የአማራ ልማት ማሕበር (አልማ) እና የልማት እንቅስቃሴው
ሰኞ፣ ሰኔ 30 2017አልማ አባላቱን ወደ 4.6 ሚሊዮን አድርሷል
የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ባለፉት 5 ዓመታት በክልሉ ከ2ሺህ 950 በላይ የመማሪያ ክፍሎች መገንባቱን አመለከተ፣ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው አልማ ችግሮቻቸውን እንደፈታላቸው ተናግረዋል፣ ማህበሩ ባለፉት 32 ዓመታት ከ10 ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ያሰባሰበ ሲሆን፣ አልማ 4 ሚሊዮን 6 መቶ ሺህ መደበኛ አባላት እንዳሉትም ታውቋል፡፡
የአማራ ልማት ማህበር ባለፉት 5 ዓመታት ከህብረተሰቡና ከአጋር አካላት ባሰባሰበው ገንዘብ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት መገንባቱን አስታወቀ፡፡ የማህበሩ የስትራቴጂክና ኢኖቬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አበረ መኩሪያ ዛሬ በቢሯቸው በሰጡት መግለጫ አልማ ባለፉት 5 ዓመታ ከመደበኛ አባላቱና ከአጋር አካላት በአገኘው 7 ቢሊዮን 877 ሚሊዮን ብር የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡
በአማራ ክልል አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ሆነዋል
አልማ ባልፉት 5 ዓመታት ከ7. 8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰብስቧል
አቶ አበረ በመግለጫቸው እንዳብራሩት፣ በተጠቀሰው ጊዜ 7 ቢሊዮን፣ 877 ሚሊዮን 462ሺህ ብር ከተለያዩ አካላት ተሰብስቧል፣ በዚህም “በ1ሺህ 198 ትምህርት ቤቶች ግቢ ውስጥ 2ሺህ 952 የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተዋል” ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ 114 የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ቴና ተቋማት መገንባታቸውን ነው ያብራሩት፡፤
ባለፉት 32 ዓመታት ከ10 ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብም በአማራ ክልል፣ በተለይም በትምህርቱና በጤናው ዘርፍ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል መማር ያልቻሉ ልጃገረዶች እያገቡ ነዉ
“አልማ በትምህርት ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል” መምህራን
የትምህርት ተቋም ከተገነባላቸው መካክል በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ የሐይቅ ቁጥር 2 አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አንተነህ አራጌ አልማ የትምህርት ቤታቸውን ሁኔታ በማሻሻሉ ተማሪዎቻቸው በጥሩ ሁኔታ ትምህርት እየተከታተሉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
“... ቀደም ሲል ትምህርት ቤቱ የፈራረሰ፣ በአቧራ የተሞላ ነበር፣ ለህፃናት መማሪያ የማይመችና የተጎሳቆለ ነበር፣ አልማ ከአጋር አካላት ጋር ባደረገው ድጋፍ 12 መማሪያ ክፍሎች ያሏቸው 3 ህንፃዎችና አንድ የአስተዳደር ህንፃ ተገንብቶልናል፡፡” ብለዋል፡፡
የሐራ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ መሀመድ ይማም እበበኩላቸው አልማ በሚያደርገው ድጋፍ የትምህርት ቤት ይዞታቸው በእጅጉ መሻሻሉን ነው ለዶይቼ ቬሌ በስልክ የተናገሩት፡፡
በአማራ ክልል ወደ 4 ሚሊዮን ታዳጊዎች ት/ቤት አይሄዱም ተባለ
“በሰሜኑ ጦርነት የወደሙ ት/ቤቶች ተገንብተውል”
በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ትምህርት ቤታቸው ወድሞ እንደነበር የገለፁት መምህሩ በአልማ ድጋፍ ትምህርት ቤታቸው በዘመናዊ መልኩ መገንባቱን ገልጠዋል፡፡ ቀደም ሲል የመምህር ተማሪ ጥምርታ 1 ለ 90 እንደነበር ያወሱት አቶ መሐመድ አሁን በተሻለ ደረጃ ላይ እንዳለ ነው ያመለከቱት፡፡ ከ300 በላይ የተማሪዎች መቀመጫ ወንበሮችም ከማህበሩ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ ለ50 ተማሪዎችም የአንድ ዓመት የትምህርት ቁሳቁስ እንደተበረከተላቸው አስረድተዋል፡፡
በአማራ ክልል የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክንዱ ዘውዱ በሰጡን አስተያየት ማህበሩ በዞኑ በርካታ ማህበራዊ መስጫ ተቋማትን መገንባቱን አስረድተዋል፡፡ በተለይም ቤተ መጽሐፍትን፣ የመማሪያ ክፍሎችንና ሌሎች ከትምህርት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን አከናውኗል ነው ያሉት፡፡
አማራ ክልል የተመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ ነው ተባለ
የአማራ ልማት ማህበር የተመሰረተው በ1984 ዓም ሲሆን 669 ሠራተኞች አሉት፡፡ በአገር ውስጥና በውጪ አገር ከ4.6 ሚሊዮን በላይ መደበኛ አባላትንም ያቀፈ ነው፡፡ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በአውስትራሊያና በኤዥያ 22 የሚደርሱ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ዓለም አቀፍ ማህበር ለመሆን ጥረት እያደረገ እንደሆነም ከማህበሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ