የነሐሴ በዓላት ማጠናቀቂያ በአማራ ክልል
ሰኞ፣ ጳጉሜን 3 2017የፍልሰታ ጾምን መጠናቅቀ ተከትሎ በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች፣ በተለይ በሴቶች የሚዘወተሩ ባህላዊ ጨዋታዎችና ዜማዎች ይሰማሉ፡፡ አሸንድዬ፣ ሻደይ፣ ሶለን፣ ቡሔ፣ እንግጫ ነቀላ፣ አንሰርቴ፣ ከሴ አጭዳና ሌሎችም ባህላዊና ሀይማኖታዊ በዓላት በሰሜን ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በዋናነት በሴቶች በድምቀት የሚከበሩ በዓላት ናቸው፡፡
ሴቶች በነኚህ የዝግጅት ወቅቶች በባህላዊ አልባሳት አጊጠውና አሸብርቀው በነትፃነት የሚንቀሳቀሱበትና “ፍፁም ነፃነት” የሚያገኙበት የጨዋታ ጊዜያቸው እንደሆነ ይነገራል። የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ በዓላቱ የአሮጌውን ዓመት መጠናቀቅና የአዲሱን ዓመት መግቢያ ማሳያዎች እንደሆኑ ነው ያስረዱት፡፡
“በዓላቱ የነሀሴ ወር ስጦታዎች ናቸው” የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ
“ ...የኢትዮጵያውያን ዘመን መቁጠሪያ ብቸኛ ጌጥ በሆነችው 13ኛዋ ወር ጳጉሜን የሚከበሩ በርካታ ክብረ በዓላት አሉ፣ በዓላቱ የነሀሴ ወር ፀጋዎችና ስጦታዎች፣ የማህበረሰቡ የተስፋ ማሳያዎችና የአዲስ ዓመት መቀበያ ደወሎች ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡
ወጣቶች ከነሀሴ አጋማሽ ጀምሮ በባህል አልባሳት አጊጠው በልዩ የፀጉር አሰራር ተውበው በየአካባቢያቸው ማክበራቸውን ያስታወሱት አቶ መልካሙ፣ ይህም ባህሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሽጋግር ያግዛል ብለዋል፡፡
“የባህል እሴቶች ለቀጣዩ ትውልድ ይሸጋገራሉ” ነፊሳ አል መሐዲ
በአገሪቱ የሚገኙ ህዝቦች በባህል፣ በአኗኗርና በመስተጋብር ግንኙነታቸው ጠንካራ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የየፌደራሉ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ነፊሳ አል መሐዲን ናቸው፣ ባህላዊ እሴቶች ለቀጣዩ ትውልድ ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲዝልቁ በጥና የተደገፈ ሥራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል፡፡ በዓላቱ በስፋት በሴቶችና በልጃገረዶች እንደሚከበሩ ያወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ይህም የሴቶችን መብት ከሚያረጋግጡ ሁነቶች መካከለ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
የፌደራል ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ ዶ/ር እንደገና አበበ በበኩላቸው የባህልና የቱሪዝም ህብቶች ለእይታ ብቻ ሳይሆን ትሩፋትም እንዲሆኑ እንደሚሰራ ገልጠዋል፡፡
“ሀብቶቹን ከአቧራ ወደ አሻራ ቅይርናቸዋል” ዶ/ር እንደገና አበበ
ባህልና ቱሪዝም ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው መስኮች ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ አገርም ማደግ የሚችለው ሁለቱ መስኮች ሲያድጉና ትኩረት ሲሰጣቸው እንደሆነ ገልጠዋል፡፡ እነኚህን ሀብቶች “ከአቧራ ወደ አሻራ ቀይረናቸዋል”፡ ብለዋል፡፡ አክለውም ሀብቶች “ለእይታ ብቻ ሳይሆን ቱርፋትም እንዲሆኑ ይሰራል” ነው ያሉት፡፡
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ተወላጅ የሺዓለም ጌታነህ ለዶይቼ ቬሌ እንዳችው “ ሻደይ ሴቶች በነፃነት የሚያከብሩት የልጃገረዶች በዓል ነው፣ በዚህም ደስታ ይሰማናል” ብላለች፡፡ አንዱ የሌላውን ባህል እንዲያውቅ በጋራ መከበሩም ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ነው የነገርችን፡፡
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ