የአሜሪካ የጉዞ እገዳ ዕቅድና አንደምታው
ሐሙስ፣ ሰኔ 12 2017የትራምፕ አስተዳደር የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ናቸው ባላቸው 12 አገሮች ላይ ወደ አሜሪካ የሚደረጉ ጉዞዎችን ሙሉ በሙሉ፣ እንዲሁም በሰባት አገራት ዜጎች ላይ ከፊል የጉዞ እገዳን በቅርቡ ጥሏል።
አስተዳደሩ ይህን ካደረገ ብዙም ውሎ ሳያድር፣ኢትዮጵያን ጨምሮ የ36 ሃገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ሐሳብ እንዳለው፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተመለከቱት፣የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሰነድ አመልክቷል።
ዶይቸ ቨለ ያነጋራቸው በቨርጂኒያ ግዛት የህግ ባለሙያ ዶክተር ፍጹም አቻምየለህ፣ይህ የትራምፕ አስተዳደር ዕቅድ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ፣ አፈጻጸሙ የሚመለከታቸው አካላት እነማን እንደሚሆኑ ያብራራሉ።
"የእነዚህን ሃገራት ፓስፖርት የያዙ ሰዎች፣ወደዚህ ሃገር እንዳይገቡ ሊያግድ ይችላል፤ሙሉ በሙሉ እገዳ ከሆነ። በከፊል እገዳ ከሆነ ተማሪዎች፣ቱሪስቶች፣ለስብሰባ የሚመጡ እንደዛ ዓይነት ሰዎች ይታገዳሉ ማለት ነው።ሁለተኛው እንግዲህ ዓይነት ዕገዳ በከፊል ከሆነ ባለስልጣናትና አንዳንድ ሰዎችን ብቻ የሚያግድ ይሆናል።"
የእግዱ ምክንያቶች
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሰነድ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ዜጎቻቸው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ሊደረጉ በታሰቡ ሃገራት ላይ አሳሳቢ ሲል የተለያዩ ምክንያቶችን ለይቶ አስቀምጧል።
ከእነዚህም መኻከል ሃገራቱ የዜጎችን ማንነት ለመለየት የሚያስችል አስተማማኝ ሰነዶችን ለማቅረብ ብቃት ማነስና ተባባሪ አለመሆን እንዲሁም የፓስፖርታቸው ደህንነት አጠያያቂ መሆን ተጠቅሷል።
አንዳንድ ሃገራት ደግሞ ከአሜሪካ እንዲወጡ የታዘዙ ዜጎቻቸውን ለመቀበል ተባባሪ አይደሉም ተብለዋል።
ሌሎቹ ደግሞ ቪዛ አግኝተው ወደ አሜሪካ የገቡ ዜጎቻቸው ለመቆየት ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ መቆየታቸውን ለዕገዳው አስፈላጊነት እንደሰበብ ተዘርዝሯል።
የተፈጻሚነቱ ጥያቄዎች
ሃገራቱ ዕገዳው ተግባራዊ እንዳይሆንባቸው፣ በስድሳ ቀናት ውስጥ ማስተካከያዎችን እንዲያደርጉ ሰነዱ የጊዜ ገደብን ማስቀምጧል። የህግ ባለሙያው ግን፣ በሁለት ወራት ውስጥ ይህን ሁሉ ማድረግ፣ ለአገራቱ አስቸጋሪ ይሆነባቸዋል ይላሉ።
"የትኞቹ ሃገራት ናቸው ይህንን በ60 ቀናት ሊያርሙ የሚችሉት የሚለው በጣም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ስር ነቀል የሆነ ለውጥ ማምጣት ይኖርባቸዋል ማለት ነው። የዶክመንት አሰጣጥ ዘመናዊ የማድረግ ነገር በስድሳ ቀናት ውስጥ የሚካሄድ አይደለም፤ በጣም ብዙ ዓመታት የሚፈጁ ናቸው።እዚህ መጥተው የሚቀሩ ዜጎች ይበዛሉ የሚለው ይህ እንግዲህ እያንዳንዱ አገር ካለው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ችግር አንፃር እዚህ መጥተው የሚቀሩ ሰዎች ሊበዛ ይችላል በስድሳ ቀናት ውስጥ መቀየር አይቻልም።"
ጉዳዮቹ በደንብ የታሰበባቸው አይመስልም የሚሉት ዶክተር ፍጹም፣ ተግባራዊ ቢደረጉ እንኳን ህጋዊ ተግዳሮቶች ሊገጥማቸው እንደሚችል ጠቁመዋል።
"ምክንያቱም፣ከዚህ በፊት የነበረው የዛሬ አምስት ዓመት የወጣውና የሙስሊም ሃገሮች ዜጎች አናስገባም የሚለው ዕቅድ፣ ጨቋኝና በትክክል ያልታሰበበት፣ የአሜሪካ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅምን ያላገናዘበ፣ ብሎም እንደዚህ ማድረጉ የአሜሪካን ደህንነት መጠበቁን ማሳየት አልቻለም ተብሎ ነው እንግዲህ ያ ውሳኔ በፍርድ ቤት ተሽሮ የነበረው እና እነዚህንም ውሳኔዎች ፍርድ ቤት የሚሞገቱ ሰዎች ይኖራሉ ብዬ ነው የማስበው።አንድ ጊዜ ይሄ ነገር ወደ ስራ እንዲገባ ከተደረገ።"
ኢትዮጵያውያን ሊያውቋቸው የሚገቡ
ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ዜጎቻቸው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ሊደረጉ እንደሚችሉ ከተጠቀሱ 36 ሃገራት መኻከል 25 ከአፍሪቃ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያዊያም አንዷ ናት። ኢትዮጵያውያን ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሊያውቋቸው የሚገቡ ጉዳዮች ምንድን ናቸው ስንል ጠይቀናቸው፣ዶክተር ፍጹም እንደሚከተለው መልሰዋል።
"በትክክል ማምጣት የሚፈልግ ሰው በቶሎ ማስገባቱ ጥሩ ነው።ጠበቃ ካለው ከጠበቃው ጋር እየተባበረ ዶክመንቶቹን በትክክል እንዲያስገባ እመክራለሁ፤ ሌላው የምመክረው ቪዛ ተሰጥቷቸው ሃገር ውስጥ ያሉ ሰዎች፣በተለይ የኢሚግራንት ቪዛ ይዘው አገር ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ ይህ ፖሊሲ ከመተግበሩ በፊት እንዲመጡ እመክራለሁ።"ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ