የትግራይ ክልል ሹም ሽር ያስከተለዉ ተቃዉሞ
ዓርብ፣ ሐምሌ 18 2017የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደርበክልሉ ደቡባዊ ዞን ያደረገዉን ያስተዳዳሪዎች ሹም ሽር የዞኑ ሕዝብ ባደባባይ ሰልፍ ተቃወመዉ።ከደቡባዊ ዞን የተዉጣጡ የሐገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት መሪዎች ሽም ሽሩን በመቃወም ትናንት ለትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ለጄኔራል ታደሰ ወረደ አቤቱታ አቅርበዉ ነበር።ፕሬዝደንቱ ከሐገር ሽማግሌዎቹና ከሐይማኖት መሪዎቹ ጋር በዝግ ያደረጉት ዉይይት ያለ አግባቢ ዉጤት መጠናቀቁ ተነግሯል። የደቡባዊ ዞን ሕዝብ ደግሞ የዞኑ ነባር አስተዳዳሪዎች በአዳዲስ መተካታቸዉን ዛሬ በማይጨዉ ከተማ ባደረገዉ ሠልፍ ተቃዉሞታል።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደርየደቡባዊ ዞን አስተዳደር አመራሮች ከስልጣናቸው ማውረዱ ተከትሎ ከአከባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ተቃውሞ እየተሰማ ይገኛል። በትላንትናው ዕለት 200 ገደማ የሚሆኑ ከተለያዩ የትግራይ ደቡባዊ ዞን ወረዳዎች የመጡ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ወደ መቐለ በመምጣት ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ጋር በዚሁ ጉዳይ ዙርያ የተወያዩ ሲሆን ነባሩ አመራር ለምን ከስልጣናቸው ወረዱ የሚሉ እና በወረዱበት ሂደት ዙርያ ለፕሬዝዳንቱ ቅሬታቸው መግለፃቸው ከተሳታፊዎች ሰምተናል። ከዚህ በተጨማሪ በዛሬው ዕለት የግዚያዊ አስተዳደር ውሳኔ የሚቃወም ሰልፍ በደቡባዊ ዞን አስተዳደር መቀመጫ ማይጨው ከተማ የተደረገ ሲሆን ዛሬ ጠዋት ስለነበረው ሁኔታ የነገሩን አቶ ግርማይ ፀጋይ፥ ህዝቡ ቁጣውን ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪ ትላንት በመቐለ ከትግራይግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ጋር የተወያዩት የደቡብ ትግራይ ዞን የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍል ተወካዮች፥ ለሚድያ ዝግ በነበረው ስብሰባ በአለመግባባት መጠናቀቁ ከተሳታፊዎች ሰምተናል።አስተያየታቸው ያጋሩን ከዞኑ አስተዳደር አካላት መካከል የሆኑት አቶ ግርማይ ፀጋይ፥ በትግራይ ደቡባዊ ዞን ጨምሮ በአጠቃላይ ክልሉ ያለው ሁኔታ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚሻ ያስረዳሉ
በተለይም የህወሓት ክፍፍል ተከትሎ በአቶ ጌታቸው ረዳ ከሚመራው ሐይል ጋር የተሰለፉት የትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳደር አካላት፣ የቀድሞ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ከስልጣን የተወገደበት አካሄድ፣ የትግራይ ሐይሎች ለአንድ የህወሓት ክንፍ በማዳላት የወሰዱት አቋም እና እርምጃ እንዲሁም በጀነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ካቢኔ አወቃቀር እና ሌሎች አካሄዶች በግልፅ ሲተቹ ቆይተዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ