የአውሮጳ ሀገራት ወታደራዊ ወጪአቸውን ከፍ እንዲያደርጉ የገጠማቸው ጫናና ተግዳሮቶቹ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 3 2017የአውሮጳ ሀገራት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወታደራዊ ወጪአቸውን ከፍ አድርገዋል። በተለይም ከሩስያ ዩክሬን ጦርነት ወዲህ ፣ ወደፊት ከሩስያ በኩል ያሰጋናል ለሚሉት ጦርነት ራሳቸውን በማዘጋጀት ላይ ናቸው። ለዚህም የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪዎቻቸውን በስፋት እያንቀሳቀሱና የጦር መሣሪያም እያከማቹ ነው። የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል ሀገራት ወታደራዊ ወጪያቸውን ከአጠቃላዩ የሀገር ውስጥ ምርት ገቢያቸው ወደ 5 በመቶ ከፍ እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ ሲቀርብላቸው በነበረው ጥሪም ተስማምተዋል።
ምንም እንኳን የኔቶ አባል ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ዩናይትድ ስቴትስ በተደጋጋሚ ስታቀርብ በቆየችው በዚህ ግብ በጥቅሉ ቢስማሙም በአተገባበሩ ላይ ግን የአውሮጳ ሀገራት ሰፊ ልዩነት አላቸው። በተለይ ከዚህ ቀደም የተቀመጠውን 2 በመቶ የመከላከያ ወጪ ለማሟላት በመፍጨርጨር ላይ የነበሩት ሌሎች አባላት በዩናይትድ ስቴትስ ግፊት ወታደራዊ ወጪአቸው በአንዴ ወደ 5 በመቶ ከፍ እንዲል የተደረገባቸውን ጫና ለመቀበል ተቸግሯቸዋል። የኔቶ ዋና ፀሀፊ ማርክ ሩተ ግን ግቡን ማሳካት እንደምንችል እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።
« የተስማማንባቸውን የብቃት ግቦቻቻችን ስትመለከቱ እጅግ ከፍተኛ ጭማሪ ነው። እነዚህ አዲስ የብቃት ግቦች ናቸው እና ገንዘብ የለም ማለት አትችሉም። ስለዚህ አምስት በመቶ ላይ መድረስ እንደምንችልም ሙሉ እምነት አለኝ ። ወደ ዝርዝሩ ከገባን አሁንም መስራት አለብን።»
ሩተ በአዲሱ እቅድ ላይ ለሚያጉረመርሙት አባላት አግባቢ ያሉትን አተገባበር አቅርበዋል። ይኽውም አባላት ከአጠቃላዩ የሀገር ውስጥ ምርት 3.5 በመቶው ለወታደራዊ ወጪ በማድረግ የተቀረውን 1.5 በመቶ ደግሞ ከደኅንነት ጋር ለተያያዙ መሠረተ ልማቶችን ለመሳሰሉ ጉዳዮች እንዲያውሉ የሚያስችል ነው።
ይህን ግብ ለማሳካት ተጨማሪ ወጪ እንደሚያስፈልጋቸው ከገለጹት መካከል የኔዘርላንድስ መንግስት አንዱ ነው። ኔዘርላንድስ እንደምትለው የተቀመጠው ግብ ላይ ለመድረስ በየዓመቱ 19 ቢሊዮን ዩሮ ያስፈልጋታል። ጀርመንም እንዲሁ ተጨማሪ ገንዘብም ሆነ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልጋት ከተናገሩት መካከል ናት። የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ቦሪስ ፒስቶሪየስ ጀርመን የተባለው ግብ ላይ ለመድረስ አሁን አቅሙ የላትም፤የወታደሮቿንም ቁጥር ማሳደግ ይኖርባታል።
«ይህ ግምት ነው። ሆኖም አሁን በጦር ሠራዊታችን ካሉን ወታደሮች ከ50 ሺህ እስከ 60 ሺህ ተጨማሪ ወታደሮች ያስፈልገናል ብለን እናስባለን። ከዚሁ ጋር ታዲያ ይህ ለሚቀጥሉት ዓመታት ለሚያስፈልገን አዲስ ወታደራዊ አገልግሎት በቂ ይሆናል አይሆንም የሚለውን መጠየቅ አለብን። ያ ከአቅም ግንባታው ጋር የሚመሳሰል ነው ብለን እንጠብቃለን ። እናደግሜ መናገር የምችለው በአሁኑ ጊዜ ረቂቅ ስርዓት ምንም ፋይዳ የለውም ምክንያቱም በጦር ሰፈርም ሆነ በስልጠና ውስጥ አስፈላጊው አቅም የለንም። ለዚህም ነው እነዚህን አቅሞቻችንን ማሳደግ ያለብን ፤ እስከዚያ ድረስ ሊኖሩን የሚችሉት በጎ ፈቃደኞች ናቸው"
የኔቶ ዋና ፀፊ ሩተ በሚቀጥሉት ዓመታት ከሩስያ በኩል ሊደርስ ይችላል ለሚሉት ጥቃት የኔቶ አባል ሀገራት ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ በየአጋጣሚው ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ጥቃቱ በሚቀጥለው አምስትና ሰባት ዓመታት ውስጥ ሊደርስ ይችላል። የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ ሩተ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ከሩስያ በኩል ሊደርስ ይችላል ሳላሉት ጥቃትና ስለዝግጅቱ አስፈላጊነት በቅርቡ ለንደን ውስጥ የተናገሩትን ያስታውሳል።
ኔቶ ወደፊት ሊመጣ የሚችል ላለው ጦርነት እንዘጋጅ ማለቱን ሁሉም አባላት የሚቀበሉት አይደለም። ከመካከላቸው ስጋቱን የሚያጣጥሉም አልጠፉም። በአንዳንድ የኔቶ አባል ሀገራትም ተጨማሪው የመከላከያ ወጪ ላይ ህዝቡ ተቃውሞውን እየገለጸ ነው። ሩስያም ብትሆን ቅስቀሳ የምትለውን ይህን ማሳሰቢያ ውድቅ አድርጋለች።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ