የትራምፕ እና ዜሌኒስኪ ውዝግብ
ቅዳሜ፣ የካቲት 22 2017ዓለም በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እየተመለከተ የተፈጠረው ክስተት ግን ሁኔታው ዋሽንግተን ለኪየቭ ልትሰጥ የምትችለውን የወደፊት ድጋፍ እጣ ፈንታ ጥርጣሬ ውስጥ ጨምሮታል።
የዩክሬይንን ማዕድን በጋራ ለመጠቀምና፣ ለቀጥዩ ሰላም መስፈን የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ወደ ኋይት ሃውስ ያቀኑት የዩክሬይኑ ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዜሌንስኪ ያሰቡት ሳይሳካ፣ ለታሪክ የሚቀመጥ ልዩ ፖለቲካዊ እሰጣገባ ነው ያስተናገዱት።
ዜሌንስኪ ለአሜሪካ ድጋፍ በቂ ምስጋና ባለማሳየታቸው ቅሬታቸውን ያሰሙት ትራምፕ እና ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ጄዲ ቫንስ መውጫ መግቢያው የጠፋቸውን፣ ማጠፊያው ያጠራቸውን ዜሌኒስኪን ከሩሲያ ጋር ሊደረግ በሚችለው የሰላም ስምምነት መንገድ ላይ ቆመዋል፣ ሰላምና ስምምነትንም አይፈልጉም ብለው ከሰዋቸዋል። የዚሌኒስኪ መሠረታዊ ጥያቄ ደግሞ ሊፈረም ከታቀደው የውድ ማዕድን የጋራ ማልማት ስምምነት ባሻገር ከአሜሪካ የሚሰጠው የሰላም ዋስትና ምንድነው፣ ደግሞም የሰላም ስምምነትን ሲጥሱ የኖሩት ፑቲንስ አሁን ቃላቸውን ለመተበቃቸው ምን መተማመኛ አለን የሚል ነበር።
እንዲህ እንዲህ እያለ የተካረረው እሰጣገባ መደማመጥ ወዳጣ ጭቅጭቅነት ተቀየረ። የሚወጡትም ቃላት፣ ከዲፕሎማሲው ጎራ፣ የአንድ ሃገር መሪ በፕሮቶኮልና በክብር ከተቀበለው የሌላ ሃገር መሪ ጋ የሚያደርገው አይነት አልበረም። “ከኛ ውጪ የምትጫወትበትም፣ የምታሸንፍበትም ካርድ የለህም” አሉ ፕሬዝዳንት ትራምፕ። “እኔ ካርታ ጨዋታ እየተጫወትኩ አይደለም” መለሱ ዜሌኒስኪ። ትራምፕ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው፣ “በሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ላይ ነው ቁማር የምትጫወተው። ከሦስተኛ የዓለም ጦርነት ጋር ቁማር የምትጫወተው” አሉ።
“እናም” አሉ ዶናልድ ትራምፕ፤ “ወይ የምትባሉትን ሰምታችሁ ትስማማላችሁ አልያም እኛ ከዚህ ጉዳይ ውስጥ እጃችንን እናወጣለን፣ እኛ ወጣን ማለት ደግሞ ጦርነቱን ብቻችሁን መጋፈጣችሁ ነው።”
ዜሌንስኪ ክፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋ መገናኛ ብዙኃን በቀጥታ ያሰራጩት የጋለ ክርክር ማድረጋቸው፣ በትራምፕ ዘንድ አልተወደደላቸውም። የእንግሊዙና የፈረንሳይ መሪወች እንኳን ሳይቀሩ በዚህ ሳምንት ትራምፕን ሲያገኙ፣ ሙገሳና ክብር የሚወዱትን ትራምፕ እየደለሉ፣ እያሞካሹ፣ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የሚፈልጉትን ለማስፈጸም ሞክረዋል። የዜሌንስኪ ቀጥተኛና ግልጽ መሆን ያበሳጫቸው ትራምፕ፣ “ዜሌንስኪ ጓይት ሃውስንም ሃገራችንንም አላከበረም፣ ለሰላምም ዝግጁ አይደለም፣ ዝግጁ ሲሆን መምጣት ይችላል።” ብለዋል። እናም ተዘጋጅቶ የቀረበው የምሳ ግብዣም ሳይደረግ፣ ውይይቱም፣ ስምምነቱም፣ የጋራ መግለጫውም ተሰርዞ ዜሌንስኪ ክኋይት ሃውስ ተባረው ወዲያው ወጥተው ሄደዋል።
ይሂው ክስተት የመገናኛ ብዙሃን ዋና መነጋገሪያ ሆኗል። ከትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊወች ውስጥ አንዱ የሆኑት የሪፐብሊካኑ እንደራሴ ሊድሲ ግራም ትራንምፕን ለአሜሪካ ክብር የቆሙ፣ ዜሌንስኪን ደግሞ ክብረቢስና ለሃገራቸው ሰላም ማምጣት የማይችሉ ብለው ማጣጣል ብቻ ሳይሆን ወይ ሃሳባቸውን እንዲለወጡ አልያም ከስልጣናቸው እንዲልቁም ጠይቀዋል።
የዲሞክራቱ እንደራሴ ሴት ዊልበር ሞውልተን በበኩላቸው ዜሌኒስኪን ጀግና ትራምፕና ጄዲ ቫንስን ደግሞ ፈሪና የቭላድሚር ፑቲን አገልጋይ ውሾች ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል።
ሌላው የዲሞካርት ፓርቲ እንደራሴ ጃክ ሪድ ደግሞ ይሄንኑ ያልተለመደ ግብግብ "የፖለቲካ ጥቃት እና የአሜሪካ መሪነት አሳፋሪ ውድቀት" በማለት ጠርተውታል። ሁኔታውን ጭካኔ የተሞላበት ትዕይንት ሲሉ የገለጹት ሪድ ሁነቱ አሜሪካ በአለም ላይ ባላት ተሰሚነት እና አቋም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ገልጸዋል። አያይዘውም፣ ትራምፕ እና ቫንስ አሜሪካ እምነት ሊጣልበት የማይችል፣ ቃሏን የማትጠብቅ ሃገር እንደሆነች ለወዳጅም ለጠላትም መልዕክት አስተላልፈዋል ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት ይሄ ክስተት ብዙወችን አስገርሟል፣ አስደንግጧል። የዩክሬይን ነገን አስግቷል። የአውሮፓን ተስፋ አጨፍግጓል። ይሄንን መጯጯህ ግጭት እንደ ጣፍጭ የሙዚቃ ቃና ታላቅ ደስታን ተላብሰው የሚሰሙት አንድ ሰው፣ ለወትሮውም የምዕራቡ አለም መከፋፈል ጾም ጸሎታቸው የሆነው፣ የራሺያው ቭላድሚር ፑቲን ናቸው።