የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ውሳኔዎች
ማክሰኞ፣ ግንቦት 20 2016የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት በብራስልስ ባካሄዱት የግንቦት ወር መደበኛ ስብሰባቸው አሁንም በዩክሬንና መካከለኛው ምስራቅ ላይ ትኩረት ሰጥተው ተወያይተዋል።
ስብሰባው በዩክሬን የሩሲያ ጥቃት ባየለበትና በተለይም በኻርካይቭ የገበያ ማዕከል ላይ የሮኬት ጥቃት በተፈጸመበት፤ በጋዛም የራፋ የስደተኞች ካምፕ በእስራኤል አውሮፕላኖች በተደበደበበት ማግስት የተካሄደ በመሆኑ የተለያዩ ስሜቶች የተንጸባረቁበትና ጠንካራ መልዕክቶችም የተላለፉበት እንደሆነ ተገልጿል።
የዩክሬን አጣዳፊ ጥያቄና የህብረቱ ምላሽ
በዩክሬን ጉዳይ አጣዳፊው ተግባር ዩክሬን ከሩሲያ ጥቃት ራሷን ልትከላከል የምትችልበትን መሳሪያ በብዛትና በአይነት ማግኘት በመሆኑ፤ በዚህ ላይ ሚንስትሮቹ ከዩክሬን የወጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድሚትሪ ኩሌባ ጋር የመከሩ መሆኑንና የተደረሰውንም ስምምነት የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተርና የስብሰባው መሪ ጆሴፕ ቦርየል በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት ገልጸዋል።
የአውሮፓ ህብረት የልማት እና ትብብር ሚኒስትሮች ስብሰባ ለዩክሬንና ፍልስጤም
“ ዩክሬን ራሷን ለመከላከል በተለይም የአየር መቃወሚያ (ፓትሪዮት) ልታገኝ በምትችልበትና ከምዕራብ አገሮች ያገኘቻቸውን የጦር መሳሪያዎችን በሩሲያ ምድር ላይ እንዳትጠቀም የተጣለባት እገዳ ሊነሳ ስለሚችልበት ሁኔታ ውይይት ተደርጓል” በማለት ለዩክሬን እንዲሰጡ የተወሰኑ የጦር እና የገንዘብ እርዳታዎች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ከአንዳንድ አባል አገሮች የሚነሱ ጥያቂዎችን በመቋቋም እንዲደርሱ እንደሚደረግና በሰኔ ወር በስዊዘርላንድ ሊካሄድ የታሰበው የሰላም ኮንፈረንስ እንዲሳካም ህብረቱ የበኩሉን እንዲያደርግ የተወሰነ መሆኑን ገልጸዋል።
የህብረቱና የአረብ አገሮች ሚኒስትሮች በጋዛ ላይ
በመካከለኛው ምስራቅ ላይ በነበረው ውይይት የአምስት አረብ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተካፋይ እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን ፤ይህም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ቦርየል ጠቅሰዋል።
“የአውሮፓ ህብረት እና የአምስት አረብ አገሮች ሚኒስትሮች፤ የአረብ ሊግ ዋና ጸሀፊ ጭምር ባንድ ላይ መምከራቸው ሁለቱ ወገኖች ለአካባቢው ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመፈለግና የሰብአዊ እርዳታው እንዲጨምር ለማድረግ የሚረዳ ነው” በማለት ሚኒስትሮቹ በነሱ በኩል ለዘላቂ ሰላም ይበጃል ያሉትን የሰላም ሀሳብ እንዳቀረቡና በተለይም የሁለት መንግስታት የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ሊሆን በሚችልበት ላይ የሚመክር የሰላም ኮንፈረንስ እንዲዘጋጅም ከስምምነት መድረሱን አስታውቀዋል።
የእስራኤል-ሀማስ ጥቃት ውግዘትና፤ የዓለማቀፉ ፍርድቤት ውሳኔ መከበር አስፈላጊነት
ጆሴፕ ቦርየል ቀደም ሲል ወደ ስብሰባው ከመግባታቸው በፊት እስራኤል በራፋህ የስደተኞች ካምፕ ላይ የፈጸመችውን የቦምብ ድብደብ በጥብቅ ያወገዙ ሲሆን፤ ከስብሰብው በኋላ በሰጡት መግለጫም ይህንኑ የእስራኤልን ድርጊትና ሃማስም በእስራኤል ላይ ያስወነጨፈውን የሮኬት ጥቃት አውግዘዋል።
“ጥቃቶቹ በጋዛ ሁሉም ቦታ አደገኛ መሆኑንና የጥቃት ተጋላጭ ይልሆነ ስፍራ አለመኖሩን የሚያረጋግጡ ናቸው። ጥቃቶቹ የተፈጸሙት የአለማቀፉ ፍርድቤት ጦርነቱ እንዲቆም ትዛዝ ባስተላለፈ ማግስት መሆኑ ደግሞ አሳዛኝ ነው” በማለት የፍርድቤቱ ውሳኔ መከበር ያለበት መሆኑን አሳስበዋል።
ሚኒስትሮቹ በስብሰባቸው በተለይ በመካከለኛ ምስራቅ ጉዳይ በሶስት ነጥቦች ተስማምተው ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን እና ጥሪ ማቅረባቸውንም ሚስተር ቦርየል አክለው አስታወቀዋል።
“አንደኛ የዓለማቀፉ ፍርድ ቤት ውሳኔና ትዕዛዝ ተግባራዊ እንዲሆን ዳግም ጠይቀናል። ሁለተኛ የፍልስጤም አስተዳደር ገንዘቡን እንዳያንቀሳቅስ በእስራኤል የተጣለው እገዳ እንዲነሳ አሳስበናል። ሶስተኛ የመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም መርጃ ድርጅትን በመወንጀል ስራውን እንዳይሰራ የሚደረገው ጥረት እንዲቆም ጠይቀናል” በማለት ሚኒስትሮቹ ባሁኑ ወቅት ከቀድሞዎቹ ጊዚያት ይበልጥ የጋራ አቋም ያራመዱ መሆኑንም አውስተዋል።
ተቃውሞ የጠነከረበት የእስራኤል ወደ ራፋ የመዝመት ዕቅድ
የህብረቱንና የእስራኤልን የጋራ የትብብርና ወዳጅነት ስምምነት የሚፈትሽ ስብሰብ እንዲጠራ ሲጠየቅ የነበረው ጥያቄ በዚህ ስብሰባ ተቀባይነት እንዳገኘ የተነገረ ሲሆን፤ ይህም በአንዳንድ ታዛቢዎች የህብረቱ አባል አገራት በእስራኤል ላይ አንድ አይነት አቋም ለማራመድ እየተቃረቡ እንደሆነ የሚሳይ ሆኖ ተወስዷል።
በተጨማሪም ሁለት የህብረቱ አገሮችና ኖርዌይ ከዛሬ ጀምሮ የፍልስጠኤምን ግዛትና መንግስት በይፋ እንደሚያውቁ ማስታወቃቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ስፔንና አየርላንድ ከዚህም ባለፈ እስራኤል የዓለማቀፉን ፍርድቤት ውሳኔ የማታከበር ከሆነ ማዕቀብ እዲጣልባት እያሳሰቡ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው።
ገበያው ንጉሴ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ