የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እርዳታ መቋረጥና ተፅዕኖው
ሰኞ፣ ሚያዝያ 27 2017የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እርዳታ መቋረጥና ተፅዕኖው
ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ርዳታ መቋረጥ ጋር ተያየዞ በአማራ ክልል በተፈናቃዮችና ሌሎች እርዳታ በሚፈልጉ ወገኖች ላይ ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተናገሩ ነው፣ መነግስት በበኩሉ ሊመጣ የሚችለውን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም እየሰራ እንደሆነ ገልጧል፡፡ አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ይሰጥ የነበረ እርዳታ መቀነስና በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ መቋረጥ በአማራ ክልል በሚገኙ ተፈናቃዮች ዘንድ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ተፈናቃዮች እየገለፁ ነው፡፡
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬሌ ከሰጡ ተፈናቃዮች መካከል ከትግራይ ክልል ተፈናቅሎ በጎንደር ከተማ አቅራቢያ ቀበሮ ሜዳና ከኦሮሚያ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙት ይጠቀሳሉ፣ እንደ ተፈናቃዮቹ ምግብ የለም፣ የመጠለያ ድንኳኖች ፈርሰዋል፣ የህክምና ባለሙያዎች ከመጠለያዎች ወጥተዋል፡፡ “ይደረጉ የነበሩ የዱቄት፣ የዘይትና አልባሳት ድጋፎች የሉም” ብለዋል፡፡የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት እርዳታ መቋረጥ በአማራ ክልል የሚፈጥረው ጫና
“ይደረጉ የነበሩ ድጋፎች አቁመዋል” የእርዳታ ሠራተኞች
34ሺህ ተፈናቃይ እያስተናገደ የሚገኘው የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ አስተባባሪ አቶ መሐመድ ሰኢድ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በተለያዩ ዘርፎች እገዛ ያደርግ እንደነበር አሳታውሰው አሁን ያ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ “ መጠለያ ጋር ተያይዞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ነበር የያዘው፣ እገዛ የሚያደርግለት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ነበር አሁን ክፍተት አለ፣ የገንዘብ እርዳታ የሚሰጡትም ጠፍተዋል፣ ተንቀሳቃሽ የህክምና አገልግት የሚሰጡ ተቋማት ነበሩ፣ እንሱም ሄደዋል” ነው ያሉት፡፡
መጠለያ ድነኳኖች ከጥቅም ውጪ እየሆኑ ነው
የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጸ/ቤት ኃላፊ አቶ ዓለሙ ይመር ሰሞኑን እንደግልፁልን ደግሞ በዞኑ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቀሉ 32 ሺህ ተፈናቃዮች በመጠለያና ከማህበረሰቡ ጋር ይኖራሉ፤ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እርዳታውን በማቋረጡ ተፈናቃዮች ለዘርፈ ብዙ ችግሮች መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡ በውጪ የመናገኛቸው ድጋፎች በመቋረጣቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተጀምረው መቆማቸውን አስረድተዋል፣ የተፈናቃዮች መጠለያ ድንኳኖች ፈራርሰዋል፣ መጀመሪያ መጠለያው ሲሰራ ድንኳኖቹ ለ6 ወራት እንዲያገለግሉ ታስቦ እንደነበር የሚጠቅሱት አቶ ዓለሙ አሁን ድነኳኖቹ ሳይጠገኑ 6 ዓመታት እነዳለፋቸው አመልክተዋል፡፡በUSAID ይፋ የተደረገው የጤና ፕሮጀክት
“ተፈናቃዮች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች እርዳታ ፈላጊዎችም ችግር ላይ ናቸው” ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጸ/ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ አከባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች እርዳታ ያገኙ እንደነበር አስረድተዋል በመሆኑም የእርዳታ ድርጅቱ እርዳታ ማቋረጡ ተፈናቃዮችንም ብቻ ሳይሆንሌሎች ወርሀዊ ቀለብ ይሰፈርላቸው ለነበሩ ዜጎችም ፈተና መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ማስተባባሪያ ኮሚሽን፣ ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በፊትም ቢሆን መንግስት የሚያቀርበው እርዳታ አብላጫ እንዳለው ጠቁመው፣ አሁንም መንግስት የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት እየሰራ መሆኑን ገልጠዋል፡፡
“ችግሩን ለመቋቋም እየተሰራ ነው” የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ኮሚሽን
ኮሚሽነሩ፣ “ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው፣ አንድ ቢሊዮን ብር ለእህል መግዣ ሰብስበናል፣ ከ46ሺህ ኩንታል በላይ አህልም ተሰብስቧል” ሲሉ እየተደረገ ነው ያሉትን ጥረት ገልጠዋል፡፡ የእርዳታ እህል ችግር ላለባቸው እንደሚላክላቸው፣ የጤናና መጠለያ ድንኳን ችግሮችን በተመለከተ የተነሳውንም ቅሬታ እንደሚያዩት ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ አጠቃላይ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በራስ አቅም የሚሰሩ ሥራዎችን በማጠናከር ከእርዳታ ጥገኝነት ለመውጣት ትኩረት መሰጠቱንም ኮሚሽነሩ አመልክተዋል፡፡ በአማራ ከልል 600ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮችን ጨምሮ 2 ሚሊዮን ያክል እርዳታ ፈላጊዎች እንደሚኖሩ ቀደም ሲል ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ