን ለማጎልበት የተቻላቸውን ጥረት እያደረግን ነዉ ሲሉም ይከራከራሉ። የአፍሪቃ መንግስታት በአሁኑ ወቅት ለሌሎች ሀገራት የውጭ ምንዛሪ እየሰጠ ያለውን የጤና ዘርፍ አገልግሎት ወደራስ ለመመለስ ዘመናዊ የጤና ተቋማትን ሊገነቡ እንደሚገባ የጤና ባለሙያዎች ያሳስባሉ።
ፕሪቨሌጅ ሙስቫንሂሪ / አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ