የነሐሴ 25 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ነሐሴ 25 2012ሊዮኔል ሜሲን ከባርሴሎና መውሰድ የሚፈልግ ቡድን የውል ማፍረሻ 700 ሚሊዮን ዩሮ የመክፈል ግዴታ ተጥሎበታል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ጀርመናውያን አሽከርካሪዎች ከባድ ሽንፈት ገጥሟቸዋል፤ የመርሴዲስ ደጋፊዎች ፈንጥዘዋል። የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታውን በዚህ ሳምንት ከስፔን ጋር ያከናውናል።
ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በጀርመን የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች
ፖላንዳዊው የባየር ሙይንሽን አጥቂ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በሰፋ የድምፅ ብልጫ የዘንድሮ የጀርመን እግር ኳስ ኮከብ ተብሎ ተመረጠ። ኪከር መጽሄት ትናንት ይፋ እንዳደረገው ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ የስፖርት ጋዜጠኞች በሰጡት ድምፅ 276 በማግኘት አሸናፊ ኾኖ ተመርጧል። የቡድን አጋሩ ቶማስ ሙይለር 54 ድምፅ በማግኘት ኹለተኛ ወጥቷል። ዮሹዋ ኪሚሽ 49 ድምጽ አግኝቶ ሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል።
የ32 ዓመቱ አጥቂ በተጠናቀቀው የቡንደስሊጋ ጨዋታ ክፍለ ጊዜ 34 ግቦችን በጀርመን ዋንጫ ስድስት እንዲሁም በሻምፒዮንስ ሊግ 15 በማስቆጠር ኮከብ ግብ አግቢነቱን ያስመሰከረ ምርጥ አጥቂ ነው። የውጭ ሃገር ተወላጅ እንዲህ አይነቱን ሽልማት ሲያሸንፍ ከአምስት ዓመት ወዲህ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ የመጀመሪያው ነው። እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ2015 ኬቪን ደ ብሩዌይነ የመጀመሪያው የውጭ ሃገር ተወላጅ አሸናፊ መኾን ችሎ ነበር።
የባየር ሙይንሽኑ አሰልጣኝ ዲተር ሐንስ ፍሊክ የጀርመን የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ተብለው ተመርጠዋል። የ55 ዓመቱ አሰልጣኝ የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬይርገን ክሎፕን በልጠው ነው ምርጥ አሰልጣኝ ተብለው የተመረጡት።
ቶማስ ሙይለር ወደ ብሔራዊ ቡድኑ?
ከሻምፒዮንስ ሊግ ድል በኋላ በርካታ የጀርመን እግር ኳስ ባለሞያዎች ቶማስ ሙይለር ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ቢመለስ ይጠቅማል በማለት ላይ ናቸው። የቶማስ ሙይለር ወደ ቀድሞ ብቃቱ መመለስን የጀርመን እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኦሊቨር ቢይርሆፍም እንደሚያደንቅ ትናንት ባደረገው ቃለመጠይቅ ዐስታውቋል። ኦሊቨር የአጥቂው ብቃት መመለስን እንደሚያደንቅ ግን ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ለመመለስ ወሳኙ አሠልጣኙ መኾናቸውን ዐስታውቋል።
የቀድሞው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ የ52 ዓመቱ ኦሊቨር ቢይርሆፍ፦ «በእግር ኳስ አይኾንም ማለት አትችልም፤ ግን አኹን ትኩረታችን ወጣቶች ላይ ነው» ሲልም ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረገው የቪዲዮ ቃለመጠይቅ አክሏል። ብሔራዊ ቡድኑ ወጣት ተጨዋቾችን ሰብስቦ ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች እስካሁን ውጤታማ መኾኑን ይኽን ውጤት ይዘው መቀጠል እንደሚሹም ጠቅሷል። ይኹንና፦ «አሰልጣኙ አስፈላጊ በሚኾንበት ጊዜ ቶማስ ሙይለርን ሊጠራው ይችል ይኾናል» ብሏል።
ምናልባትም የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮኣኺም ሎይቭ ቶማስ ሙይለርን ቡድናቸውን እንዲቀላቀል ሊጠሩትም ይችሉ ይኾናል። አሰልጣኙ ቡድናቸውን ለዩሮ 2021 ውድድር ማደራጀት የያዙት በብዛት በወጣት ተጨዋቾች ነው።
አሰልጣኙ በወጣት ተጨዋቾች ያደራጁት ብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ግጥሚያውን የፊታችን ሐሙስ ሽቱትጋርት ከተማ ውስጥ ከስፔን ጋር ያከናውናል። በዚህ የወዳጅነት ግጥሚያ የሚሰለፉ 11ዱ ተጨዋቾች በአብዛኛው 24 እና 26 ዓመታቸው አለያም ከዚያ በታች ነው። የሪያል ማድሪድ አማካይ ተጨዋች ቶኒ ክሮስ ብቻ 30 ዓመቱን ደፍኗል። ከብሔራዊ ቡድኑ ዋና ተሰላፊዎች መካከል ኹለቱ ግብ ጠባቂዎች 30 ዓመታቸውን የያዙ ሲኾን፤ የአርሰናሉ ቤርንድ ሌኖ 28 ዓመቱ ነው። ከአማካዩ ቶኒ ክሮስ ጋር ተመሳሳይ ዕድሜ ላይ የሚገኘው አጥቂ ቶማስ ሙይለር ምናልባትም ወደ ብሔራዊ ቡድኑ የመመለስ ዕድል ይኖረው ይኾናል።
የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ከባድ ሽንፈት ገጥሞት ከውድድሩ ከወጣ በኋላ ነበር ቶማስ ሙይለር ከቡድኑ የተሰናበተው። አሰልጣኝ ዮአኺም ሎይቭ በወቅቱ ከቶማስ ሙይለር በተጨማሪ ጄሮም ቦኣቴንግ እና ማትስ ሑመልን የመሳሰሉ የዓለም ዋንጫ በማስገኘት በቡድኑ ቆየት ያለ ልምድ ያካበቱ ተጨዋቾችንም አልማሩም።
ባየር ሙይንሽን በሻምፒዮንስ
በዘንድሮ የጨዋታ ክፍለጊዜ ሦስት የተለያዩ ወሳኝ ዋንጫዎችን በእጁ ያስገባው ባየር ሙይንሽን ለቀጣዩ የቡንደስሊጋ ውድድር ከወዲሁ ዝግጅቱን አጠናቋል። ባየር ሙይንሽን ከሦስት ሳምንት በኋላ ለሚጀምረው የቡንደስሊጋ አዲስ ውድድር ተጨዋቾቹ በሚቀጥለው ሳምንት የኮሮና ምርመራ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፏል። ከምርመራው ኹለት ቀናት በኋላም መስከረም አንድ ቀን 2013 ዓም የቀጣይ ዘመን የቡንደስሊጋ ውድድሩን በይፋ እንደሚጀምር ዐስታውቋል። መስከረም 7 ቀንም በቡንደስሊጋው ከሻልከ 04 ጋር የመጀመሪያ ግጥሚያውን ያከናውናል።
ባየር ሙይንሽን በሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜው ፓርሲ ሴንጀርማን 1 ለ0 ባሸነፈበት የፖርቹጋሉ ዋና ከተማ ሊዝቦን አብዛኞቹ ተጨዋቾቹ የረፍት ጊዜያቸውን እያሳለፉ ነው። ኒክላስ ሱሌ እና ሌሮይ ሳኔ ብቻ ለብሔራዊ ቡድኑ ባለባቸው ግዴታ ጀርመን ቀርተዋል።
ይኽ በእንዲህ እንዳለ፦ አሰልጣኝ ሐንስ ዲተር ፍሊክ እስኪተኳቸው ድረስ ባየር ሙይንሽንን አሰልጥነው ቡድኑ ከባድ ሽንፈት ሲደጋገምበት የተባረሩት አሰልጣኝ ኒኮ ኮቫች በፈረንሳይ ሊግ አንድ ውጤት ቀንቷቸዋል። ኒኮ ኮቫች የያሰለጥኑት ሞናኮ በኹለተኛ ዙር የፈረንሳይ ሊግ ግጥሚያው ሜትዝን 1 ለ0 አሸንፏል። ከሳምንት በፊት የሊጉ ውድድር በአዲስ መልክ በጀመረበት ወቅት የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን ከሬሚ ጋር አከናውነው ኹለት እኩል ነበር የተለያዩት። ኒኮ ኮቫች ከባየር ሙይንሽን ከተሰናበቱ ከጥቂት ወራት በኋላ ሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ ነበር የሞናኮ አሰልጣኝ እንደኾኑ የተገለጠው።
ሊዮኔል ሜሲ
አርጀንቲናዊው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ ረዥም ዘመን ከቆየበት ባርሴሎና ፍቺው እንዲፋጠን ጫና በማሳደር ላይ ይገኛል። ሊዮኔል ሜሲ ቡድኑ በጀርመኑ ባየር ሙይንሽን በሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ 8 ለ2 ከተሰናበተ በኋላ እሱም ከልጅነት ቡድኑ በፍጥነት እንዲያሰናብቱት እየወተወተ ነው። ከባርሴሎና ጋር ገና የአንድ ዓመት ተጨማሪ ውል ቢኖረውም በቡድኑ ፈጽሞ መቆየት አለመፈለጉን ባገኘው አጋጣሚ እያሳየ ነው።
ትናንት የባርሴሎና ተጨዋቾች በነበራቸው የኮሮና ተሐዋሲ መለያ ምርመራ ላይ እንደማይሳተፍ በአባቱ በኩል ማስታወቊ የባርሴሎና ቡድን ኃላፊዎችን በጣም ነው ያስደነገጣቸው። ምርመራውን አድርጎ ነፃ መኾኑ ካልታወቀ በዛሬው ልምምድ መሳተፍ እንደማይፈቀድለት እያወቀም ነው ምርመራውን ማድረግ አለመፈለጉን ያስታወቀው።
ሊዮኔል ሜሲን ከባርሴሎና ጋር የገባው ውል ሳይገባደድ መውሰድ የሚፈልግ ቡድን ለባርሴሎና 700 ሚሊዮን ዩሮ እንዲከፍል በስፔን ብሔራዊ የአንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር በአጭሩ ላሊጋ ግዴታ ተጥሎበታል። ከዚያ ባሻገር ሜሲ 250 ሚሊዮን ዩሮ በእጁ እንዲገባ ይሻል።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቊሙት ከኾነ የ33 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ ወደ ጁቬንቱስ አቅንቶ ከሌላኛው የዓለማችን ምርጥ የእግር ኳስ ተጨዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር ሊሰለፍ ይችል ይኾናል። ኹለቱ ብርቅዬ የእግር ኳስ ተቸዋቾች በአንድ ቡድን ጎን ለጎን ተሰልፈው መመልከት የበርካቶች የእግር ኳስ አድናቂዎቻቸው ምኞትም ነው። ምኞታቸው መቶ በመቶ ዕውን እንዳይኾን ግን ሌሎች ተቀናቃኝ ቡድኖችም የዓለም ምርጡን ተጨዋች ማሰለፍ አጥብቀው ይሻሉ።
ከእነዚህ መካከል ማንቸስተር ሲቲ ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል። ሊዮኔል ሜሲ ባርሴሎናን መልቀቅ እንደሚሻ የባየር ሙይንሽን አሰልጣኝ ለነበሩት የሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ አስቀድሞ ነግሯቸዋል። እሳቸውም የቡድናቸው ኃላፊዎችን ጠቀም ያለ ገንዘብ አውጥተው ሊዮኔል ሜሲን እንዲያስመጡ ለማሳመን ጥረት ማድረጋቸውን ታይምስ ዘግቧል።
የስፔኑ ድረገጽ (sport.es) እንደዘገበው ከኾነ ደግሞ ፔፕ ጋርዲዮላ ሊዮኔል ሜሲን ወደ ማንቸስተር ሲቲ ለማስመጣት 100 ሚሊዮን ዩሮ መክፈል ብቻ ሳይኾን ሦስት ምርጥ ተጨዋቾቻቸውንም ወደ ባርሴሎና መላክ ግድ ይላቸዋል። እነዚህ ሦስቱ ምርጥ ተጫዋቾችም፦ የ19 ዓመቱ ኤሪክ ጋርሺያ፤ በ50 ሚሊዮን ዩሮ የተገዛው ቤርናርዶ ሲልቫ እንዲሁም ብራዚላዊው ጋብሬል ጄሱስ ናቸው። እንደዘገባው ከኾነ እነዚህ ሦስት ምርጥ ተጨዋቾች ሊዮኔል ሜሲን ለማስመጣት ከባርሴሎና ጋር በሚኖረው ውል መሠረት በቅርቡ ስፔን ይታያሉ።
የፈረንሳዩ ፓሪስ ሳንጀርማ ቡድንም ሊዮኔል ሜሲ ላይ ዐይናቸውን ከጣሉ ቡድኖች ዋነኛው ነው። እዚያ በእርግጥ የሀገሩ ልጅ አጥቂው ዲ ማሪያ እና ሌላኛው ወዳጁ የቀድሞ የባርሴሎና ተሰላፊ ኔይማርም ይገኛሉ። እነዚህ ኹለት የባርሴሎና ተጨዋቾች ወዳጃቸው ሊዮኔል ሜሲ ቡድናቸውን እንዲቀላቀል የማግባባት ሥራ እየሠሩ ነው ሲል ሙንዶ ዲፖርቲቮ ዘግቧል።
ፎርሙላ አንድ
በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የፌራሪ አሽከርካሪዎች ያልተጠበቀ ደካማ ውጤት አስመዝግበዋል። የመርሴዲስ አሽከርካሪው ሌዊስ ሀሚልተን ፈርሽታፓንን በ47 ነጥብ ይመራል። እስካኹን 157 ነጥብ የሰበሰበ ሲኾን፤ ማክስ ፈርሽታፓን 110 ነጥብ አለው። ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ቫለሪ ቦታስ በ107 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል። ጀርመናውያኑ የፌራሪ አሽከርካሪ ሠባስቲያን ፌትል እና የሬሲንግ ፖይንት አሽከርካሪው ኒኮ ሑውይልከንበርግ 13ኛ እና 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ