የአረና ትግራይ አዲስ የጊዜያዊ አስተዳደር ጥሪ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 27 2017ወቅታዊ የትግራይ፣ ኢትዮጵያ እና ቀጠናዊ ሁኔታዎች የዳሰሳ ስብሰባ ካደረገ በኋላ መግለጫ እንዳወጣ የገለፀው በትግራይ ክልል በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ እንዳለው ከጦርነቱ በኋላ በትግራይ የተቋቋሙ ጊዜያዊ አስተዳደሮች ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ባገለለ መልኩ በህወሓት ብቻ የተመሰረቱ መሆናቸውን ተከትሎ፥ ቅቡልነት ማጣታቸውን እና መውደቃቸውን ገልጿል። በህወሓት ላይ የሰላ ትችት የሰነዘረው ዓረና ትግራይ፥የህወሓት ቡድን «ከሻዕብያ እና የአማራ ታጣቂዎች» ጋር ግንኙነት እያደረገ መሆኑን በማንሳት፥ ከዚህ ጥፋት ሊያስከትል የሚችል ያለው ግንኙነት ራሱን እንዲያገልልም ጥሪ አቅርቧል።
የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረ ሥላሴ በትግራይ አዲስ፣ አቃፊ እና አሳታፊ የሽግግር መንግሥት በአስቸኳይ መመስረት መቻል አለበት ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል የእርስበርስ ውጊያ እንዳያስከትል ስጋት መኖሩ፣ ምልክቶችም እየተስተዋሉ መሆኑን አመልክቷል።
የዓረና ትግራይ መግለጫ
ዓረና በመግለጫው በትግራይ ክልል በሕገወጥ መንገድ የሚደረግ ማዕድናት የማውጣት ሥራ መበራከቱን ያነሳ ሲሆን፥ ወርቅ ለማውጣት ጥቅም ላይ የሚውሉ ኬሚካሎች በሰው እና አካባቢ ላይ የከፋ ጉዳት እያስከተሉ መሆኑን ባደረገው ጥናት ማረጋገጡንም አስታውቋል። በዚህ ሕገወጥ ተግባር ውስጥም የትግራይ ጀነራሎች፣ ፖለቲካዊ መሪዎች እንዲሁም ባለሀብቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ ሲል ከሷል።
ከህወሓት ጋር የወገኑ ወታደራዊ መሪዎች ትጥቃቸውን ፈትተው፣ ወደ ፖለቲካ ይግቡ፥ ይህ ካልሆነ ግን ትግራይን ወደከፋ ሁኔታ እንደሚመራት የዓረናው ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረ ሥላሴ ጨምረው ገልፀዋል።
ከተፈናቃዮች ጋር በተገናኘ ህወሓት በትግራይ ክልል የተለያዩ መጠልያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደየቀያቸው እንዳይመለሱ እንቅፋት ሆኖ እንዳለ ያነሳ ሲሆን የፌደራል መንግሥቱም እግር እየጎተተ ነው ሲል ወቅሷል። ከዚህ በተጨማሪ ወቅታዊ የትግራይን ፖለቲካዊ ሁኔታ አስመልክቶ መግለጫ ያሰራጨው ሌላው ተቃዋሚ ፓርቲ ሣልሳይ ወያነ ትግራይ፥ በትግራይ ያለውን አደገኛ ሁኔታ ለመቀየር «ብሔራዊ ጉባኤ» ይጠራ ብሏል።
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ