የነዳጅ እጥረት ሥራ ማስተጓጎሉ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 10 2017
የሀገር አቋራጭ የመጓዣ መኪኖች በደሴ ከተማ ቆመዋል። የጭነት አገልጎሎት የሚሰጡ መኪና አሽከርካሪዎችም ሥራ ላለማቆም በእጅ መንሻ ነዳጅ እንደሚቀዱ ይናገራሉ። የነዳጅ ዘይት እጥረት በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ችግር ሆኖ ተስተውሏል። በተለይም ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ አካባቢዎች የነዳጅ ዘይት አቅርቦቱ መቆራረጥ እንደገጠመው እና ለቀናት በነዳጅ ማደያዎች አካባቢ ረዣዥም የመኪና ሰልፎችን መመልከት እየተለመደ መጥቷል። ይህንን የነዳጅ ዘይት መቆራረጥ የዋጋ ጭማሪ መፍትሄይሰጠዋል ተብሎ በሊትር 31 ብር ከሚሸጥበት በአምስት ዓመት ውስጥ 122 ብር ተመን ተቆርጦለታል። ሆኖም ግን ችግሩ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ በነዳጅ ማደያ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ የነገሩኝ የሕዝብ ማመላለሻ መኪና አሽከርካሪ በነዳጅ ዘይት እጥረት ምክንያት ሥራ ለመስራት መቸገራቸውን ይናገራሉ።
‹‹ተሰቃይተናል ከመሰቃየትም በላይ ቀናትን ጠብቀን በስንት ጊዜ ይሰጡናል 2000 (ሁለት ሺ ብር) አውጥተን በስንት መስመር ላይ ሰው እየተሰቃየ በመናኸሪያ ውስጥ ናፍታ የለም ይሉናል። ሁሉም ክፍት ሆኖ የለም ነው የሚሉት።››
አሽከርካሪዎች ቀናትን የነዳጅ ዘይት ለመቅዳት በማደያዎች ይሰለፋሉ
በነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች ለቀናት ተሰልፈውም የእጅ መንሻ በመስጠት የሚገኙ ነዳጅ በረፍ የለሽ የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ ተጠቅመው ከጨረሱም በኋላ በድጋሜ ለሌሎች ተጨማሪ ቀናት በነዳጅ ማደያ ተሰልፈን ነዳጅ እንጠብቃለን የሚሉት አሽከርካሪዎቹ ሠርተን ተገቢውን ክፍያ ማግኘት አልቻልንም ይላሉ።
እጅ መንሻ ነጃጅ ለመቅዳት ተለምዷል
‹‹ብር ሰጥተን (የሻይ) ነው የምናገኘው አለበለዚያ የለም። እንደዚህ ጨምሮ እንኳን አላገኘንም አለ ገብቷል እንባላለን ግን የለም። መስመር እያለን መጠቀም አልቻልንም። እኔ ሊገባኝ አልቻለም። አለ ይባላል እኮ 3 እና 4 ቀንም እንጠብቃለን።››
የነዳጅ ዘይት ከዚህ ቀደም በተረጋጋ የሽያጭ ሁኔታ በየትኛውም አካባቢ ይገዙ እንደነበር ለዶቼቬሌ ሃሳባቸውን ያጋሩ የድንበር ተሻጋሪ መኪና አሽከርካሪ አሁን መንግሥት የዋጋ ጭማሪን በተመለከተ መግለጫ ካለው ነዳጅ የመደበቅ እና ወደ ጎረቤት ሃገራት አሳልፎ የመሸጥ ተግባር ተበራክቶ ይታያል ይላሉ።
መንግሥት የሚደጉመውን ነዳጅ ሕገወጦች ወደ ጎረቤት ሀገር ይሸጣሉ
‹‹ማደያ ውስጥ አሁን መንግሥት ሌብነት ለማስቀረት ይሰራል። ግን እያንዳንዱ ማደያ ወደ ጎረቤት ሀገር ያሻግራል። ነዳጁን መንግሥት ይደጉማል የሚደጎመውን ወደ ጎረቤት ሀገር ስለሚያሻግሩት መንግሥት ደግሞ በኮታ አደረገው።››
የነዳጅ ዘይት በሚቀጥሉት ጊዜያት የዋጋ ጭማሪ ሊያደርግ ይችላል በሚል የሚደብቁም የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች መኖራቸውን ነው አሽከርካሪዎቹ የሚናገሩት።
‹‹የነዳጅ ክምችት በሀገሪቱ ውስጥ አለ ከዲፖ እስከ ግለሰብ ግን መንግሥት በሚናገረው የነዳጅ መረጃ ማደያዎች ነዳጁን ይይዙታል።››
ከዚህ ቀደም የነዳጅ ዘይት መሸጫ ማደያ ባቤቶች በቀጥታ ሽያጭ ገንዘብ በከፈሉበት ዕለት የነዳጅ አመላላሽ ቦቴዎቻቸውን ነዳጅ ቀድተው ከጅቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ ይንቀሳቀሱ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ከ15 እና ከዚያ በላይ ቀናትን በጂቡቲ ወረዳ ይዘው ለማሳለፍ እንደተገደዱ ይናገራሉ። «‹ገንዘብ ከፍለን በወቅቱ አይመጣልንም። በፊት ባዘዝንበት ሰዓት ወዲያው ነበር የሚመጣልን አሁን ግን ከፍለን ከ15-20 ቀን እንጠብቃለን።››
በአማራ ክልል ደቡብ እና ሰሜን ወሎ አካባቢዎች ከሰሞኑ የነዳጅ ዘይት አቅርቦት መቆራረጥ የፈጠረው ተፅዕኖ በርካታ አሽከርካሪዎችን ከሥራ ውጭ ለቀናት ቢያደርጉም እንደ ደሴ ያሉ ከተሞች ግን የሚመጣውን ነዳጅ ዘይት ለበርካታ ወረዳዎች ጭምር የሚያደርሱ በመሆኑ ችግሩ እየጎላ መምጣቱን አቶ ዮናስ እንዳለ የደሴ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ይናገራሉ።
‹‹ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ ነው፤ ጨምሯል፤ እስከዛሬ ድረስ ሁለት ሦስት ማደያ ላይ ካለ ይበቃ ነበር። አሁን አራትም አምስትም ማደያ ኖሮ ከፍተኛ ሰልፍ ነው ያለው በዙሪያው ያሉ ወረዳዎች በቂ አቅርቦት እየቀረበላቸው አይደለም። በተጨማሪም ከፍተኛ የልማት ፍላጎት አለ። በቀን እስከ 10,000 ሊትር የሚወስዱ ፕሮጀክቶች አሉ። ፍላጎቱ ከፍተኛ ሆኗል፤ አቅርቦቱ ግን እንደ በፊቱ አይደለም።››
አሁን ላይ ከነዳጅ ዘይት አቅርቦት መቆራረጥ ጋር ተያይዞ የሚቆሙ መኪናዎች እየተበራከቱ መጥተዋል። በዚህ ዜና ላይም የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊን ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካልንም።
ኢሳያስ ገላው
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ