የአፍሪቃ መሪዎች የተሳተፉበት የአፍሪቃ አሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 7 2015ኢትዮጵያን ጨምሮ የ49 ሃገራት መሪዎች የተሳተፉበትና ለሦስት ቀናት በዋሽንግተን ዲሲ የተካሄደው የአሜሪካ አፍሪቃ የመሪዎች ጉባዔ ትናንት ተጠናቋል። በስብሰባው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያኑ ጋር ያደረጉት ውይይት፣በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ታውቋል። ከዚህ በፊት በውጭ የሚገኙ ዜጎችን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያነሳቸው የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ባለፉት አራት ዓመታት የፖለቲካ፣የማኀበራዊና የሕግ ማሻሻያዎች ማከናወኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣አሁን እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችንም በዘላቂነት ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ከአሜሪካ የኢንቨስትመንት አባላት ጋር ጥሩ የሚባል ውይይት ማድረጋቸውን፣ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን እና እርሳቸው ታሪካዊ ያሉትን ማሻሻያዎች ተከትሎ፣በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ማበረታቻ መስጠታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣የአሜሪካን እና የኢትዮጵያን የንግድ ግንኙነት ማስፋፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአሜሪካ የንግድ ተወካይ አምባሳደር ካትሪን ታይ ጋር ጥሩ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአሜሪካ ጉብኝት አስመልክቶ ዶይቸ ቨለ ያነጋገራቸው፣በኢትዮጵያና ቡርኪናፋሶ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺን፣"ጠቃሚና አሜሪካም ከእርሳቸው ጋር መልካም ግንኙነት ለመመስረት እየጣረች መሆኑን የሚያሳይ"ሲሉ ገልጸውታል።
ይሁንና የሰሞኑ ስብሰባ በኢትዮጵያና ዩናይትድስቴትስ ግንኙነት ላይ ምን ዓይነት አንደምታ እንደሚኖረው ለመገመት አዳጋች መሆኑን፣እኚሁ የቀድሞ አምባሳደርና በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ይናገራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣የአፍሪቃና የአሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ የመጨረሻው ቀን፣ በመሪዎች መኻከል በሚደረጉ የከፍተኛ ደረጃ ውይይቶች የተወሰነ ነበር።
ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን፣አጀንዳ 2063 ባሉት የአፍሪቃ ህብረት የአህጉሪቱ ስትራቴጂካዊ ራዕይ ላይ ውይይት አካሂደውበታል።
ፕሬዚዳንቱ ውይይቱን ያጠቃለሉት፣ሩሲያ በዩክሬን ላይ በምታካሄደው ጦርነት ምክንያት፣የምግብ እና የማዳበሪያ ዋጋ መጨመር እና የዐለም የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል፣ለአፍሪቃ አጋሮቻቸው ወሳኝ በሆነው የምግብ ዋስትና እና የምግብ ስርዓት ጉዳይ ላይ በመነጋገር ነበር።
ለሦስት ቀናት የተካሄደው የአፍሪቃና አሜሪካ መሪዎች ጉባዔ፣ዩናይትድስቴትስ ከአፍሪቃ አጋሮቿ ጋር፣በጋራ መከባበርና ጥቅሞቿ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ለማጠናከር መሠረት የተጣለበት እንደሆነ ተመልክቷል።
አዲስ የዳይስጶራ ምክር ቤት እንደሚቋቋምና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችል ድጋፍ እለአፍሪቃ እንደምታደርግ የተገለጸበት ነበር።
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሚላ ሃሪስ፣ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን እና በርካታ የአሜሪካ ካቢኔ አባላት በቀጣዩ የጎርጎሮሳውያኑ አዲስ ዓመት አፍሪቃን ለመጎብኘትም አቅደዋል።
ታሪኩ ሃይሉ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ታምራት ዲንሳ