የዶናልድ ትራምፕ ታሪፍን እንደ መሣሪያ የመጠቀም ሥልት የዓለም የንግድ ሥርዓትን አስግቷል
ረቡዕ፣ ጥር 28 2017ጀርመን እና ፈረንሳይን ጨምሮ የአውሮፓ ኅብረት ሀገራት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ ለሚጥሉት ታሪፍ ራሳቸውን እያዘጋጁ ነው። ፕሬዝዳንቱ ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ ጀምሮ በካናዳ፣ ሜክሲኮ እና ቻይና ላይ የጣሏቸው የታሪፍ ጭማሪዎች በዓለም ንግድ ላይ አሉታዊ ጫና እንዳያሳድሩ አስግቷል።
የታሪፍ ውዝግብ ሲቀሰቀስ ዓለም አቀፍ የአክሲዮን ገበያዎች ዋዥቀዋል፤ ዶላር እንደ ዩሮ እና ፓውንድ ከመሳሰሉ መገበያያ ገንዘቦች አንጻር ያለው የምንዛሪ ተመን አድጓል። የነዳጅ የመሸጫ ዋጋም ጨምሯል። ትራምፕ ከምረጡኝ ዘመቻቸው ጀምሮ በአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ላይ ታሪፍ ሊጥሉ እንደሚችሉ በግልጽ ሲናገሩ ነበር።
“መኪናዎቻችንን አይገዙም፤ የግብርና ውጤቶቻችንን አይገዙም። ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የ350 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ጉድለት አለን” ያሉት ትራምፕ “እጅግ በመጥፎ ሁኔታ ነው የሚያስተናግዱን፤ ስለዚህ ታሪፍ ይጣልባቸዋል” የሚል ዛቻቸው በተደጋጋሚ የተደመጠ ነው።
በእርግጥም በሸቀጥ በተለይም በተሽከርካሪዎች ንግድ ረገድ አሜሪካ በአውሮፓ ገበያ ከምትሸጠው ይልቅ ከኅብረቱ የምትሸምተው የላቀ ነው። በአውሮፓ ኮሚሽን መረጃ መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2023 የአሜሪካ የሸቀጥ ንግድ ጉድለት 155.8 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 161.6 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር። በአገልግሎቶች ረገድ በአንጻሩ አሜሪካ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የነገደችው 104 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ያለው ነው።
የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት በአሜሪካ ገበያ ከሚሸጡት 30 በመቶው የጀርመን ድርሻ ነው። ጣልያን በ13 በመቶ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በጎርጎሮሳዊው 2024 ሦስተኛ ሩብ ዓመት የአውሮፓ ኅብረት 46 በመቶውን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ (LNG) እና 15 በመቶ ነዳጅ የሸመተው ከአሜሪካ ነው።
እንዲያም ሆኖ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አውሮፓ የበለጠ ከአሜሪካ እንዲገዛ ይፈልጋሉ። ይኸን ፍላጎታቸውን ለማሳካት ታሪፍን እንደ መሣሪያ መጠቀማቸው እንደማይቀር የተገነዘቡት የኅብረቱ አባል ሀገራት ተመሣሣይ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
የጀርመን መራኄ-መንግሥት ኦላፍ ሾልስ “አሜሪካ እና አውሮፓ በመካከላቸው ካለው የሸቀጦች እና የአገልግሎቶች የንግድ ልውውጥ ተጠቃሚ ናቸው። የጉምሩክ ፖሊሲ ይኸን አስቸጋሪ ካደረገው ለአሜሪካ እና ለአውሮፓ መጥፎ ይሆናል” ሲሉ ተደምጠዋል። ይሁንና አሜሪካ ታሪፍ ከጣለች ኅብረቱ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስድ “በጉምሩክ ፖሊሲ ለመጣብን በጉምሩክ ፖሊሲ ምላሽ እንሰጣለን” በማለት በአጽንዖት ተናግረዋል።
የአውሮፓ ኅብረት በጉዳዩ ላይ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገር እንደሚፈልግ የኅብረቱ የበይነ-ተቋማት ግንኙነት ኮሚሽነር ማሮስ ሴፍኮቪች ተናግረዋል። የኅብረቱ ሹማምንት ግን እስካሁን ከትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣናት ጋር እንዳሻቸው መገናኘት አልተሳካላቸውም።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን በበኩላቸው በሁለቱ አጋሮች መካከል ያሉ ቅሬታዎችን ለመፍታት የአውሮፓ ኅብረት ለጠንካራ ድርድር ዝግጁ እንደሆነ ቢያረጋግጡም ትራምፕ ታሪፍ ከጣሉ ተመሳሳይ ምላሽ ሊጠብቁ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
“ፍትኃዊ ባልሆነ መንገድ ወይም በዘፈቀደ ዒላማ ከተደረግን የአውሮፓ ኅብረት ጠንካራ ምላሽ ይሰጣል” ያሉት ፎን ዴር ላየን “የታሪፍ ክፍያዎች የቢዝነስ ወጪዎችን ያንራሉ። ሠራተኞችን እና ሸማቾችን ይጎዳሉ፣ አላስፈላጊ ኤኮኖሚያዊ መስተጓጎል ይፈጥራሉ፣ የዋጋ ንረትንም ይጨምራሉ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
“ዶናልድ ትራምፕ ማንን እንደሚያዳምጡ በጭራሽ ማወቅ አይቻልም” የሚሉት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ኮን ደ ሉስ “ትልልቆቹ ሀገሮች ላይ” ሊያነጣጥሩ እንደሚችሉ እምነት አላቸው። “ምክንያቱም በእነዚህ ሀገራት ትልቅ ድንጋጤ መፍጠር ከቻሉ፤ የተቀረው የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት እንደሚከተሉ ያውቃሉ። ትልልቅ እና በጣም ጠቃሚዎቹ ሀገራት ፈረንሳይ እና ጀርመን ናቸው። ስለዚህ ለእነዚህ ሀገራት ጠቃሚ የሆኑ ዘርፎች ዒላማ ይሆናሉ” ሲሉ አብራርተዋል።
ታሪፍ ሀገራት ከውጪ በሚሸምቷቸው ሸቀጦች እና አገልግሎቶች ላይ የሚጣል ግብር ነው። የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን ከውድድር ለመጠበቅ እና የመንግሥታትን ገቢ ለማሳደግ እንደ መሣሪያ ሊያገለግል ይችላል።
ዶናልድ ትራምፕ የሚጥሉትን ታሪፍ አምራች ሀገሮች ወይም ኩባንያዎች ይከፍላሉ የሚል አቋም ቢኖራቸውም በተጨባጭ ግን ከፋዮቹ ሸቀጦቹን ከዓለም ገበያ ሸምተው ወደ አሜሪካ የሚያስገቡ ኩባንያዎች ናቸው። ኩባንያዎቹ ከተሳካላቸው የሚከፍሉትን ተጨማሪ ታሪፍ ወደ ደንበኞቻቸውን ለማሸጋገር ይሞክራሉ። በዚም ምክንያት የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች እንደሚሉት ታሪፍ የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል።
ዶናልድ ትራምፕ ታሪፍን እንደ መሣሪያ የሚጠቀሙት የንግድ ሚዛን ጉድለትን ለማረቅ ብቻ አይደለም። ፕሬዝደንቱ ፖለቲካዊ አጀንዳዎቻቸውን ለማስፈጸም እና ሌሎች መንግሥታትን ለማስገደድ ተግባራዊ እያደረጉት ነው።
ቡና አምራቿ ኮሎምቢያ ወደ አሜሪካ በምትልካቸው ሁሉም ሸቀጦች ላይ 25 በመቶ ታሪፍ በትራምፕ አስተዳደር ሊጣልባት የነበረው ሕገ-ወጥ የተባሉ ስደተኞች የጫኑ የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች አልቀበልም በማለቷ ነበር።
ስደተኞችን እና ፌንታሊን የተባለውን ጨምሮ ወደ አሜሪካ የሚገቡ አደንዛዥ ዕጾችን ሜክሲኮ እና ካናዳ እንዲቆጣጠሩ ለመጫን ትራምፕ በሁለቱ ሀገራት ላይ 25 በመቶ ታሪፍ የመጣል ዕቅድ ነበራቸው።
ሜክሲኮም ሆነች ካናዳ የትራምፕን ውሳኔ በመቃወም በአጸፋው ከአሜሪካ በሚሸምቱት ሸቀጥ ላይ ታሪፍ ለመጣል ቢዝቱም የኋላ ኋላ ግን አፈግፍገዋል። ሜክሲኮ ከአሜሪካ በምትዋሰንበት ድንበር 10,00 ወታደሮች ለማሥፈር ተስማምታለች።
ዶናልድ ትራምፕ ከሜክሲኮ እና ካናዳ መሪዎች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በሁለቱ የአሜሪካ ጎረቤቶች ላይ ሊጣል የነበረው 25 በመቶ ታሪፍ ለ30 ቀናት እንዲቆም ተስማምተዋል።
ትራምፕ ከቻይና ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የጣሉት 10 በመቶ ታሪፍ በአንጻሩ ትላንት ማክሰኞ ሥራ ላይ ውሏል። ለቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ አስፈላጊ የሆኑ እና አንገብጋቢ የሚባሉ የቻይና ማዕድናት ወደ አሜሪካ እንዳይላኩ ገደብ ተጥሏል። ነገር ግን የቻይና የበቀል እርምጃ እስከ መጪው የካቲት 4 ቀን 2017 ድረስ ሥራ ላይ አይውልም።
በፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ አራት የሥልጣን ዓመታት እንደተከሰተው ሁሉ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ከሚፈጠር “የንግድ ጦርነት አሸናፊ እንደማይኖር” የገለጹት በተባበሩት መንግሥታት የቻይና ቋሚ መልዕክተኛ ፉ ኮንግ ሀገራቸው ጉዳዩን ወደ ዓለም የንግድ ድርጅት እንደትወስድ አስታውቀዋል።
“ይኸን ተገቢ ያልሆነ የታሪፍ ጭማሪ በጥብቅ እንቃወማለን” ያሉት ፉ ኮንግ “ውሳኔው የዓለም የንግድ ድርጅት ሕግጋትን የሚጥስ እንደሆነ እናምናለን። በዚህም ምክንያት ቻይና ለዓለም ንግድ ድርጅት ክስ ታቅርባለች” ሲሉ ተናግረዋል።
ቻይናም ሆነች አሜሪካ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተፈጠረው ውዝግብ በንግግር እንዲፈታ ፍላጎት እንዳላቸው ጥቆm ሰጥተዋል። በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው አቻቸው ሺ ዢንፒንግ ጋር ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌላ የታሪፍ ውጥረት እየፈጠሩ የሚገኙ ሀገራት እንዲረጋጉ፤ አደብም እንዲገዙ ዛሬ ረቡዕ አሳስበዋል። ሀገራት ኤኮኖሚያቸውን ከውድድር ለመጠበቅ በተለያዩ ስልቶች ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የጠቀሱት ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌላ እንዲያም ሆኖ የገጠሙትን ተግዳሮቶች በመቋቋም ዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ 30.4 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን ገልጸዋል።
“አብዛኞቹ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ሀገራት ነጻ፣ ክፍት፣ የተረጋጋ እና ተገማች ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት የሰዎችን አኗኗር በማሻሻል አስደናቂ ለውጥ እንዳመጣ እውቅና ይሰጣሉ” ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌላ ያሉት “ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ከድሕነት አውጥቷል” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ይህን አዎንታዊ ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓትን የበለጠ ክፍት፣ ነጻ እና ተገማች የማድረግ ፍላጎት አለ። የንግድ ፖሊሲ እርግጠኝነት ማጣት እና የገበያ መበጣጠስ ዓለምን በመጥፎ መንገድ እንዳይጎዳ እጅግ መጠንቀቅ አለብን” የሚል ምክር የለገሱት ዋና ዳይሬክተሯ “እርምጃ እና የአጸፋ ምላሽ ለመውሰድ አንቸኩል። ምክንያቱም እንዲህ አይነቱ አካሔድ አይሰራም። ስለዚህ ጸንተን እንጠብቅ፤ እንረጋጋ” ሲሉ ተናግረዋል።
የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌላ የሰጡትን “እንረጋጋ” ማሳሰቢያ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ይሰሙ ከሆነ በመጪዎቹ ቀናት የሚታይ ይሆናል። ቻይና በዓለም የንግድ ድርጅት በኩል የምታቀርበው ቅሬታ በትራምፕ ታሪፍ ምክንያት የተፈጠረውን ውጥረት መፍታት የሚችል አይመስልም። ለዚህ ደግሞ ትራምፕ በዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ያላቸው አቋም የራሱ ሚና ይኖረዋል።
ትራምፕ ትላንት ማክሰኞ አሜሪካን ከተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሚያስወጣ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል። ትዕዛዛቸው አሜሪካ ለተባበሩት መንግሥታት የምትሰጠው የገንዘብ ድጎማ እንዲገመገም የሚያደርግ ጭምር ነው።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ