ከኢኮኖሚው ዓለም፤ የትግራይ ጦርነት በኢኮኖሚው ላይ የጣለው ጠባሳ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 8 2017በጦርነቱ ምክንያት የተዳከመው የትግራይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ፥ ከጦርነቱ በኃላም ቢሆን አልተነቃቃም። በጦርነቱ የተፈጠረው ኪሳራ የሚያካክስ ድጋፍ ከመንግስት በኩል አለመደረጉ ብቻ ሳይሆን የቀጠለው ፖለቲካዊ ውጥረት ኢኮኖሚ ተዳክሞ እንዲቀጥል እንዳደረገው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። በዚህ ምክንያት በክልሉ ስራ አጥነት ተበራክቷል፣ ድህነት ተባብሷል። በክልሉ የሚገኙ ባለሀብቶችከአበዳሪ ባንኮች ጋር የገቡበት ውዝግብ ደግሞ ሌላ ፈተና ሲሆን፥ የፌደራሉ መንግስት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ይጠብቃሉ።
በተጨባጭ ቁጥራዊ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ እንኳን ቢሆን በትግራይ በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እጅግ ከፍተኛ እና ለመተካቱም ረዥም ግዜ የሚፈልግ መሆኑ የዘርፉ ተዋናዮች ይገለፃል። ከጦርነቱ መቆም ከሁለት ዓመት በኃላ ጭምር በትግራይ ይጠበቅ የነበረው ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት አሁንም አለመታየቱ ደግሞ በዜጎች ላይ የተራዘመ ችግር ፈጥሯል፤ ወጣቶች በስራ ማጣት እየተፈተኑ ይገኛሉ፣ ተስፋ ቆርጦ የሚሰደድ ቁጥርም እጅጉ ተበራክቷል። አርክቴክት እና የኢንቨስትመንት አማካሪው ዳንኤል ሰሙንጉስ በትግራይ በተለይም ከፕሪቶርያው ስምምነት በኃላ በርካቶች ተስፋ ሰንቀው ወደ ስራ በመግባት ላይ እንደነበሩ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ሆነው ጭምር የስራ እንቅስቃሴ መታየት ተጀምሮ እንደነበረ ያስታውሳል። ይሁንና ኢኮኖሚው የሚያነቃቃ የመንግስት ድጋፍ መጥፋት እንዲሁም በትግራይ የቀጠለው ፖለቲካዊ መካረር ተከትሎ ብዙም ሳይዘልቅ መዳከሙ ያነሳሉ።
የትግራይ ንግድ እና ዘርፍ ማሕበራት ምክርቤት ምልከታ
በትግራይ በደረሳቸው ውድመት አልያም በኪሳራ ምክንያት ከጦርነቱ በኃላ ወደ ስራ ያልተመለሱ ተላልቅ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። የትግራይ ንግድ እና ዘርፍ ማሕበራት ምክርቤት በክልሉ የሚገኙ ነጋዴዎች እና ኢንቨስተሮች በተራዘመ ችግር ውስጥ እና ኪሳራ ላይ መሆናቸው ይገልፃል። በትግራይ ያለው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ያብራሩልን የዓዲግራት ንግድና ዘርፍ ማሕበራት ፕሬዝደንት እና የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማሕበራት ቦርድ አመራር አባል ዲበኩሉ አለም ብርሃነ እንደሚሉት በትግራይ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራው የሚያካክስ ድጋፍ አለመደረጉ ተከትሎ ችግሮች ተባብሰው እንዲቀጥሉ እንዳደረገ ያነሳሉ።
የትግራይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መዳከም ተከትሎ፣ ስራ አጥነት ተንሰራፎቷል፣ ኢንቨስትመንት ቀንሷል፣ በዚህ ተስፋ የቆረጠ ወጣት ደግሞ በከፍተኛ መጠን ወደ ስደት እያመራ መሆኑ ይገለፃል። በመቐለ ያነጋገርናቸው ወጣቶች የሚሉት ይህንኑ ነው።
የትግራይ ነጋዴዎች ስሞታ
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአጠቃላይ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግርች ተቀዛቅዞ በቆየ እንቅስቃሴ ምክንያት ተቸግረው እንዳሉ የሚያነሱት በትግራይ የሚገኙ ኢንቨስተሮች ባንኮች ብድር እንዲመልሱ፣ የጦርነቱ ወቅት የብድር ወለድ እንዲከፍሉ እያስገደዷቸው መሆኑ በማንሳት ደግሞ ቅሬታዎች ያቀርባሉ። የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማሕበራት እንደሚለው «በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ሁሉም የመንግስት እና ግል ባንኮች ተዘግተው በቆዩበት፣ ገንዘብ ማንቀሳቀስ በማይቻልበት እንዲሁም ከፍተኛ ውድመት በደረሰበት ሁኔታ፥ የፋይናንስ ተቋማት የጦርነቱ ወቅት ወለድ ጭምር እንድንከፍል ማስገደዳቸው በክልሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ችግር እየፈጠረ ነው።»
ዲበኩሉ አለም ብርሃነ 'የትግራይ ንግድ ማሕበረሰብ ከመንግስት ይጠብቀው የነበረ ድጋፍ አላገኘም ብቻ ሳይሆን፥ በተቃራኒው በጦርነቱ ለወደመ ሀብት ዕዳ እንዲከፍል፣ ብድርና የብድር ወለድ እንዲሁም ቀጣታ ጭምር እንዲከፍል ተበይኖበት' ይላሉ።
በትግራይ ያሉ ከባንኮች ብድር የወሰዱ ባለሀብቶች እና የፋይናንስ ተቋማት መካከል ያለው ልዩነ፥ የተለየ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጠው የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማሕበራት ምክርቤት ጥሪ በማቅረቅ ላይ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማነቃቃት ለዘላቂ ሰላም ጭምር መሰረታዊ እርምጃ መሆኑ የሚያነሱት የኢኮኖሚው ዘርፍ ተዋናዮች፥ ተጨባጭ እርምጃዎች ከፌዴራሉ መንግስት እና የክልሉ አስተዳደር እንደሚጠበቅ ያነሳሉ።
ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚያነቃቁ እርምጃዎች በመውሰድ በትግራይ በከፋ ሁኔታ እየተስተዋለ ያለ የወጣቶች ስደት እና ተያያዥ ችግሮች መፍታት፥ በቅርቡ ስልጣን ከተረከበው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የሚጠበቅ ቀዳሚ እርምጃ ሊሆን እንደሚገባ በርካቶች አስተያየታቸው ያጋራሉ።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር