የትራምፕ የሰሞኑ ንግግር በተንታኞች ዓይን
ዓርብ፣ የካቲት 28 2017የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካ ኮንግረስ ባደረጉት ንግግር ከአገር ውስጥ ፖሊሲ እስከ ዩክሬን ጦርነት ባሉት ጉዳዮች ራሳቸውን እንደ ትክክለኛ ያያሉ።ነገር ግን ተንታኞች ንግግራቸው ሀገርን በጥልቅ የሚከፋፍል ነው ሲሉ ይተቻሉ።
አንዳንዶች እንደሚሉት የእሳቸው ንግግር በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ያለው ልዩነት ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ የሚያሳይ እና በሪፐብሊካኖች እና በዴሞክራቶች መካከል ምን ያህል የማይታረቅ ሀሳብ እንዳለ ለመጀመሪያ ጊዜ ግልጽ የሆነበት ነው።
ራሳቸውን በማወደስ ንግራቸውን የጀመሩት 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት፣ዶናልድ ትራምፕ፣ «በ 43 ቀናት ውስጥ ሌሎች በአራት እና ስምንት ዓመታት ውስጥ ካከናወኗቸው ተግባራት የበለጠ አከናውነናል" ብለዋል ።ሪፐብሊካኑም በጭብጨባ ድጋፋቸውን ገልፀውላቸዋል።
የበርሊን አስፐን ኢንስቲትዩት ኃላፊ የሆኑት ስቶርሚ-አኒካ ሚልድነር እንደሚሉት የፕሬዚዳንቱ ንግግር የምርጫ ዘመቻን የሚያስታውስ ነው።
«በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ ውስጥ ረጅሙ ንግግር ነበር። እናም ንግግሩ ከምክር ቤት ይልቅ የምርጫ ዘመቻ ንግግር ወይም የመክፈቻ ንግግር ይመስላል። ተመሳሳይ ትኩረት፣ ተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች እና በባይደን አስተዳደር ላይ ብዙ ትችቶች።ይህ ደግሞ ከመክፈቻ ንግግር ጋር ተመሳሳይ ነበር።»
«አሜሪካ ወደ ቀድሞ ክብሯ ተመለሰች»
«አሜሪካ ተመለሰች»በሚለው መፈክር ንግግራቸውን የጀመሩት ትራምፕ መንግስታቸው ስላስመዘገበው ከበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መውጣት፣ የሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤውን “የአሜሪካ ባሕረ ሰላጤ” ብሎ መሰየም እና ለሁለት ፆታዎች ብቻ እውቅና መስጠትን አንስተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ከእርሳቸው በፊት ከነበሩት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች በበለጠ ለ100 ደቂቃ ያህል ትኩረታቸውን በዋነኛነት የተኮሩት አሜሪካ ላይ ነው። ስለሀገራቸው የዋጋ ግሽበት በንግራቸው ያወሱት ትራምፕ፤ ተጠያቂው የቀድሞው መንግስት ነው ብለዋል።ነገር ግን ችግሩ እንዴት እንደሚፈታ መልስ መስጠት አልቻሉም። ቢሮክራሲን ለመቀነስ በተወሰዱ እርምጃዎች የአማካሪቸውን አወድሰዋል። የኤሎን ማስክ ዶጂ ባለስልጣን እንዳሉት በስድስት ሳምንታት ውስጥ 105 ቢሊዮን ዶላር ማዳን ተችሏል ። ነገር ግን ይህ አሃዝ በገለልተኛ ወገን ሊረጋገጥ አይችልም።ምክንያቱም መረጃው የሚመጣው ከማስክ ኤጀንሲ ብቻ ነው።
የመኪናዎች እና የጉምሩክ ቀረጥ
ምንም እንኳን ብዙ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በአሜሪካ የፍጆታ ዋጋን ከፍ ሊያደርግ ይችላል በሚል እያስጠነቀቁ ቢሆንም ፤ዶናልድ ትራምፕ የታሪፍ ፖሊሲያቸውን በድጋሚ ተከላክለዋል።ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ በአውሮፓ እና በህንድ የመኪና ኢንዱስትሪዎች ላይ ተጨማሪ የቀረጥ እርምጃዎች ሊጣሉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። እንደ ሚልድነር ገለፃ የትራምፕ ፖሊሲ ከመደበኛው የኢኮኖሚ ህግ ጋር የሚጋጭ ነው።
«ከመደበኛ ኢኮኖሚ እና በአብዛኛው ካለፈው ፖሊሲ ጋር የሚቃረን የታሪፍ እይታ አለው።. ታሪፉ የሚከፈለው በውጭ ኩባንያዎች ነው። እና ለአካባቢው ህዝብ የማይተላለፍ ነው ብሎ ያምናል።.ያ በእርግጥ እውነት አይደለም.»
ትራምፕ “በግብርና ምርቶች ላይ ታሪፍ ሲጥሉ ስለራሳቸው ሀገር ገበሬዎች የተናገሩት አስገራሚ ነበር።ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት «መጀመሪያ ላይ አንዳንድ አለመረጋጋት ይኖራል. ነገር ግን በእኛ ላይ ምንም ችግር የለውም።ብዙም አይሆንም።» ነበር ያሉት። ሚልድነር እንደገለጹት ይህ መግለጫ ትራምፕ ፖሊሲዎቹ ወደ ችግሮች እንደሚመሩ ማወቃቸውን ያሳያል።
«ይህ ወደ ችግር እንደሚመራ የሚያውቅ ይመስላል።ግን አንድ የተወሰነ ትረካ በመፍጠር እና በውጤቱም በኢኮኖሚ የተጎዱትን ለማሳመን በጣም ጥሩ ነው ። በእውነቱ የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ ሁኔታ ሲጨምር ይህንን ትረካ በማዞር ይሳካለት እንደሆነ አላውቅም። በመጀመሪያው የአስተዳደር ዘመን ግን ሠርቷል።»
የውጭ ፖሊሲ በስድስት ደቂቃ
ዶናልድ ትራምፕ ከአንድ ሰአት በላይ በፈጀው ንግግራቸው ስለ የውጭ ፖሊሲ ብዙም አላነሱም። ስለ አለም ግጭት ያወሩት ከስድስት ደቂቃ አይበልጥም።ስለ ዩክሬን ከአምስት ደቂቃ በታች ጋዛን በተመለከተ 49 ሰከንድ ብቻ አውርተዋል። ትራምፕ "ወደ ዘላቂ ሰላም ለመቅረብ በተቻለ ፍጥነት ወደ ድርድር ለመምጣት" ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪደብዳቤ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል። በዋይት ሀውስ ለዩክሬን ሊሰጥ በሚችለው የዩኤስ የደህንነት ዋስትና በተመለከተ ያለፈው አርብ በዋይት ሀውስ ታይቶ የማይታወቅ ቅሌት ከተፈጠረ ወዲህ፤ ዜለንስኪ አሁን የታቀደውን የጥሬ ዕቃ ስምምነት ከአሜሪካ ጋር ለመፈረም ዝግጁ ሆነዋል።
ትራምፕ በንግግራቸው ስለ የደህንነት ዋስትናዎች ምንም አላነሱም። ትራምፕ ከዩክሬን ጋር ባለው ግጭት የሩሲያ መሪዎች "ሰላም" እንደሚፈልጉ "ምልክቶች" ማየታቸውን ተናግረዋል ። ሆኖም ትራምፕ ወደዚያ የሚያደርሰው ፍኖተ ካርታ ምን እንደሚመስል በትክክል አላብራሩም።
በሌሎች የውጭ ፖሊሲ ጉዳዮች ትራምፕ ብዙም አስታራቂ አልነበሩም። በድጋሚ የፓናማ ካናልን በአሜሪካ ቁጥጥር ስር እንደሚመልስ ዝተዋል። በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገች እና የዴንማርክ ንብረት የሆነችውን ግሪንላንድን ለመቆጣጠር እንደሚፈልጉም «በአንድም ሆነ በሌላ እናገኘዋለን »-ሲሉ በድጋሚ አስታውቀዋል። የቤርትልስማን ፋውንዴሽን ባልደረባ ብራንደን ቦረን ዩናይትድ ስቴትስ ከግሪንላንድ ጋር በተያያዘ ቀጥተኛ ወታደራዊ እርምጃ እንድትወስድ አይጠብቅም ይላሉ። ሆኖም፣ በዴንማርክ እና በግሪንላንድ ላይ ያለው ጫና ሊጨምር እንደሚችል ይገምታሉ። የአሜሪካዊቷ ተንታኝ ሚልድነር ከፓናማ መተላለፊያ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ የመሠረተ ልማት አውታሮችን የአሜሪካ ኩባንያዎችበከፊል እንደሚገዙ እና የአሜሪካ መንግስትም ይህንን እንደሚደግፍ ገልፀዋል።
የዴሞክራቶች አቅም ማጣት
በትራምፕ ንግግር ወቅት በዴሞክራቶች በኩል ተደጋጋሚ ተቃውሞዎች ነበሩ። ብዙዎቹ የፓርላማ አባላቱ የዩክሬንን ቢጫ እና ሰማያዊ ቀለም ያላቸው መለያዎች ደረታቸው ላይ አድርገዋል። አንዳንዶቹ በተቃውሞ አዳራሹን ለቀው ወጥተዋል። ተወካይ ጃስሚን ክሮኬት "ተቃወሙ" የሚል መፈክር ያለበት ቲሸርት አሳይተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ሁሉ ተስፋ አልቆረጡም። እናም ሁሉንም እርምጃዎች እንደ "የአሜሪካ የማይቀር የህልም መታደስ" ሲሉ ተናግረዋል። በመጨረሻም "ገና እየጀመርን ነው!" በማለት ለዴሞክራቶች ነግረዋል።
ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ