የትግራይ የኢኮኖሚ ኪሳራና የስምምነቱ ተስፋ
ረቡዕ፣ ኅዳር 14 2015የኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት በሰዉ ሕይወት፣ አካል፣ ኑሮና ስነልቡና ላይ ካደረሰዉ ጥፋት በተጨማሪ ከፍተኛ ምጣኔ ሕብት ቀዉስ ማስከተሉ በተደጋጋሚ እየተነገረ ነዉ።የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ እንዳስታወቀዉ ጦርነቱ ያጠፋዉ ንብረት በትንሽ ግምት ከ20 ቢሊዮን ዶላር ይበልጣል።ይሁንና የተለያዩ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች እንደሚሉት ጦርነቱ ያደረሰዉ የምጣኔ ሐብት ኪሳራ በቅጡ ቢጠና መንግስት ከመገመተዉ በእጅጉ ይበልጣል።የመቀሌዉ ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለ ስላሴ ያነጋገራቸዉ ባለስልጣናትና ሰራተኞች እንደሚሉት ደግሞ ትግራይ ዉስጥ ብቻ የደረሰዉ የኤኮኖሚ ኪሳራ በሰራተኞችና በቤተሰቦቻቸዉ ላይ ያሳደረዉ ጫና ሲበዛ ከባድ ነዉ።
በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ አምራች ኢንዳስትሪዎች ወድመዋል፣ ስራ አቁመዋል፣ ሰራተኞቻቸውን በትነዋል። እንደ የትግራይ ኢንቨስትመንት እና ኤክስፖርት ኮምሽን መረጃ በጦርነቱ ምክንያት ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑ በኢንዳስትሪው ዘርፍ ባሉ የስራ ዓውዶች የነበሩ ሰራተኞች ከስራ ውጭ ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪ ጦርነቱ 12 ሺህ ገደማ የሚሆኑ በትግራይ የነበሩ ፍቃድ ያገኙ የተለያየ ደረጃ ያላቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች በአብዛኛው ስራ ማቆማቸው የክልሉ አስተዳደር መረጃ ያመለክታል። ከጦርነቱ በተጨማሪ የመሰረተ ልማት ውድመት፣ የባንክ ጨምሮ የተለያዩ የህዝብ አገልግሎቶች፣ የነዳጅ ጨምሮ የተለያዩ አቅርቦቶች እጦት በትግራይ ዜጎች ከኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲገደቡ አድርጓቸዋል።
የ29 ዓመቱ ወጣት ዳዊት ካሕሳይ ተምሮ በተመረቀበት የሙያ ዘርፍ መቐለ በሚገኝ የኪብር ትሬዲንግ ማጋርመንት ኢንዳስትሪ ከጦርነቱ በፊት ለነበሩ 7 ዓመታት ስራ ላይ ቆይቷል። ሰርቶ በሚያገኘው ገቢ ራሱን ችሎ ቤተሰቡ ይደግፍ የነበረው ዳዊት፥ ይሰራበት የነበረው የጨርቃጨርቅ አምራች ኢንዱስትሪ በጦርነቱ ምክንያት ስራ በማቆሙ አሁን ስራአጥ፣ ተጧሪ እንዲሆን እንዳደረገው ይገልፃል። ዳዊት "በድርጅቱ እኔን ጨምሮ ከ1 ሺህ በላይ ሰራተኞች ነበርን። አብዛኛው ሰራተኛ በሚያገኘው ደሞዝ ነበር የሚተዳደረው። ስራ ካቆምን እና ደሞዝ አተቋረጠ 16 ወራት አልፈዋል" ይላል።
ዳዊት የመሰሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በትግራይ በነበሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ዜጎች አሁን ስራ አጥ ናቸው። ከጦርነቱ በፊት የነበረ በትግራይ የነበረ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለብዙሃን የስራ ዕድል የፈጠረ፣ ሀገራዊ አበርክቶው የላቀ፣ የውጭ ምንዛሬ በማስገባትም ትልቅ ሚና የነበረው ነው ይላል የትግራይ ኢንቨስትመንት ኮምሽን። የተለያዩ መዓድኖች በተለይም ወርቅ በማቅረብ ትግራይ ትልቅ ሚና ነበራት የሚሉት የትግራይ ኢንቨስትመንት ኮምሽን ምክትል ኮምሽነር አቶ ዳኒኤል መኮንን የአገልግሎት እና ቱሪዝም እንዲሁም አምራች ኢንዳስትሪው ከጦርነቱ በፊት በትግራይ ዕድገት ላይ እንደነበረ ያስረዳሉ። ይሁንና ይህ አሁን ላይ ተቀይሮ በትግራይ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወድመዋል፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተገድቧል፣ ሰራተኞች ስራ አጥ ሆነዋል ይላሉ ምክትል ኮምሽነሩ አቶ ዳኒኤል።
በሁለት ዓመቱ ጦርነት ምክንያት በትግራይ ኢኮኖሚ ዘርፍ የደረሰው አጠቃለዋል ኪሳራ፣ በኢንዳስትሪው የደረሰ ውድመት በዝርዝር ለማወቅ ጥናት እየተካሄደ መሆኑ የሚገልፁት ባለስልጣኑ፣ ባለው ዳሰሳ ግን በሀገር ውስጥ እና ውጭ ሀይሎች በትግራይ የነበሩ ታላላቅ ኢንዱስትሪዎች ላይ ዘረፉ መፈፀሙ ውድመት መድረሱ ይናገራሉ።
በቅርቡ የተፈጠረው የሰላም ዕድል በኢኮኖሚው አወንታዊ ውጤት ሊፈጥር ዜጎች ይጠብቃሉ። የትግራይ ኢንቨስትመንት ኮምሽን በበኩሉ በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ የደረሰው ውድመት ለማቃለል ትግራይ ከኢትዮጵያ መንግስት ልዩ የድጋፍ ማዕቀፍ እንደምትጠብቅ ይገልፃል።
ሚሊዮን ኃይለ ስላሴ
ነጋሽ መሐመድ