የአውሽቪትስ 80ኛ ዓመት ሲዘከር
ሰኞ፣ ጥር 19 2017ከጀርመን ናዚ የኦሽቪትዝ ማጎሪያ የጅምላ ፍጅት ሰለባዎች 80ኛ ዓመት መታሰቢያ ተከበረ። ከማጎሪያ ካምፑ በህይወት የተረፉ ጥቂት ሰዎች ፖላንድ ኦሽቪትዝ ተገኝተው ዕለቱን አስበው ውለዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከ19 40 እስከ 1945 በነበሩ አምስት ዓመታት ከዓለማችን አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ወንጀል በተፈጸመበት ወቅት ስድስት ሚሊዮን ያህል አይሁዳዉያን በቀጥታ እና በስልታዊ መንገድ ተገድለዋል። ሌሎች 100 ሺ ያህል አይሁድ ያልሆኑ ሰዎችም የሰለባው አካል ነበሩ ።
ከማጎሪያ ካምፑ በህይወት ከተረፉት እና በወቅቱ የ2 ዓመት ህጻን የነበሩት ኤቫ ኡምላውፍ በስፍራው በሰጡት አስተያየት በወቅቱ ናዚዎች አይሁዳውያንን የሰዎች ያህል አይቆጥሩም ነበር።
«ሰውን እንደ ሰው አይቆጥሩም ነበር። አይሁዶችን እንደ አይጥ ነበር የሚቆጥሯቸው።»
በኦሽቪትዝ 80ኛ ዓመት መታሰቢያ የእንግሊዙ ንጉስ ቻርለስ ፣ የጀርመኑ መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ እና የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጨምሮ የበርካታ ሃገራት መሪዎች ታድመዋል።
ሰዎች የሚገደሉበት የአውሽቪትዝ ካምፕ የራሱ የባቡር መስመር ነበረው።ከጀርመንም ሆነ ከሌላ የአውሮጳ ሀገር የሚነሱ ባቡሮች የመጨረሻ መድረሻ አውሽቪትዝ ነው።
ስፍራው ሰዎችን ለማጎርና ለመግደልም የተመረጠው በአውሮጳ ማዕከል የሚገኝና በቀላሉም በባቡር ሊደረስበት የሚችል በመሆኑ ነበር።
በዚህ ሁኔታ ከበርካታ የአውሮጳ ከተሞች አይሁዶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ አውሽቪትዝና ሌሎች ማጎሪያዎች በከብቶች ማመላለሻ ባቡሮችም ይወሰዱ ነበር። ባቡሮቹ ከማዕከላዊ እና ምሥራቅ አውሮጳ እንዲሁም ከፈረንሳይ፣ ቤልጅየም ኔዘርላንድስ፣ ጣሊያን፣ ሀንጋሪ እና ግሪክ እንዲሁም ከባልካን ሀገራት ከቡልጋሪያ እና ከመቆዶንያም ይመጡ ነበር።
ከመካካላቸው የሚገደሉት ተለይተው በጋዝ ታፍነው ወደሚሞቱበት ስፍራ ይወሰዳሉ። ቀሪዎቹ ደግሞ በመጀመሪያ በማጎሪያ ካምፑ ውስጥ በጉልበት ስራ ይሰማራሉ ።
አንዳንድ ከግድያው የተረፉ ሰዎች እንደሚያስታውሱት ወደ አውሽቪትስ የሚወስዱ በርካታ መጓጓዣዎች ነበሩ። እዚያ ለመገደል የተላኩት ሰዎች በጋዝ ታፍነው የሚገደሉበት ቦታ ስፍራ ሰውነታቸው መግባት ካልቻለ ተተኩሶባቸው ይገደላሉ። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ከነነፍሳቸው ወደ ማቃጠያ ጉድጎዶችም ይወረወሩ ነበር።
እነዚህን የመሳሰሉ ግፎች የተፈጸሙበት አውሽቪትዝ ስፍራውን ነጻ ያወጣው ሶቭየት ኅብረት ጦር በጎርጎሮሳዊው ጥር 27 ቀን 1945 ዓም ነበር ።
ነጻ አውጭዎቹ ከዩክሬን ከሩስያ እና ከቀድሞዋ የሶቭየት ሕብረት ግዛቶች የመጡ ወጣት ወታደሮች ነበሩ።
በዚህ ሁኔታ በዘር ርጭፍጨፋው በወቅቱ 6 ሚሊዮን አይሁዶች መገደላቸውን መረጃዎች ያሳሉ።
ልደት አበበ
ፀሀይ ጫኔ