የነዳጅ እጥረት በደቡባዊ ኢትዮጵያ የሸቀጦች ዝዉዉርን እያጎለ ነዉ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 17 2017የደቡብ ኢትዮጵያና የሲዳማ ክልል ነጋዴዎች በናፍጣ እጥረት ምክንያት የገቢና ወጪ ምርቶችን ማጓጓዝ እንዳልቻሉ አስታወቁ።ነጋዴዎቹ እንደሚሉት ናፍጣ ባለመኖሩ ወደ መሀል አገር የሚልኩት በተለይ አትክልትና ፍራፍሬ እየተበላሸባቸዉ ነዉ፡፡ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች በበኩላቸዉ የሚጠይቁትን ያክል ነዳጅ ዘይት እንደማያገኙ ገልጠዋል።የኢትዮጵያ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ግን የነዳጅ ጥረት የለም።ሚንስቴሩ ለነዳጅ እጥረቱ “ስግብግብ “ ያላቸዉን ነጋዴዎች ተጠያቂ አድርጓል
የነፍጣ አለመኖር ያስከተለው መስተጓጎል
አቶ ያሲን ረመዳን በደቡብ ኢትዮጵያ እና በሲዳማ ክልሎች በአስመጪ እና ላኪነት እንዲሁም በአትክልት እና ፍራፍሬ አቅራቢነት ተሠማርተው እንደሚገኙ ይናገራሉ ፡፡ ይሁንእንጂ የናፍጣ እና የቢንዚን ምርት እጦት ሥራቸውን አንዳስተጓጎለባቸው ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ ናፍጣ አለማግኘታችን ከፍተኛ ጫና ፈጥሮብናል ያሉት አቶ ያሲን “ የወጪ እና የገቢ ምርቶችን የጫኑ ተሸከርካሪዎች ተገተዋል ፡፡ በወቅቱ ከአገር መውጣትም ሆነ ወደ ማሀል አገር መንቀሳቀስ አልቻሉም ፡፡ እኛ የጫነውን ፍራፍሬና አትክልት ወደ መሀል ገበያ ለማድረስ ተቸግረናል ፡፡ ለምሳሌ የቲማቲም ምርት ለአንድ ቀን ካደረ በሚቀጥለው ቀን በሰበሰ ማለት ነው ፡፡ ይህ ደግሞ በህዝቡም ሆነ በመንግሥት ላይ ጉዳት ያመጣል ፡፡ የሚመለከታቸው የንግድ ቢሮ ሃላፊዎች ችግሩን ሊያስተካክሉ ይገባል “ ብለዋል ፡፡
በናፍጣ ሠልፍ የተማረሩት አሽከርካሪዎች
በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ለወትሮም ቢሆን የተሽከርካሪ ሠልፎች ተለይቷቸው አያውቅም ፡፡ በተለይ ካለፉት ሦስት ቀናት ወዲህ ሰልፉ ብሶበት ነው የሚስተዋለው ፡፡ ዶቼ ቬለ በወረፋ ላይ እንዳሉ ያነጋጋራቸው የአርሻ ትራክተር ሾፌሮች እና የአንዱስትሪ ግበዓቶችን አራግፈው የሚመለሱ የኬኒያ የጭነት አሽከርካሪዎች በሁኔታው መማረራቸውን ተናግረዋል ፡፡ በተለይም ለሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ግብአት በማራገፍ ወደ አገሩ ለመመለስ ናፍጣ ሊያገኝ አለመቻሉን ለዶቼ ቬለ የተናገረው ሳራዋ ማባዋ የተባለ አሽከርካሪ ‹‹ ከኬኒያ እዚህ የሚያደርሰኝን ጋዝ ቀድቼ ነው የመጣሁት ፡፡ ለመመለስ ተጨማሪ ቢያሥፈልገኝም እዚህ ላገኝ አልቻልኩም ፡፡ የግድ እስከ ድንበር የሚያደርሰኝን መቅዳት ይኖርብኛል ፡፡ ነገር ግን አስቸጋሪ ነው ፡፡ከጠዋት ጀምሮ ለረጅም ሰዓታት እየጠበቁ እገኛለሁ “ በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል ፡፡
የሚንስትሩ መግለጫ
ዶቼ ቬለ የደቡብ ኢትዮጵያ እና የሲዳማ ክልል የሥራ ሃላፊዎችን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ሃላፊዎቹን ማግኘት ባለመቻሉ ሊሳካ አልቻለም ፡፡ አንድ ሥማቸውና ድምጻቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሀዋሳ ከተማ ነዳጅ ማደያ ባለቤት ግን እጥረቱ ሊከሰት የቻለው አቅርቦቱን በጠየቅነው መጠን ማግኘት ባለመቻላችን ነው ብለዋል ፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በበኩሉ በአገሪቱ ምንም አይነት የአቅርቦት እጥረት እንደሌለ አስታውቋል፡፡ ይልቁንም አንዳንዶች የዋጋ ክለሳ ሊኖር ይችላል በሚል በአቋራጭ ለመክበር በሚያደርጉት ሙከራ የተነሳ ነው ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ዶክተር ካሳሁን ጎፌ ትናንት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል ፡፡
የነዳጅ አቅርቦት እና ሥርጭት ላይ እየተስተዋለ የሚገኘው ችግር ባልተገባ መንገድ በተሰራጨ የተሳሳተ መረጃ ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን የጠቀሱት ሚንስትሩ “ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ይሆናል የሚል ሃሳብ እንዲኖር ማድረጉን እና በስግብግብ ነጋዴዎች ምክንያት የነዳጅ እጥረት እንዳለ ለማስመሰል ሙከራ እየተደረገ ይገኛል ፡፡ አሁን ላይ ምንም አይነት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እንደሌለ እና ይህንን ተከትሎ በአቅርቦቱ ላይ እክል በሚፈጥሩ አካላት ላይ ክትትልና ርምጃ መውሰድ ተጀምሯል “ ብለዋል።
ዘገባ ፡ ሸዋንግዛው ወጋየሁ