ደሴ በባቲ ከተማ ሰዓት እላፊ ተጣለ
በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የባቲ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት፣ በአካባቢዉ ይንቀሳቀሳሉ የተባሉ ታጣቂዎችን ለመቆጣጠር ፣ ክልከላዎችን መጣሉን አስታወቀ። በዚሁ መሠረት ማንኛዉም ሰዉ ከምሽቱ 4:00 ሰዓት በኋላ በከተማው ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ተከልክሏል ፤ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎትም ከ12 ሰዓት በኃላ ታግዷል ሲል ኢሳያስ ገላው ዘግቧል። መንግስት ኦነግ ሸኔ ሲል የሚጠራው ቡድን በአካባቢዉ ይንቀሳቀሳል ሲሉ ነዋሪዎች ለዶቼቬለ ተናግረዋል። በከተማዋ አቅራቢያ ባሉ የገጠር ቀበሌዎች ታጣቂዎች እንደሚንቀሳቀሱና የከተማዋ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ለጥቃት እንደሚጋለጡ ነዋሪዎች ለዶቼቬለ ተናግረዋል። በባቲ ከተማ የሰዓት እላፊ እንቅስቃሴ ገደብ ባለፉት 2 ዓመታት በተደጋጋሚ ይጣል እንደነበር የተናገሩት አንድ የከተማው ነዋሪ የትራንስፖርት እና የሰው እንቅስቃሴ መገደቡ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮብናል ብለዋል፡፡
በባቲ ከተማ የሰዓት እላፊ ገደብ የተጣለው የከፋ ነገር ተፈጥሮ ሳይሆን አንዳንድ አመላካች ጉዳዮች ለሥጋት ስለዳረጉን ነው ሲሉ የባቲ ከተማ ከንቲባ አቶ አብዱ አህመድ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድንም የተደራጀ እና አቅም ያለው አይደለም ያሉት ከንቲባው ማህበረሰቡን ለሥጋት የሚዳርግ ምንም ችግር የለምም ብለዋል።
‹‹በቁጥጥር ስር ያደረገው ቀበሌ የለውም፤ ተደራጅቶ ኃይል ሲመጣበት የሚገጥምም አይደለም፤ አምስት ሁለት እየሆኑመንገድ ላይ ይሹለከለካሉ፤ እየተደበቁ ይህንን ያህል የሚያስፈራ አይደለም፤ አሁን ወቅቱ ክረምት በመሆኑ አረንጓዴ መልበስ ስላለ ለዚያ ብለን ነው እንጂ የከፋ ነገር የለውም፡፡››
ገደቡም ለጥቂት ጊዜ ብቻ የሚቆይ ነው ሲሉም የባቲ ከተማ ከንቲባ ተናግረዋል።
ለንደን ኢትዮጵያ ተገን ጠያቂ በወሲባዊ ጥቃት ጥፋተኛ ተባለ
አንድ የብሪታንያ ፍርድ ቤት በአንዲት ሴትና በአንዲት የ14 ዓመት ልጃገረድ ላይ ወሲባዊ ጥቃት በመፈጸም በተጠረጠረው አንድ ኢትዮጵያዊ ተገን ጠያቂ ላይ የጥፋተኝነት ብይን አሳለፈ። ትናንት ያስቻለው የምሥራቅ ለንደኑ የቼልምስፎርድ ማጂስትሬት ፍርድ ቤት አንድ ዳኛ ተጠርጣሪውን ሀዱሽ ገብረ ሥላሴን በሁለት የወሲባዊ ጥቃት የክስ ጭብጥና በአንድ የወሲብ ጥቃት ለመፈጸም በመሞከር የክስ ጭብጥ አንዲሁም ልጃገረድን ለወሲብ ድርጊት በማነሳሳት የክስ ጭብጥ እና ጥቃት-አልባ ወሲባዊ ትንኮሳ በመፈጸም የጥፋተኛነት ውሳኔ አሳልፈዋል። የ41 ዓመቱ ሀዱሽ በአነስተኛ ጀልባ ብሪታንያ ከገባ ከሳምንት በኋላ ኤፒንግ በተባለ ከተማ ውስጥ አግዳሚ ወንበር ላይ የተቀመጠች አንዲትየ14 ዓመት ልጃገረድን ለመሳም መሞከሩን እጁንም ጭኗ ላይ በማድረግ ፀጉሯን መዳበሱን አቃቤ ሕግ ተናግሯል ። ከዚህ ሌላ የህይወት ታሪኩን የስራ ልምዱንና የትምህርት ደረጃዎቹን ማስረጃዎች በጽሁፍ በመሰነድ ልትረዳው ፈቃደኛ የነበረች አንዲት ሴት ላይም ተመሳሳይ የወሲብ ጥቃት መፈጸሙንም አስረድቷል። ተከሳሹ ሀዱሽ ግን የቀረቡበትን ክሶች በሙሉ አልተቀበለም። ዳኛው ተገን ጠያቂው ኢትዮጵያዊ ላይ በመጪው መስከረም 19 ቀን 2018 ዓም ብይን እንደሚሰጡ ተናግረዋል። ስደተኛው ወሲባዊ ጥቃት መፈጸሙ ከተዘገበ በኋላ በኤፒንግ እና በሌሎችም ከተሞች ቀኝ አክራሪዎችም የተሳተፉባቸው የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄዱ ቆይተዋል ። በአንጻሩ ተቃዋሚዎቹን በቁጥር የሚበልጡ የስደተኞች ደጋፊዎች የተካፈሉባቸው ሰልፎችም ተካሂደዋል። የብሪታንያ መንግስት ለተገን ጥያቄአቸው ውሳኔ የሚጠብቁ ስደተኞችን ሆቴሎች ውስጥ ማቆየቱ በብሪታንይ ውጥረቱን አባብሶታል። ስደተኞቹን ሆቶሎች ውስጥ ማስቀመጡ ግብር ከፋዩን ህዝብ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ፓውንድ ያስወጣሉ የሚለው ትችት ኅብረተሰቡ በስደተኞች አያያዝ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ አድርጓል። ስደተኞችም በየሚኖሩበት አካባቢ ዒላማ ውስጥ እንደገቡ ይሰማቸዋል።
ጄኔቫ RSF በሱዳን በሰብዓዊነት ላይ ወንጀሎችን ፈጽሟል
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በምህጻሩ RSF በሱዳኑ የርስ በርስ ጦርነት ሰብዓዊነትን የሚጻረሩ በርካታ ወንጀሎችን ፈጽመዋል ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርማሪዎች አስታወቁ።መርማሪዎቹ ዛሬ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት ወንጀሎቹ የተፈጸሙት በተለይ በምዕራብ ዳርፉሩ በኤል ፋሸር ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለሱዳን ሀቅ አፈላላጊ ተልዕኮ ባወጣው አዲስ ዘገባ RSF በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል ፈጽሟል፤ በተለይም ግድያ፣ ቁም ስቅል ማሳየት ፣ የግዳጅ ማፈናቀል፣ ጎሳን መሰረት ያደረገ ማሳደድ እና ሌሎች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች መፈጸማቸውን ዘርዝሯል።
በምርመራቸው ውጤትም በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተገደሉበት በሱዳኑ ግጭት ተካፋይ በሆኑት ሁለቱም ወገኖች ማለትም በመደበኛው ጦር ሠራዊትና በRSF የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸውን የሚያሳይ ማስረጃም ማግኘታቸውንም አስታውቋል። በግኝታችን ሰላማዊ ሰዎች በጦርነቱ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ መሆኑ አያጠራጥርም ሲሉ የተልዕኮው ሃላፊ መሐመድ ቻንዴ ኦትማን ባወጡት መግለጫ ተናግረዋል። ሃላፊው የደረሱት ድንገት የተከሰቱ አደጋዎች ሳይሆኑ፣ ይልቁንም በስልት ሆነ ተብሎ የተወሰዱ እስከ ጦር ወንጀል የሚደርሱ ጥቃቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል። መርማሪዎቹ ለደረሱት የጦር ወንጀሎች ሁለቱንም ወገኖች ተጠያቂ ቢያደርጉም በተለይ ግን ከግንቦት አንስቶ በከበባት በኤልፋሸር የRSFን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት አጉልቷል። በዚህም ቡድኑ ኤልፋሸርንና አካባቢውን ከቦ በቆየናቸው ጊዜያት የተፈጸሙት ግድያ፣ ማሰቃየት፣ እንደ ባሪያ መያዝ ፣አስገድዶ መድፈር፣ የወሲብ ባሪያ ማድረግ እና የወሲብ ጥቃቶች በሰብዓዊነት ላይ ከፈጸማቸው ወንጀሎች ውስጥ ተካተዋል። RSF እና አጋሮቹ ህዝቡን ማስራብንና መድኃኒትና በሕይወት ለመቆየት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችንም መከልከልን እንደ አንድ የጦርነት ስልት እንደተጠቀሙም መርማሪዎቹ ዘግበዋል።
በርሊን ጀርመን ለአፍጋኒስታን የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሰለባዎች 2.1 ሚሊዮን ዩሮ እርዳታ ልትሰጥ ነው
ጀርመን ለአፍጋኒስታን የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሰለባዎች የ2.1 ሚሊዮን ዩሮ እርዳታ እንደምትሰጥ አስታወቀች። ይህም ከከባዱ የአፍጋኒስታን የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በኋላ ጀርመን የምትሰጠው የአጭር ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ መሆኑን የጀርመን ዜና አገልግሎት DPA ዘግቧል። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዛሬ በርሊን ውስጥ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የገንዘብ እርዳታው በመሬት መንቀጥቀጡ ለተጎዱት ፣ለምግብ ለመጠጥ ውኃ ለአስቸኳይ መጠለያዎች ለንጽህና መጠበቂያዎች እና ለሕክምና አገልግሎት የሚውል ነው። ገንዘቡም ለአፍጋኒስታኑ የታሊባን መንግሥት ሳይሆን ለዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የሚሰጥ መሆኑን አስታውቀዋል። ይፋ በአሁኑ የቅርብ ጊዜ አሀዛዊ መረጃዎች መሠረት ባለፈው እሁድ በሀገሩ ሰዓት አቆጣጠር እኩለ ለሊት አካባቢ ምስራቅ አፍጋኒስታንን በመታው የመሬት መንቀጥቀጥ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 2 ሺህ 200 ደርሷል። 3640 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
ጄኔቫ የአፍሪቃው የኤም ፖክስ ወረርሽኝ ለዓለም አስጊ አይደለም ተባለ
በአፍሪቃ የተከሰተው የኤምፖክስ ወረርሽኝ ከአሁን በኋላ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት አይደለም ሲል የዓለም የጤና ድርጅት አስታወቀ። የድርጅቱ ሃላፊ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሽታው በወረርሽኝ መልክ ከተከሰተ በኋላ የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ ኮሚቴ፣ ሁኔታው ከአሁን በኋላ የአፍሪቃው የኤምፖክስ ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት እንዳይደለ እንደመከራቸውና እርሳቸውም ምክሩን መቀበላቸውን ተናግረዋል። ይሁንና ዶክተር ቴዎድሮስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ፣ስጋቱ የለም ማለት እንዳይደለና በሽታውን በተመለከተም የድርጅታው ምላሽ እንደማይቆም ተናግረዋል። ኤምፖክስ በተህዋሲ አማካይነት የሚመጣ በሽታ ነው። የሚተላለፈውም የግብረ ስጋ ግንኙነትን ጨምሮ በቅርብ ንክኪዎች ነው ። የዓለም የጤና ድርጅት ኤምፖክስን ዓለም አቀፍ አስቸኳይ የጤና ስጋት ሲል ባለፈው ዓመት ነሐሴ አውጆ ነበር።
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ