የናዚ ጀርመን የሰዎች መጨፍጨፍያና ማጎሪያ ካምፕ አውሽቪትዝ ነጻ የወጣበት 80ኛ ዓመት
ማክሰኞ፣ ጥር 20 2017አውሽቪትዝ ምን ነበር?
በጎርጎሮሳዊው ጥር 27 ቀን 1945 ዓ.ም በሶቭየት ኅብረት ጦር ከናዚዎች ነጻ የወጣው አውሽቪትዝ-ቢርከናው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለኳሽ ናዚ ጀርመን ዘመን አሰቃቂ ግድያ የሚፈጸምበት ትልቁ የሰዎች ማጎሪያ ነበር። በዚህ ቦታ ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ሰዎች በናዚዎች መጨፍጨፋቸው በታሪክ ተመዝግቧል። በዶቼቬለው ክሪስቶፍ ሽትራክ ዘገባ መሠረት የአውሽቪትዝ-ቢርከናው ግድያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በማንኛውም ስፍራ ከተፈጸመ የሰዎች ጭፍጨፋ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም። ስፍራው በሶቭየት ኅብረት ወታደሮች ነጻ የወጣበት 80ኛ ዓመት የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ፣ የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ፣የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ፣የእንግሊዙ ንጉስ ቻርልስና የበርካታ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት ታስቧል። በዚህ የመታሰቢያ ስነ ስርዓት ላይ ስፍራውን ነጻ ያወጣው የሶቭየት ኅብረት ጦር አካል የነበረችው የሩስያ መሪ ግን በሩስያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት አልተጋበዙም።
ትንሽቱ የፖላንድ ከተማ ኦስቬንቺም በጎርጎሮሳዊው 1939 ዓ.ም. በናዚ ጀርመን ጦር ኃይል ሙሉ በሙሉ ታያዘች ። በወቅቱም የነዋሪዎችዋ ቁጥር 10 ሺህ ያህል ነበር።ያኔ ናዚዎች ወደ ግዛታቸው የቀላቀሏትን ይህችን ከተማ ስሟን ቀይረው አውሽቪትዝ አሏት። በ1941 ደግሞ ትልቁን የሰዎች መግደያ የአውሽቪትዝ-ቢርክናው የሰዎች ማጎሪያ ካምፕን በዚሁ አካባቢ አቋቋሙ። የዓለም አቀፉ የአውሽቪትዝ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዝዳንት ክሪስቶፍ ሆይብነር ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ስፍራው የተቀነባበረ እና ስልታዊ ግድያ የሚፈጸምበት ፣ ሰዎች በማንነታቸው ተለይተው የሚገደሉበትም ስፍራም ጭምር ነበር። « በመንግስት የተደረጃ ግድያ የሚፈጸምበት ወንጀል ነበር።ወንጀሉም ሰዎችን ለመግደል ስልታዊ መሳሪያዎችን ማደራጀትን ያካትታል። ይህም በጣም የተወሰኑ ሰዎች ማለት አይሁዶች፣ ሲንቲና ሮማዎች፣እንዲሁም በርካታ ሌሎች ላይ ያተኮረ ነበር።»
የአውሽቪትዝ መታሰቢያ 75 ተኛ ዓመት
በዚህ ካምፕ ውስጥ እስከ ጎርጎሮሳዊው ጥር 1945 ዓም ድረስ ቢያንስ 1.1 ሚሊዮን ሰዎች በናዚዎች ተጨፍጭፈዋል። ከተገደሉት አብዛኛዎች አይሁዶች ቢሆኑም ጂፕሲ ተብለው የሚታወቁት በርካታ ሮማ እና ሲንቲዎች፣ አካል ጉዳተኞች፣ግብረ ሰዶማውያን፣የፖለቲካ እስረኞች እና ሌሎች አናሳ የሚባሉ ቡድኖች አባላትም ይገኙበታል። ስፍራው ሰዎችን ለማጎርና ለመግደልም የተመረጠው በአውሮጳ ማዕከል የሚገኝና በቀላሉም በባቡር ሊደረስበት የሚችል በመሆኑ ነበር።ከዚህ በተጨማሪ የዓለም አቀፉ የአውሽቪትዝ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዝዳንት ክሪስቶፍ ሆይብነር ለዶቼቬ እንደተናገሩት የቦታ ምርጫው የየሎጂስቲክ አቅርቦትን ማቀላጠፍንም ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር ። «አውሽቪትዝ እነርሱ እንደሚሉት ሰዎችን ከአገር ከመባረር፣ ከማስወጣት ጋር ተመሳሳይ ቃል ነው ። ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት የተመረጠ ቃል ነው። በትራንስፖርት ረገድ በአውሮጳ መሃል ላይ ስለሚገኝ እነዚህን የተጋዙ ሰዎችን የሚያጓጉዙ ባቡሮቹ በቀላሉ ሊደረሱበት ይችላሉ።በእርግጥ የሎጂስቲክስ ጉዳዮችም ነበሩ።»
ናዚዎች ለስልታዊ ግድያ ያወጡት የሎጂስቲክስ እቅድ
የሎጂስቲክ አቅርቦት ወሳኝ ነበር። ናዚዎች ሁሉም ነገር በፍጥነት እንዲከናወን ነበር የሚፈልጉት በተቻለ መጠን በርካታ ሰዎችን መግደል ይፈልጉ ነበር። ናዚዎች በደንብ በማቀድ ፣በጅምላ ግድያ እና የገደሏቸውንም በመዝገብ በማስፈር ይታወቃሉ። በጀርመን በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የጅምላ ግድያ የተካሄደው ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊትም ነበር። ጀርመን ፖላንድን በጎርጎሮሳዊው 1939 መጀመሪያ ላይ ማጥቃት እንደጀመረች በምስራቅ አውሮጳ ብዙ የጅምላ ግድያዎች ተፈጽመዋል። እነዚህ ወንጀሎችም በቅጡ የተሰነዱ ናቸው።
የሂትለርዋ ጀርመን እና ጦር ሠራዊቷ አብዛኛውን አውሮጳ ከተቆጣጠሩ በኋላ እቅዳቸው አይሁዶችን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ነበር። ይህን እቅዳቸውን ለማሳካትም ጥር 20 ቀን 1942 ዓም ምሥራቅ በርሊን ውስጥ ቫንዜ በተባለ ሐይቅ ላይ በሚገኝ ያኔ የፖሊሶችና ብሔራዊ ሶሻሊስቶች ማረፊያ በነበረ ቪላ ውስጥ ተሰበሰቡ።በዚሁ ስፍራ 15 የናዚ አገዛዝ ባልደረቦች፣ በአውሮጳውያን አይሁዶች ላይ የሚፈጸም የጅምላ ማጋዝና ግድያን ግልጽ የሚያደርግና የሚያመቻች አንድ ሰዓት ተኩል የወሰደ ጉባኤ አካሂዱ። ከተሰታፊዎቹ መካከል ብሔራዊ ሶሻሊስት ከሚባሉት አንዱ የናዚ ከፍተኛ መኮንን ሩዶልፍ ላንገ ለስብሰባው በርሊን ከመሄዱ አንድ ቀን አስቀድሞ በአሁኗ ላቲቭያ ዋና ከተማ ሪጋ አካባቢ የሚገኙ ከ900 በላይ አይሁዶች ተኩስ እንዲከፈትባቸው አዞ ነበር።
ለጎብኝዎች ክፍት የሆነው የቫንዜው ጉባኤ የተካሄደበት ቤት ውስጥ የሚገኝ የ90 ደቂቃውን ጉባኤ የሚመለከት አንድ የማስታወሻ ጽሁፍ ውስጥ «ግድያ» የሚል ቃል የለም።ሆኖም በጽሁፉ ላይ « ብቸኛው የመጨረሻ መፍትኄ»የሚል ይገኝበታል። ይሁንና በዚህ ስብሰባ ላይ የተካፈለ ሁሉ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ያውቃሉ። በዚያን እለት በተካሄደው ጉባኤ ላይ ከታቀዱት ውስጥ ተጨማሪ መጨፍጨፊያ ካምፖችን መስራትም ይገኝበታል። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በመጋቢት 1942 የታጋዙ ሰዎችን የሚወስዱ ባቡሮች ከመላው አውሮጳ በናዚ ወደተያዘችው ወደ ፖላንድ ማቅናት ጀመሩ።ዓላማውም አይሁዶችን ከአውሮጳ ማጥፋት ነበር።
የአውሽቪትስ 80ኛ ዓመት ሲዘከር
በወቅቱ ከጀርመንም ሆነ ከሌላ የአውሮጳ ሀገር የሚነሱ ባቡሮች መድረሻ አውሽቪትዝ ሆነ። ሰዎች የሚገደሉበት የአውሽቪትዝ-ቢርከናው ካምፕ የራሱ የባቡር መስመር ነበረው።ከመካካላቸው የሚገደሉት ተለይተው በጋዝ ታፍነው ወደሚሞቱበት ስፍራ ይወሰዳሉ። ቀሪዎቹ ደግሞ በመጀመሪያ በማጎሪያ ካምፑ ውስጥ በጉልበት ስራ ይሰማራሉ ።
ኮሎኝ ፣ሽቱትጋርት፣ ሀምቡርግ እና ቪስባደንን ጨምሮ በበርካታ የጀርመን ከተሞች ግድያ ወደ ሚፈጸምባቸው ካምፖች የተጋዙት ሰዎች መታሰቢያዎች ይገኛሉ። ከመካከላቸው በበርሊኑ የግሩነቫልድ ባቡር ጣቢያ የሚገኘው 17 ቁጥር የባቡር ማቆሚያና መነሻ መታሰቢያ በጣም ታዋቂ ከሆኑት አንዱ ነው። ስፍራው በፖለቲከኞችና በሌሎች የውጭ ሀገር ጎብኚ ባለሥልጣናት ይዘወተራል። ከዚህ የባቡር ጣቢያ ብቻ 17 ሺህ አይሁዶችን ያሳፈሩ 35 እንደሚደርሱ የተነገረ ባቡሮች ወደ አውሽቪትዝ ቢርከናው ሄደዋል።
ከበርካታ የአውሮጳ ከተሞች አይሁዶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ አውሽቪትዝና ሌሎች ማጎሪያዎች በከብቶች ማመላለሻ ባቡሮችም ጭምር ይወሰዱ ነበር። ባቡሮቹ ከማዕከላዊ እና ምሥራቅ አውሮጳ እንዲሁም ከፈረንሳይ፣ ቤልጅየም ኔዘርላንድስ፣ ጣሊያን፣ ሀንጋሪ እና ግሪክ እንዲሁም ከባልካን ሀገራት ከቡልጋሪያ እና ከመቆዶንያም ይመጡ ነበር። በሚቀጥለው ሐምሌ 100 ኛ ዓመታቸውን የሚያከብሩት ቤላሩሳዊቷ አኒታ ላስከር ቫልፊሽ አውሽቪትዝ በባቡር ከተወሰዱት ወጣት ሴቶች አንዷ ነበሩ። እድለኛ ሆነው በሕይወት ተርፈዋል።
ከምክንያቶቹ በከፊል በዚያ በነበረው የልጃገረዶች ኦርኬስትራ ውስጥ ቼሎ የተባለውን የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት በመቻላቸው ሊሆን ይችላል።ከ1943 እስከ 1944 አውሽቪትዝ የነበሩት አኒታ ላስከር ቫልፊሽ ከዚያ በፊት ሰሜን ጀርመኑ በኒደርዛክሰን ግዛት በሚገኘው ቤርግነ ቤልሰን በተባለው የሰዎች ማጎሪያ ውስጥ ነበሩ። በጎርጎሮሳዊው 2018 የአውሽቪትዝ ሰለባዎች በጀርመን ምክር ቤት ቡንደስታግ ሲታሰቡ ባደረጉት ንግግር አንድ ሰው አውሽቪትዝ እንደደረሰ ሰዎች በጋዝ ታፍነው ወደሚገደሉበት ክፍል ባይወሰድም በዚያ ብዙ አይቆይም። ቢበዛ ሦስት ወር ብቻ ነው ብለው ነበር ። በርሳቸው እምነት የሙዚቃ ችሎታቸውው በሕይወት የመኖር እድል ሰጥቷቸዋል። ወላጆቻቸው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተገደሉባቸው ላስከር ቫልፊሽ ከጦርነቱ በኋላ ኑሮአቸውን ብሪታንያ አድርገዋል።
እርሳቸው እንደሚያስታውሱት ወደ አውሽቪትስ የሚወስዱ በርካታ መጓጓዣዎች ነበሩ። ወደዚያ የተላኩት ሰዎች በጋዝ ታፍነው የሚገደሉበት ቦታ ስፍራ ሰውነታቸው መግባት ካልቻለ ተተኩሶባቸው ይገደላሉ። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ከነነፍሳቸው ወደ ማቃጠያ ጉድጎዶችም ይወረወሩም ነበር።ዛሬ አውሽቪትዝን የሚጎበኙ ሰዎች በስፍራው በተፈጸሙት አሰቃቂ ተግባራት ይደነዝዛሉ። የተከማቹ የሜትር ከፍታ ያላቸው የሰዎች ፀጉሮች፣መነጽሮች፣ አርቲፊሽያል ልብ እና ጡት የመሳሰሉ የሰውነት ክፍሎች እና የግለሰቦች ንብረቶች በምስክርነት በአውሽቪትስ ለእይታ ቀርበዋል። እነዚህን የመሳሰሉ ግፎች የተፈጸሙበትን አውሽቪትዝ የ ሶቭየት ኅብረት ጦር በጎርጎሮሳዊው ጥር 27 ቀን 1945 ዓም ነበር ነጻ ያወጣው። ነጻ አውጭዎቹ ሶቭየቶች ያኔ በአውሽቪትስ ያዩትንን ማመን ተስኗቸው ነበር።
ከአውሽቪትዙ ግድያ ከተረፉት ሰዎች ብዙዎቹን ያነጋገሩት የረዥም ጊዜው የዓለም አቀፉ የአውሽቪትዝ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዝዳንት ክሪስቶፍ ሆይብነር ከነርሱ የሰሙትን ጠቅለል አድርገው ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
«ያኔ ወቅቱ ፍፁም ዝምታ የሰፈነበት ነበር። ነጻ አውጭዎቹ ከዩክሬን ከሩስያ እና ከቀድሞዋ የሶቭየት ሕብረት ግዛቶች የመጡ ወጣት ወታደሮች ነበሩ። በአውሽቪትዝ በራፍ ላይ ቆመው የሚያዩትን ማመን ነበር ያቃታቸው እስከዛ ድረስ ብዙ እጅግ አሰፈሪ ነገሮችን አይተዋል። እዛ ሲደርሱ ያዩት ግን አይተው የማያውቁት ነበር። ሞት በሁለት እግሩ ቆሞ ነበር ያዩት። የሰዎቹን ፊትና ዓይኖች ካዩ በኋላ ነበር ሕይወት ያላቸው አጽሞች መሆናቸውን የተገነዘቡት።»
የአደጋውን መጠን መረዳት አዳጋች ነበር
አውሽቪትዝ ውስጥ የታጎሩ እስረኞች መለያ ቁጥር ይሰጣቸዋል። ይህ ቁጥርም በእጆጃቸው ላይ ተነቅሶባቸዋል። አኒተ ላስካር ቫልፊሽ እንደተናገሩት «በንጹሀን ላይ ይፈጸማሉ ተብለው የማይታሰቡ ወንጀሎች ቀስ በቀስ ይፋ መሆን መጀመራቸውን ያኔ የአደጋውን መጠንም መረዳት አዳጋች እንደነበረ በመንግስት ደረጃም የተቀነባበረ ድርጊት መሆኑን እናም ወንጀሉ ሰዎችን በስልታዊ መንገድ ለመግደል የተዋቀረ እንደነበር ተናግረዋል። በጀርመን በአውሽቪትዝ የተፈጸሙ አሰቃቂ ድርጊቶችን የመጋፈጥ ሰፊ ሂደት ከመጀመሩ በፊት አስርት ዓመታት ወስዷል። ከዚህ አሰቃቂ ድርጊት ሰለባዎች አንዳንድ የመጨረሻ ምስክሮች ዛሬም በሕይወት አሉ።
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ