የትግራይ ክልል ኃይል አዛዦች ውሳኔ የገጠመው ተቃውሞ
ዓርብ፣ ጥር 16 2017
የትግራይ ክልል ኃይል አዛዦች ያስተላለፉትን ውሳኔ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አወገዙት። ሁለት መቶ ገደማ የሚሆኑ የትግራይ ሐይሎች አዛዦች በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ እውቅና በመስጠት፥ በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ያለው ሃምሳ ሲደመር አንድ ድርሻ እንዲረከብ እንደሚሹ መግለፃቸው ተከትሎ የፖለቲካ ውጥረቱ ተባብሷል።
ሁለት መቶ ገደማ የሚሆኑ የጀነራል እና ኮሎኔል መአርግ ያላቸው የትግራይ ሐይል አዛዦች ትላንት በሰጡት መግለጫ በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ለሚመራ የህወሓት ክንፍ እውቅና በመስጠት፥ ግዚያዊ አስተዳደሩ እንዲረከብ እንደሚደግፍ ማስታወቃቸው ተከትሎ ፖለቲካዊ ውጥረቱ ወደባሰ ሁኔታ ተሸጋግሯል። የጦር መኮኑኖቹ መግለጫ ተከትሎ በበርካቶች ነዋሪዎች ዘንድ ግጭት እንዳይፈጠር የተሰጋ ሲሆን የዚህ ማሳያ ደግሞ ነዋሪዎች ከባንክ ገንዘብ ማውጣት ጨምሮ ሸቀጦችን መሸመት በበርካቶች ዘንድ ይስተዋላል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሦስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የትግራይ ክልል ኃይሎች አዛዦች ውሳኔን አውግዘዋል።
"ካልቻሉ አሁን ከስልጣን መልቀቅ አለባቸው" ተቃዋሚዎች
ዛሬ መግለጫ የሰጡት የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ እንዲሁም ባይቶና የትግራይ ኃይሎች ወታደራዊ መኮንኖች ወደ ፖለቲካ እጅ በማስገባት ስልጣን የመቆጣጠር አልያም ስልጣንን ለሚፈልጉት ኃይል አሳልፎ የመስጠት እንቅስቃሴ ላይ ናቸው በማለት አውግዘዋል። የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ደጀን መዝገበ እንዳሉት፥ የጦር አዛዦቹ የግል ጥቅማቸውን ለማረጋገጥ በትግራይ ወታደራዊ ስርዓት የመትከል ፍላጎት አላቸው በማለት ይህንኑ ኮንነዋል።
ዶክተር ደጀን "ለዓለም ምን ዓይነት መልእክት እያስተላለፉ እንዳለ፣ ለትግራይ ህዝብ ምን ዓይነት ችግር ይዘው እየመጡ እንዳለ እየገባቸው አይደለም። አንድ እና አንድ እነሱ ጋር ያለው ፍላጎት ቡድናዊ ጥቅም ለማስቀጠል ስልጣን ላይ መቆየት በመሆኑ፥ ፍፁም ወታደራዊ አምባገነናዊ አቋም ይዘው ቀርበዋል። የትግራይ ህዝብ የሚሻው ሲቪል አስተዳደር ነው" ብለዋል።
የባይቶና ከፍተኛ አመራር ዮሴፍ በርሃ በትግራይ ኃይሎች ስም እየተንቀሳቀሱ ያሉት በጦሩ ውስጥ ያሉ የህወሓት ሰዎች ናቸው ብለዋል። አቶ ዮሴፍ በርሃ "በሰራዊቱ ስም መግለጫ እየሰጡ ያሉት እነማን ናቸው ያልን እንደሆነ፥ በሰራዊት ውስጥ ያሉ የህወሓት ክንፍ ነው። በተደጋጋሚም ብለነዋል፥ በተግባርም የምናውቃቸው ናቸው። በሰራዊቱ ውስጥ ያለው የህወሓት ክንፍ በሰራዊት ስም ነው መግለጫ እየሰጠ ያለው። የሰራዊቱ አዛዦች ለሚያምኑት፣ ለሚፈልጉት ነው ስልጣን ይሰጥ እያሉ ያሉት" ሲሉ ገልፀዋል።"አዲስ የትግል አቅጣጫ እንከተላለን" የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን
ከዚህ በተጨማሪ የጦር መኮንኖቹ እንቅስቃሴ ወንጀላቸውን ለመደበቅ ያለመ ነው ሲሉ የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ ተናግረዋል። አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ"እነዚህ አካላት በሰሜን ምዕራብ ዞን በወርቅ እና ኬሚካል እጃቸው ያለበት ናቸው። የተፈጥሮ ሀብታችንን አካባቢያችንን ያወደሙ ናቸው። በሕግ እንዳይጠየቁ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ መቆም አለበት" ሲሉ አክለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወታደራዊ መንግስት ፈፅሞ አንቀበልም ያለው ሌላው ተቃዋሚ ፓርቲ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ በበኩሉ በሐይልም ይሁን በወታደር ታዝሎ ወደ ስልጣን የሚመጣ የፖለቲካ ፓርቲ እንደ ታጣቂ ሐይል ስለምንመለከተው የፓርቲ ግንኙነት እንደማይኖረው ገልጿል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፈርሶ እንደ አዲስ ይቋቋም ጥሪ
ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ክልል ኃይል አዛዦች ያስተላለፉት ውሳኔ ተከትሎ አስቸኳይ የካቢኔ ስብሰባ መጥራቱን የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ትላንት ማታ አስታወቋል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የትግራይ ክልል ኃይሎች ከፍተኛ አዛዦች "ከተልእኳቸው ውጭ ለአንድ ሕገወጥ ቡድን ወግነው ግዚያዊ አስተዳደሩን የማፍረስ፣ ስርዓት አልበኝነትን የማንገስ እና ሠራዊት የመበተን ግልፅ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን አሳውቀዋል" በማለት የጦር መኮንኖቹ ውሳኔ ተችቷል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ