የአሜሪካ አዲሱ የስደተኞች ህግ እና ኢትዮጵያዉያን
ሐሙስ፣ ጥር 22 2017
የዶናልድ ትራምፕን ዳግም ወደ ፕሬዝዳንትነት መመለስን ተከትሎ የወጡ የስደተኞችን ጉዳይ የተመለከቱ ት ዕዛዞችና ህጎች ተፈጻሚ እየሆኑ ነው። ነው። በተለይ በአሜሪካ ስር ዓት ውስጥ ያልተመዘገቡ ስደተኞችን የማፈስና ወደ ሃገራቸው የመመለስ ዘመቻው በርካታ ኢትዮጵያውያንን ለጭንቀት መዳረጉንና በፍርሃት እቤታቸው እንዲቀመጡ እንዳስገደዳቸው ታውቋል። ይሂው አፈሳና አዲስ ህግ ነዋሪወቹን ብቻ ሳይሆን የንግድ ተቋማትንና ግብረሰናይ ድርጅቶች ላይም ጫና መፍጠሩ አልቀረም። ይሄንኑ የህግ ትርጓሜና አፈጻጸም ብሎም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኢትዮጵያውያን ማወቅ ያለባቸውን በተመለከተ የዋሽንግተኑ ዘጋብያችን አበበ ፈለቀ ቀጣዩን ዘገባ ልኮልናል።
በዲሲና በአካባቢዋም ሆነ በሌሎች የአሜሪካ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም የመኖርያ ፍቃድ የሌላቸውና ህጋዊ ሂደት ውስጥ ያሉት ጭምር በሰፊው እየተወሰደ ባለው የስደተኞች አፈሳና መመለስ ጋ ተያይዞ በቂ መረጃ አለማግኘት፣ ጭንቀትና ስጋት ውስጥ ወድቀዋል። የተለያዩ የኢትዮጵያ የንግድ ተቋማት፣ ሬስቶራንቶች፣ ገበያወች ውስጥ የሚሰሩትም በፍርሃት በመዋጣቸው ከቤት አለመውጣትን እንደመረጡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በዲሲና አካባቢዋ ያሉ የሃበሻ ንግድ ቤት ባለቤት ተናግረዋል።
ይሄንኑ ችግር አስመልክቶ ያነጋገርኩትና ከህጉ ጋር በተያያዘ ባለበት ስጋት ሳብያ ድምጹ እንዳይቀረጽ ስሙም እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ ወጣት የስራ ፍቃድ እንዳለው ጠቁሞ፣ ኡበር በመንዳት የሚተዳደር ቢሆንም፣ ድንገት ከመኪና አደጋ ጋ ቢገጥመውና በፖሊስ እጅ ቢወድቅ ለዚሁ የመታፈስ አደጋ እጋለጣለሁ ብሎ በመፍራት መኪናውን አቁሞ እቤቱ ቁጭ ማለቱን ነግሮኛል። ሌላዋ ኢትዮጵያዊት በእጮኛ ቪዛ የመጣች፣ የተጠየቀውን የጋብቻ ስነስራዓት ፈጽማ፣ የመኖርያና የስራ ፈቃድ ማመልከቻም ያስገባች ቢሆንም ፈቃዶቹ ገና ስላልመጡ “ቤት ውስጥ ዘግቼ ነው የምውለው” ብላለች። እንዲህ ያሉ የጭንቀት የጥበት ሁነቶች በሰፊው እየተስተዋሉ ነው። ያም ሆኖ ይሄው የመያዝና መመለስ ዝመቻ ህጋዊ የሆን ሂደት ውስጥ የገቡ ስደተኞችን እንደማይመለከት የህግ ባለሞያና ጠበቃው ዶ/ር ፍጹም አቻሜለህ ጠቁመዋል። ይሄው ህጋዊ ማዕቀፍ በቤተሰብ ቅልቅልም ሆነ በእጮኛ ቪዛ መጥተው ህጉ በሚፈልገው መንገድ የሚጠበቅባቸውን ማመልከቻ ያስገቡ ሰወችንም ይመለከታል።
በሌላ መልኩ በአሜሪካ የህግ ስርዓት ውስጥ ያልተመዘገቡ፣ በህጋዊ መንገድ ለመቆየት የሚያበቃ መረጃና ፍቃድ የሌላቸው እንዲሁም በየትኛውም የስደተኝነት ወይም የጥገኝነት ማመልከቻ ሂደት ውስጥ የሌሉ ሰወች ሊያዙም ወደሃገር ሊመለሱም ይችላሉ። እንዲሁም የጥገኝነት ማመልከቻቸው ውድቅ ተደርጎ በስደተኞች ፍርድ ቤት ሃገር እንዲለቁ የታዘዙም የዚሁ ዘመቻ ኢላማወች ናቸው። ሌላው የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ትኩረት ለወትሮው በቀላሉ የሚታዩ ወንጀሎችን እንደ መያዣ መጠቀምን ነው። በዚህም መሰረት በየትኛውም የጥገኝነት ማመልከቻ ሂደት ውስጥ ያሉ፣ እንዲሁም የስራ፣ የትምህርትም ሆነ የጉብኝት ቪዛ ያላቸው ቢሆኑም በወንጀል የተከሰሱ፣ የተፈረደባቸው፣ የተጠረጠሩ ወይም የወንጀል ታሪክ ያላቸው ከሆነ ለዚህ የአፈሳ ተዕዛዝ የተጋለጡ ናቸው።
የአሜሪካ የስደተኞች ጉዳይ ሃይሎች ከዚህ ቀደም አፈሳ ተደርጎባቸው በማያውቁ ቦታውች ጭምር፣ በገበያወች፣ በቤተ እምነቶች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሆስፒታሎችና በመኖርያ ቤቶች ጭምር የተቀናጀ የአፈሳ ዘመቻ እያደረጉ መሆኑን ዶ/ር ፍጹም ገልጸው እትዮጵያውያን መውሰድ ስለሚገባቸው እርምጃወችና ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄወች ይህን ብለዋል። ምንም አይነት ወረቀት እና ህጋዊ እውቅና የሌላቸው ሰወች ግን ይሄ ሁኔታ እስኪሰክንና ነገሮች መስመር እስኪይዙ ድረስ ከቢት እንዳይወጡ የመከሩት ዶ/ር ፍጹም በዚህ ሁኔታ ውስጥ የአፈሳ ፖሊሶች ቢመጡ ያለመተባበር መብት እንዳለም ጠቁመዋል። የፕሬዝዳንት ትራምፕ አዳዲስ መመሪያወች ጫና የፈጠሩት በስደተኞች ላይ ብቻ አይደለም። ። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች የመቀበል መርሃ ግብር ለ90 ቀናት እንዲታገድ በመወሰናቸው፣ ከመላው አለም ለሚመጡ በርካታ ስደተኞች የማቋቋም አገልግሎት በመስጠት ከአራት አስርተ አመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ልማት ምክር ቤትም ስራ መስተጓጎሉን የተቋሙ ፕሬዝዳንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ጸሃዬ ተፈራ ገልጸዋል።
ሌላው በአሚሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል የውጪ እርዳታወችን ከማቆም ጋ ተያይዞ የወጣው ተዕዛዝ ለድርጅቱ የስደተኞች ማቋቋምያ ይሰጥ የነበረውን ድጋፍ በማስቆሙ ምክንያት ተቋሙ ተያያዥ ስራወችን ለጊዜውም ቢሆን ለማቆም መገደዱን ዶ/ር ጸሃዬ ጠቁመዋል። ድርጅቱ እንዲህ ያለው አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ለወትሮው ተስፋ ለሆናቸው በርካታ ስደተኞች ጉዳት መሆኑ አይቀርም። አዳዲስ ህጎቹ ከስደተኛው ህዝብ እስከ ንግድ ተቋማት፣ ከቤተሰብ እስክ ድጋፍ ሰጪ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች ድረስ ያላንኳኩት በር የለም። ሁሉም ጋ ግራ መጋባትና ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ እርግጠኛ ያለመሆን ሁኔታ መኖሩ ደግሞ ችግሩን አብሶታል። እናም ሁሉም ሰው አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ፣ ራስን መጠበቅ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ በቂ መረጃ ላይ መመርኮዝ እና፣ ሁል ጊዜም ቢሆን ህጋዊ ድጋፍን ማግኘት እጅጉ አስፈላጊ ነው።
አበበ ፈለቀ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ