የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ፣ የገና ሸመታና የመሬት መንቀጥቀጥ
ሐሙስ፣ ጥር 1 2017
የ2017 ታኅሳስ አብቅቶ ዛሬ ጥር አንድ ብሏል።ለወትሮዉ ለደገኛዉ ኢትዮጵያዊ ገበሬ ምርት መሰብሰቢያ፣ መሰረጊያ፣መደሰቻ ወርም ነበር።ዘንድሮ ግን ኢትዮጵያ ጥርን የተቀበለችዉ ዓመታት ካስቆጠረዉ ግጭት፣ዉዝግብና የኑሮ ዉድነት ጋር ብዙም በማታዉቀዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ከፊል ግዛትዋ እየተናጠ፣ በነዳጅ ዘይት ዋጋ ጭማሪ ለተጨማሪ የኑሮ ዉድነት ተጋለጠ ነዉ።ለክርስትና እምነት ተከታዮች የገና ገበያ አልቀመስ ማለቱም ከሳምንቱ ዓበይት ዜናዎች አንዱ ነበር።
ሳምንቱን የነዳጅ ዘይት ዋጋ ጭማሪ፣ የገና በዓል ገበያና በአፋር ክልል የተከሰተዉ የመሬት መንቀጥቀጥ የብዙ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተከታታዮችን ትኩረት ስብሰበዋል።ከተሰጡ አስተያየቶች የጎሉት ከስድብና ዘለፋ የፀዱትን ነቅሰን ባጫጭሩ እንቃኛለን።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለነዳጅ ዘይት የሚሰጠዉን ድጎማ ቀስበቀስ እየቀነሰ፣በሸማቹ ላይ የዋጋ ጭማሪ እያደረገ ነዉ።ብዙዎች እንደዘገቡት መንግሥት ለነዳጅ ዘይት ይሰጥ የነበረዉን ድጎማ የሚቀንሰዉ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF)ን ከመሳሰሉ አበዳሪዎች ጋር ብድር ለማግኘት በገባዉ ዉል መሠረት ነዉ።በያዝነዉ ሳምንት ይፋ በሆነዉ አዲስ የዋጋ ተመን መሠረት አንድ ሊትር ቤንዚን ባንድ ጊዜ 10 ብር ጭምሮ አሁን 101 ብር ከ47 ሳንቲም ሆኗል።
ማሜሜክስ አቡ ረሐና «ድፍድፍ አገኘን ምናምን የተባለውስ?» ጠየቀ በፌስ ቡክ።ቴዳ ዴሌሌም «የሶማሌው ክልል ነዳጅ ግን የት ገባ?» የሱም ጥያቄ ነዉ።
በነዳጅ ዘይት ዋጋ ላይ አዲስ ጭማሪ የተደረገዉ «የጫኑትን ነዳጅ ዘይት አላግባብ ደብቀዉ ነበር» የተባሉ ከ50 በላይ ነዳጅ ጫኝ መኪኖች (ቮቴዎች) አፋር ክልል መገኘታቸዉን መንግስት ባስታወቀ በዕለታት ዉስጥ መሆኑ ነዉ።መብራቱ ከበደ በፌስ ቡክ እንደፃፈዉ የተደበቀ ነዳጅ ዘይት «ተገኘ» መባሉና የዋጋዉ ጭምሪ መገጣጠም እንቆቅልሽ ሳይሆንበት አልቀረም።
«ተደብቆ ተያዘ በተባለው ነዳጅ ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲደረግ መወሰን ማለት ደባቂው ማን ነበር የሚለውን መመለስ አይችልምን ?» ይጠይቃል መብራቱ።
ሳላሑዲን አል አዩቢ «ከባድ ነው።» ይላል እሱም በፌስ ቡክ። «ሀገሪቱ ወደ ለየለት ውንብድና ትገባለች።አከለ ሳላሑዲን።የፌስ ቡክ ስሙን ጋሞ ዙኔ ያለ አስተያየት ሰጪ ግን «ዝም ላለ ሕዝብ አይበዛበትም» ይላል።
ዌኩ ና «ለ IMF እና ለUAE እንደተሸጥን እስካሁን ያወቀ ማነው?» ጥያቄ ነዉ።በፌስ ቡክ የቀረበ ጥያቄ።ወደ ሁለተኛዉ ርዕስ እንለፍ።
ገና በዓል ሸመታ-ዉድ ነዉ
ሁለተኛዉ ርዕስ ባለፈዉ ማክሰኞ የተከበረዉ የገና በአል ሽመታ ነዉ።ብዙ ጊዜ በበዓላት ወቅት ለሽያጭ የሚቀርቡ ሸቀጦችና የእርድ ከብቶች ከወትሮዉ በርከት፣ ዋጋቸዉም ጨመር ያደርጋል።ዘንድሮም በብዙ አካባቢዎች የምርት እጥረት አልታየም።ዋጋዉ ግን ከነባሩ የኑሮ ዉድነት፣ አማራና ኦሮሚያ ክልልን በመሳሰሉ አካባቢዎች ካለዉ ግጭትና የመንቀሳቀስ ችግር ጋር ተደማምሮ ብዙዎች እንዳሉት አለቅጥ ተንቻርሯል።
ኃይለአብ በላይ ኦባዶ በተባለዉ አካባቢ ዶሮ ዝቅተኛዉ 500 ከፍተኛዉ ደግሞ 2000 መሸጡን ፅፏል-በፌስ ቡክ።ፊሽ መኮንን በፋንታዉ «የጉድ ሐገር» ይላል።ጉድ የማለቱን ምክንያት ሲያስረዳ «አንድ በሬ ሁለት መቶ ሺ ፣ አንድ ፍየል ሰላሳ ሺ ብር ሲሸጥ። ለአንድ ቀን ሳይበላ ቢቀርስ። ግማሹ የዳቦ መግዣ ባጣበት ሀገር» ፊሽ መኮንን ነዉ ይኽን ባዩ።
ሕይወት ደረጀ « ኦ! በጣም ደስ የሚል አከባበር ነበር» ትላለች በፌስ ቡክ።ፀሎት አከለችበትም።«ፈጣሪ አምላካችን ሐገራችንን ይጠብቅ» ብላ።
አበራ ሲሳይ ጌታቸዉ ግን የከብትና የምርት ዋጋ የሚባለዉን ያክል አልጨመረም ባይ ነዉ።አበራ በፌስ ቡክ በፃፈዉ ዘለግ ያለ አስተያየት፣ «የበግ እና የፍየል ዋጋ በጣም እንደተወደደ ነው። ኮተቤ ካራ አሎ አካበቢ ከብት ከ55,000 ብር በታች ሁሉ ሲሸጠ ነበር።ጤፍም ክረምት ከነበረዉ ቀንሷል» ባይ ነዉ።አበራ።ይሁንና ሥጋና ምግብ ቤቶች ዋጋ አልቀነሱም-እንደ አበራ ግምገማ።
ሐሰን ጣሒር ጂቢኮ «እኛ በሩቅ ከማየት ውጪ የመግዣ ገንዘብ የለንም።» ጄይ ሸሪፍ ግን ማስታወቂያ ብጤ አለዉ።
«የበግ ኪራይ ስንት ገባ? በዓሉን ከኔ ጋ ዉሎ፣ ተጫውቶ፣ ፎቶ ተነስቶ፣ ጎረቤቶቼ እንዲሰሙት ጮክ ብሎ የሚጮህና በነጋታው የሚመለስ ጠይቁልኝ…» የዘንድሮዉ በዓል አልፏል።ምናልባት ለከርሞ---የምታዉቁ ጠቁሙት።እና ወደ መጨረሻዉ ርዕሳችን እንለፍ።
የመሬት መንቀጥቀጥ። ሰዉ አልሞተም፣ ግን ተፈናቅሏል፣ ንብረትም ጠፍቷል
የኦሮሚያና የአማራ ክልሎችን የሚያዋስነዉ የአፋር ክልል በተደጋጋሚ በመሬት መንቀጥቀጥ እየተመታ ነዉ።በተለይ አዋሽ-ፈንታሌና ዱለቻ ወረዳዎች ላይ የጠነከረዉ የመሬት መንቀጥቀጥ አንዳዴ ብዙ ኪሎሜትሮች ርቆ ከገለምሶ እስከ አዲስ አበባ ድረስ የተለያዩ አካባቢዎችን ይነዝራል።የመሬት መንቀጥቀጡ ከወራት በፊት ዶለቻ አካባቢ ዉሐ ሲያፈልቅ፣ ፈንታሌ ተራራ ልይ ደግሞ ጢስ አዉጥቷል።
ሰሞኑን ደግሞ ዶፈን-ቦለሐሞ አካባቢ የእሳተ ጎሞራ ትፍ (ላቫ) የሚመስል ቅላጭ፣አዋራና ብናኝ መታየቱን የአካባቢዉ ነዋሪዎች አስታዉቀዋል።የመሬት መንቀጥቀጡ በሰዉ ሕይወት ላይ እስካሁን ያደረሰዉ ጉዳት ስለመኖር አለመኖሩ በግልፅ የተባለ ነገር የለም።
ይሁንና የከሰም ስኳር ፋብሪካ ሕንፃዎችን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መኖሪያ፣ መማሪያና መስሪያ ቤቶችን አፈራርሷል።በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችም መፈናቀላቸዉ ተዘግቧል።ራቢያት ሐሰን በፌስ ቡክ ዱዓ ብጤ ታደርጋለች። «አላህ በአዛኝነቱ በታጋሽነቱ ሸሃዳ ከሌለው ሞት ይጠብቀን» እያለች።
ዛፉ ዛሳ ግን በፌስ ቡክ «የኢትዮጵያ ከፍታ ግዜ ይመጣል። የተከለከልነው ቀይ ባሕር ወደ ኢትዮጵያ ሊፈስ ነው» ይላል።ኢማም ሱጋቶ ዜይኔ ሪያድ--።«የባህር በር ወይም የወደብ ጥያቄያችን ከሰው ሳይሆን ከፈጣሪ ዘንድ ዘላቂ ምላሽ ያገኛል ! አብሽሩ» ይላል።-ኢማም ሱጋቶ ዜይኔ ሪያድ-ስሙ ግን ረጅም ነዉ።
በሪሁ ሐይሉ «ሰው የሰውን መሬት ለምውሰድ ይባላል፣ መሬት እኛት ልትበላ አፍዋን ከፍታ እየመጣች ነው።» አለ በፌስ ቡክ።ዘነቡቴና ቴና «እግዚአብሔር ሆይ ማረን፣ራራልን፣ ይቅር በለን አሜን» ትላለች።ደሳለኝ ተሰማ እሱም በፌስ ቡክ ምፀት ብጤ አስፍሯል።«ሁሉም መለያየትን ስለሚሰብክ፣ ፈጣሪ የፋላጎታችንን ሊሰጠን ይሆን። እንጃ እሱ ያዉቃል።»ደሳለኝ ተሰማ ነዉ-ይኽን ባዩ።
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ